ፕሪምየር ሊግ | የጉዳት ዝርዝሮች

በባህር ዳር አምስት የጨዋታ ሳምንታትን ያሳለፈው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ወደ ድሬዳዋ ሲሻገር በየክለቦቹ የተፈጠሩ 26 ጉዳቶች የሚገኙባቸውን ደረጃ ተመልክተናል።

የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያዋ አስተናጋጅ ከተማ በነበረችው ባህር ዳር 39 ጨዋታዎችን አካሂዷል። ከእነዚህ የአምስት ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ ሀዋሳ ከተማ ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ስብስባቸው ከጉዳት ነፃ ሆነው ወደ 6ኛው ሳምንት ተሻግረዋል። በቀሪዎቹ 12 ቡድኖች ውስጥ ደግሞ የ26 ተጫዋቾች ጉዳት ላይ እንደሚገኙ ከየክለቦቹ ማረጋገጥ ችለናል።

– ወላይታ ድቻ ስድስት ጉዳቶች አሉበት። ተከላካዩ አንተነህ ጉግሳ የተረከዙ ጅማት (Calcaneous tendon) ላይ ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሞ ነበር። ለ21 ቀናት ጀሶ እንዲደረግለት በሀኪም ታዞ የነበረ ሲሆን በቀጣይ ከ4-6 ሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ ለማወቅ ተችሏል። ይህም ማለት በድሬዳዋ የሚደረጉ ጨዋታዎች ያመልጡታል። አማካዩ እንድሪስ ሰዒድ ጉልበቱ ላይ menscial ጉዳት አጋጥሞታል። አብነት ይስሀቅ ሆዱ ላይ ህመም ከተስተዋለበት በኋላ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን መኖሩ በመታወቁ ህክምና እየተደረገለት ይገኛል። ፂዮን መርድ በበኩሉ የቀኝ የጉልበት ጉዳት የገጠመው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት እያገገመ ይገኛል። ወንድወሰን አሸናፊ ራሱን የመሳት ችግር አጋጥሞት ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን የህክምና እርዳታ ከተደረገለት በኋላ ጥሩ የጤንነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል። አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱ ቀኝ ጉልበቱ ላይ ከደረሰበት ጉዳት በኋላ ምርመራ የተደረገለት ሲሆን ሰኞ ወደ ሙሉ ልምምድ ይመለሳል።

– እንደ ድቻ ሁሉ ስድስት ጉዳቶች ባሉበት ወልቂጤ ከተማ የሊጋመንት ጉዳት የገጠመው ተከላካዩ ቴዎድሮስ ሀሙ ለስድስት ሳምንታት ከጨዋታ እንደሚርቅ ታውቋል። ባተጨማሪ ሮበርት ኦዶንካራ ያለፉትን 2 ቀናት ልምምድ ቢሰራም እጁ ላይ መጠነኛ ጉዳት ያለበት ሲሆን ኤፍሬም ዘካሪያስ እና ጌታነህ ከበደ ቁርጭምጭሚት ፣ ጀማል ጣሰው የጉልበት እንዲሁም አፈወርቅ ኃይሉ የታፋ ጡንቻ ጉዳት ማስተናገዳቸው ታውቋል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ጉዳቶች አሉበት። በአዳማው ጨዋታ የቁርጭምጭሚት ጉዳት የገጠመው ዳዊት ተፈራ የታሰረለት ጀሶ ከ 15 ቀናት በኋላ የሚፈታ ሲሆን አማካዩ በድሬዳዋው ውድድር ላይ አይደርስም። ሌላው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ የጡንቻ መሰንጠቅ ጉዳትየገጠመው ተመስገን ዮሐንስ ነው። ግብ ጠባቂው ቀዶ ጥገና የተደረገለት ሲሆን ከአንድ ወር በኋላ ወደ ቀላል እንቅስቃሴ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

– መቻል ውስጥ ይህ ነው የሚባል ረጅም ጉዳት ያጋጠመው ተጫዋች በአሁኑ ወቅት የለም፡፡ ተሾመ በላቸው የጉልበት ጉዳት አጋጥሞት የነበረ ሲሆን MRI ምርመራ ከተደረገለት በኋላ በጉልበት መገጣጠሚያው ውስጥ ፈሳሽ እንደተቋጠረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ጉዳት ከጨዋታ ለአንድ ሳምንት ያህል ሊያርቀው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ሌላኛው ጉዳት ያለበት ተጫዋች ተስፋዬ አለባቸው ሲሆን hamstring ጉዳቱ ለውጥ እያመጣ ሲሆን ከዋናው ቡድን ጋርም ተቀላቅሎ ልምምድ እየሰራ ይገኛል፡፡

– በአዳማ ከተማ በኩል ጉዳት ላይ ያሉ ሁለት ተጫዋቾች አሉ፡፡ እነርሱም ዳዋ ሆቴሳ እና ሚሊዮን ሰለሞን ናቸው፡፡ ዳዋ ጉዳት የገጠመው ጉልበቱ ላይ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል፡፡ ሚሊዮን hamstring ጉዳት ካጋጠመው በኋላ እርዳታ እየተደረገለት ቆይቶ ጥሩ ለውጥ ማሳየት ቢችልም MRI ከተነሳ በኋላ ለ15 ቀናት ዕረፍት ማድረግ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

– ፋሲል ከነማ ውስጥ ሃብታሙ ተከስተ የኪንታሮት ህመም (hemorrhoid) አጋጥሞት የቀዶ ጥገና ህክምና የተደረገለት ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከቡድኑ ጋር የለም፡፡ ሱራፌል ዳኛቸው የጡንቻ መሰንጠቅ (muscle tear) ያጋጣመው ሲሆን በቅርቡ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

– በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ተስፋዬ በቀለ ካጋጠመው hamstring ጉዳት እያገገመ ሲገኝ በአሁኑ ወቅት የማገገሚያ (rehabilitation) ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ በሚመጡት 2 እና 3 ቀናትም ወደ ሙሉ ልምምድ ተመልሶ ቡድኑን እንደሚቀላቀል የደረሰን መረጃ ያሳያል፡፡

– በሲዳማ ከተማ በኩል አንጋፋው አጥቂ ሳላሀዲንም ከብሽሽት ጉዳቱ እያገገመ ለድሬዳዋ ጨዋታዎች ይደርሳል ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም በሁለቱ እግሮቹ ላይ ያለው የብሽሽት ጉዳት ለተጨማሪ ጊዜያት ከሜዳ እንደሚያርቀው ታውቋል።

– በኢትዮጵያ ቡና በኩል ጉዳት ያጋጠመው ተጫዋች መስፍን ታፈሰ ሲሆን Quadriceps ( የታፋው የፊት ጡንቻ) ነው የተጎዳው። ትተጫዋቹ የ6ኛ ሳምንት ጨዋታ የሚያመልጠው ሲሆን በቀጣይ ቀናት አገግሞ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

– በባህር ዳሩ ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ ተቀይሮ የወጣው የለገጣፎ ለገዳዲው ዮናስ በርታ ለምን ያህል ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ ባይታወቅም የጀርባ ጉዳት እንዳስተናገደ ተጠቁሟል።

– ባህር ዳር ውስጥ ጉዳት ያለበት ተጫዋች ያሬድ ባየህ ሲሆን ያጋጠመው hamstring ጉዳት ነው። ጉዳቱ ለ2 ሳምንታት ከሜዳ ያርቀዋል።

– በበርካታ ጉዳቶች ዓመቱን የጀመረው ኢትዮጵያ መድን ውስጥ አሁን ላይ ሳሙኤል ዮሐንስ ለአንድ ወር የሚያርቀው ጉዳት አለበት። የMRI ምርመራ የተደረገለት ተጫዋቹ ደረጃ ሦስት የብሽሽት ጉዳት እንደገጠመው ታውቋል።

ያጋሩ