ሪፖርት | የጣና ሞገደኞቹ የድሬዳዋ ቆይታቸውን በድል ጀምረዋል

አምስት ጎሎችን ያስመለከተን የባህር ዳር ከተማ እና ትዮጵያ መድን ጨዋታ በባህር ዳር ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ኢትዮጵያ መድን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት መቻልን ሲያሸንፍ ከተጠቀመበት ቋሚ ተሰላፊዎች መካከል በጉዳት በሌለው ተስፋዬ በቀለ ምትክ ያሬድ ካሳዬን በብቸኝነት ቀይሯል። በተስተካከይ መርሀግብር ከፋሲል ጋር ነጥብ የተጋሩት ባህር ዳር ከተማዎች በአንፃሩ ያሬድ ባዬን በተስፋዬ ታምራት ፣ በረከት ጥጋቡን በአለልኝ አዘነ ፣ አደም አባስን በሀብታሙ ታደሰ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል፡፡

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ጅምሩን ያደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የግብ ሙከራን ያሳየን ገና በጊዜ ነበር፡፡ የመሀል ዳኛው አሸብር ሰቦቃ ጨዋታውን ባስጀመሩበት ቅፅበት በቅብብሎች የመድን የግብ ክልል የደረሱት ባህር ዳር ከተማዎች አለልኝ አዘነ ከቀኝ መስመር በኩል ወደ ሳጥን ሲያሻግር ሀብታሙ ታደሰ በግንባር ገጭቶ አቡበከር ኑራ ባወጣበት አስገራሚ ሙከራ ተጀምሯል፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ አርባ አምስት ሁለቱም ቡድኖች ትኩረታቸውን በብዛት በሚሻገሩ ኳሶች ላይ አድርገው መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በዚህም ከየትኛውም የሜዳ ክፍል ኳስን ለአጥቂ ክፍሉ አሻግሮ ጎል ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ቢስተዋሉም የወጥነት ችግሮች መታየታቸው ሙከራዎችን በበቂ ሁኔታ እንዳንመለከት አድርጓል፡፡

33ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ በቀለን ተክቶ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የገባው ወጣቱ ተከላካይ ያሬድ ካሳዬ ወደ ግብ ክልል ሲያሻግር የባህር ዳር ከተማው ግብ ጠባቂ ታፔ አልዛየር ስህተት ታክሎበት ብሩክ ሙሉጌታ ኳሷን ቀድሞ አግኝቷት በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ቡድን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ጎል ካስተናገዱ በኋላ በይበልጥ ወደ ቀኝ መስመር በተሰለፈው ዱሬሳ ሹቢሳ አጋድለው ለማጥቃት የታተሩት የጣና ሞገደኞቹ ወደ ጨዋታ የመለሳቸውን ጎል አግኝተዋል፡፡ 37ኛው ደቂቃ ላይ ሔኖክ ኢሳያስ ከማዕዘን ምት ያሻማትን ኳስ ተከላካዮች በኋላ ላይም አማካዩ ዮናስ ገረመው በአግባቡ በግንባሩ ማራቅ ያልቻለውን ኳስ ከጀርባው የነበረው ተከላካዩ ተስፋዬ ታምራት አግኝቷት እጅግ አስገራሚ ጎል በግምት ከ40 ሜትር ርቅት አቡበከር ኑራ መረብ ላይ አሳርፎ ቡድኑን 1-1 አድርጓል፡፡

የጨዋታ ቅኝት ውስጥ የገቡት ባህርዳሮች በዱሬሳ እና ሀብታሙ የኮሪደር አጨዋወት ጎልን ካገኙ በኋላ በይበልጥ ለመጫወት ቢጥሩም ወደ መሪነት ለመምጣት ግን አላስቻላቸውም፡፡ 43ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል ሀብታሙ አሻምቶ ግልፅ ዕድልን ዱሬሳ ያመከነበት አስቆጪዋ ሙከራ ነበረች፡፡

ከዕረፍት መልስ ባህርዳር ከተማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ከተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች ጋር አቀናጅቶ የወሰደበት ነበር፡፡ ለዚህም ማሳያው ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ አምስት ደቂቃዎች ብቻ እንደተቆጠሩ የመድኑ የመሀል ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ ለአስጨናቂ ፀጋዬ የሰጠውን ኳስ ተጫዋቹ ከጀርባው የነበረውን ፉዓድ ፈረጃን መመልከት ባለመቻሉ አማካዩ በፍጥነት ነጥቆት ባህር ዳርን ወደ 2-1 ያሸጋገረች ጎል በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል፡፡

ከመሪነት ወደ ተመሪነት የሄዱት መድኖች በቀዳሚው አጋማሽ በጉዳት በወጣው ሲሞን ፒተር ምትክ እዮብ ገብረማርያምን የለወጡ ሲሆን መሀል ክፍሉ ላይ የነበረባቸውን ክፍተት ለመድፈርን በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ዮናስ ገረመውን በጋናዊው ሀቢብ መሀመድ በመተካት ተከላካዩ አስጨናቂ ፀጋዬን ከኋላ ወደ አማካይ ስፍራ በማምጣት መሀል ሜዳ ላይ የነበረባቸውን ክፍተት ለመድፈን ጥረት ማድረግ ቢችሉም በተቃራኒው በተረጋጋ እንቅስቃሴ በፉአድ ፈረጃ የሚመራው የባህር ዳር ከተማ የአማካይ ክፍል የተሻለ ሆኖ መገኘቱ ሦስተኛ ጎልን መመልከት እንድችል አድርጎናል፡፡

63ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል አስማማው በአንድ ሁለት ቅብብል ያገኘውን ኳስ ለአለልኝ ሰጥቶት ግዙፉ አማካይ ወደ ጎል አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ሲተፋው ከፊቱ የነበረው ሀብታሙ ታደሰ ወደ ጎልነት ለውጦ የባህር ዳርን የግብ መጠን ወደ ሦስት አሳድገዋል ፤ ተጫዋቹ ጎሏን ካስቆጠረ በኋላ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ ሦስት ጎሎች መረባቸው ላይ ያረፈባቸው መድኖች በሂደት ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት በተለይ ኪቲካ ጀማን የጥቃት መስመራቸው አድርገው ለመጫወት ብርቱ ጥረትን ሲያደርጉ ታይቷል፡፡ 

72ኛ ደቂቃ ላይ ኪቲካ ከራሱ መነሻዋን ያደረገች ኳስን ወደ ሳጥን ሰብሮ በመግባት ወደ ጎል ሲመታው ግብ ጠባቂው ታፔ አውጧታል፡፡ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ቀይሮ በማስገባት ጎል ለማስቆጠር አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አማራጮችን በቀሩት ደቂቃዎች መውሰድ ችለዋል፡፡ ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት ላይ ከመሀል ሜዳው ኪቲካ ጀማ የደረሰውን ኳስ ግብ ጠባቂው ታፔን አልፎ በማስቆጠር መድንን 3-2 ያደረገ ቢሆንም ጨዋታው በጣና ሞገዶቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ያጋሩ