መረጃዎች | 23ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉ የድሬዳዋ ቆይታ ሁለተኛ ቀን ነገ ቀጥሎ ሲውል ሁለቱን የነገ መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ይቀርባሉ።

መቻል ከ ወላይታ ድቻ

በተለያየ ምክንያት ሙሉ ሦስት ነጥቡን አጥብቀው የሚፈልጉትን ሁለቱ ቡድኖች የሚያገናኘው የነገው 10 ሰዓት መርሃግብር ለአሸናፊው ቡድን ከሚኖረው ጠቀሜታ አንፃር ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይታመናል።

አዲሱ የውድድር ዘመን ሲጀመር በርካቶች መቻልን የተሻለ የውድድር ዘመን ያሳልፋሉ ብለው ከገመቷቸው ቡድኖች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ቢመደቡም በብዙ መልኩ ተቀይሮ የቀረበው መቻል ግን እስካሁን በሚፈለገው ልክ እየተንቀሳቀሰ አይገኝም። በሊጉ እስካሁን ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ አሸንፈው በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግደው በሊጉ በ6 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በክረምቱ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ያስፈረሙት መቻሎች በተለይም ቡድኑ በእጅጉ ያሻሽላሉ የተባሉ
ጥራታቸው የላቁ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን ከግለሰቦች ባለፈ እስካሁን እንደ ቡድን የተዋሀደ እንቅስቃሴን ለማድረግ ተቸግረው ተመልክተናል። በርከት ያሉት አዳዲስ ፈራሚዎች በቀደመው ክለብ ካስመለከቱን ነገር አንፃር ፍፁም ደካማ ጊዜያትን በመቻል እያሳለፉ ይገኛል። በተለይም የማጥቃት ጨዋታ ከፍተኛ ድክመት የነበረበትን ቡድን ለማሻሻል መቻል ቤት የደረሱት ከነዓን ማርክነህ ፣ ፍፁም ዓለሙ እና በረከት ደስት በጋራ እስካሁን አንድ የጎል ተሳትፎ ብቻ የማስመዝገባቸው ጉዳይ ቡድኑ በምን ያህል መጠን መሻሻል እንደሚገባው ማሳያ ነው። መቻሎች በነገው ወሳኝ ጨዋታ የወጣቱ አጥቂያቸውን ተሾመ በላቸው እና አማካዩን ተስፋዬ አለባቸውን አያገኙም።

በሊጉ ምንም እንኳን አንድ ቀሪ ጨዋታ ያላቸው ወላይታ ድቻዎች አሁን ላይ በሁለት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛሉ። ሊጉን በተከታታይ የአቻ ውጤቶች የከፈቱት ድቻዎች ባደረጓቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ግን ተከታታይ ሽንፈትን አስተናግደዋል። በአራት የሊግ ጨዋታዎች እስካሁን ቃልኪዳን ዘላለም ኤሌክትሪክ ላይ ካስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ውጭ በክፍት ጨዋታ የመጀመሪያ ግባቸውን ፍለጋ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች የውድድር ዘመናቸውን ወደ መስመር የሚመልስላቸውን ሙሉ ሦስት ነጥብ ፍለጋ መቻልን ይገጥማሉ። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በነገው ጨዋታ በርከት ያሉ ወሳኝ ተጫዋቾቹን አያገኙም። ፂዮን መርዕድ ፣ አንተነህ ጉግሳ ፣ ስንታየሁ መንግሥቱ ፣ እንድሪስ ሰዒድ እና ቢንያም ፍቅሬ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆናቸው ሲረጋገጥ ግብ ጠባቂው ወንደሰን አሸናፊ ግን ለነገው ጨዋታ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም አስራ አራት ያህል ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች ስድስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዙ መቻሎች ደግሞ ሦስት ጨዋታ ሲረቱ የተቀሩት አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል።

ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት አባይነህ ሙላት እንዲመሩት የተመደቡ ሲሆን ሶሬሳ ዱጉማ እና መሐመድ ሁሴን በረዳትነት እንዲሁም ደግሞ ተስፋዬ ግሩሙ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል። ይህም ጨዋታ ለአራቱም ዳኞች የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ጨዋታቸው እንደሚሆን ይጠበቃል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መንገድ እየተጓዙ የሚገኙትን ወልቂጤ ከተማን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ሌላኛው ተጠባቂ መርሃግብር ነው።

ሊጉን በሁለት ተከታታይ ድሎች መክፈት የቻሉት ወልቂጤ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ግን ተከታታይ ሽንፈቶችን በማስተናገድ በ6 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ተጋጣሚያቸው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ በተቃራኒው በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ቢያስተናግዱም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ባሳኳቸው አውንታዊ ውጤቶች በ5 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በሊጉ 17 አዳዲስ ተጫዋቾችን በክረምቱ የዝውውር መስኮት በመቀላቀል ከሊጉ ክለቦች ቀዳሚ የሆኑት ወልቂጤዎች በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ባሳኳቸው ድሎች ተሸፍነው የነበሩ ጥያቄዎች አሁን ላይ ዳግም መነሳት ጀምረዋል። በቡድን ውህደት እና በተጫዋቾች ጥራት ዙርያ ጥያቄዎች እየተነሱበት የሚገኘው የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድኑ ይህን ሂደት ለማለዘብ ቶሎ ወደ ውጤት መመለስ የግድ ይለዋል።

ቡድኑ በሊጉ ካስቆጠራቸው አምስት ግቦች ውስጥ ሦስት(60%) ማስቆጠር የቻለው ጌታነህ ከበደ ለቡድኑ ሁለንተናዊ አጨዋወት እጅግ ወሳኙ ሰው ስለመሆኑ ወልቂጤ ከተማዎች በሲዳማ ቡና የተሸነፉበት የመጨረሻ ጨዋታ በሚገባ ማሳያ ነው። በቁርጭምጭሚት ጉዳት ምክንያት በተጠባባቂነት በጀመረበት ጨዋታ በ78ኛው ደቂቃ ተቀይሮ እስኪገባ ድረስ ወልቂጤዎች ፍፁም ደካማ የነበሩ ሲሆን የጌታነህ ከበደን መግባት ተከትሎ ግን ቡድኑ ፍፁም ተሻሽሎ ተመልክተናል። በነገው ጨዋታም ከጉዳቱ ሙሉ ለመሉ ባያገግምም የተወሰኑ ደቂቃዎችን እንደሚጫወት ይጠበቃል።

በተጨማሪነት በርከት ያሉ ተጫዋቾቻቸው አሁንም በጉዳት የማያገኙት ወልቂጤ ከተማዎች በነገው ጨዋታ በሊጋመንት ጉዳት የማይኖረውን ቴዎድሮስ ሀሙን ጨምሮ አፈወርቅ ኃይሉ ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን ግብ ጠባቂዎቹ ጀማል ጣሰው እና ሮበርት ኦዶንካራ መጠነኛ ጉዳት ቢኖርባቸውም ከሁለቱ አንዱ በቋሚ ተሰላፊነት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በብዙ መመዘኛዎች ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን በማሳየት ላይ ይገኛል። ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ማግስት ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች እድገት እያሳየ የሚገኘው ቡድኑ በአውንታዊ አጨዋወት ውስጥ በመከላከሉ የተረጋጋ እንዲሁም በማጥቃቱ ተስፋ ሰጪ መሻሻል እያስመለከተን ይገኛል።

ከቡድኑ መሻሻል በስተጀርባ በሊጉ እጅግ አስደማሚ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው አማካዩ አብነት ደምሴ ተጠቃሹ ተጫዋች ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ቡና በውሰት ቆይታ በማድረግ ራሱን በሊጉ ያስተዋወቀው አብነት ደምሴ ዘንድሮ በኤሌክትሪክ ቤት በመከላከሉ ሆነ በማጥቃቱ አስደናቂ አበርክቶን እያደረገ ይገኛል። በድምሩ በአራት ግቦች ላይ ( 3 ጎሎች + 1 አመቻችቶ በማቀበል) ተሳትፎ ማድረግ ችሏል። ከዚህ ባለፈም የፊት አጥቂው ሄኖክ አየለም እንዲሁ ለቡድኑ መሻሻል አይነተኛ ሚናን እየተወጣ ይገኛል።

በኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኩል ጉዳት ላይ ከሚገኘው ተከላካያቸው ተስፋዬ በቀለ ውጭ የተቀረው የቡድን ስብስብ ለነገ ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠናል።

ለሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የመጀመሪያ የሚሆነውን መርሃግብር ሚካኤል ጣዕመ በዋና ዳኝነት እንዲሁም ማዕደር ማረኝ እና ደረጀ አመራ ረዳቶች ሲሆኑ ተከተል ተሾመ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ለጨዋታው ተመድበዋል፡፡