ከፍተኛ ሊግ | ሰበታ ከተማ በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ዝግጅት ጀምሯል

አሰልጣኝ ታዬ ናኒቻን የቀጠረው ሰበታ ከተማ አስራ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የስድስት ነባር ተጫዋቾችን ውልም አድሷል፡፡

ከተጠናቀቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን ከወረዱ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሰበታ ከተማ በከፍተኛ ሊጉ ለሚያደርገው ጠንካራ ጉዞው አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ መቀላቀል ጀምሯል፡፡ አሰልጣኝ ታዬ ናኒቻን በቅርቡ የሾመው ክለቡ አስራ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን የስብስቡ አካል ሲያደርግ ስድስት በክለቡ የነበሩ ተጫዋቾችን ውል ደግሞ ለተጨማሪ ዓመት አድሶ በሰበታ ስታዲየም ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡

ይስሀቅ መኩሪያ የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የፋሲል ከነማ ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና ድሬዳዋ ከተማ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የተጠናቀቀውን ዓመት በንግድ ባንክ ካሳለፈ በኋላ ቀጣዩ መዳረሻው ሰበታ ሆኗል፡፡ ናትናኤል ጋንቹላ ወደ ቀድሞው ክለቡ ተመልሷል። በፋሲል ከነማ እና ሰበታ ከተማ ከዚህ በፊት በመስመር አጥቂነት ሚና የምናውቀው ተጫዋቹ ያለፈውን ዓመት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ቆይቶ ወደ ቀድሞው ክለቡ ዳግም ተመልሷል፡፡

ኪዳኔ አሰፋ አራተኛው የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ነው፡፡ በስሑል ሽረ ፣ ዲላ ከተማ ፣ ሀላባ እና ሀምበሪቾ የተጠናቀቀውን ዓመት አማካዩ በሀምበርቾ አሳልፎ ሰበታን ተቀላቅሏል፡፡ ኤፍሬም ቀሬ ሌላኛው አዲሱ ተጫዋች ነው፡፡ ከሙገር ሲሚንቶ የተገኘው እና በአክሱም ከተማ ኢትዮጵያ መድን ሲጫወት የምናውቀውን አጥቂ ጨምሮ ኢብሳ አበበ ግብ ጠባቂ ከቡራዩ ፣ ሚሊዮን ሰለሞን ግብ ጠባቂ ከየካ ፣ ታመነ ቅባቱ ተከላካይ ከቡራዩ ፣ ሰላሙ አለፈ አማካይ ከለገጣፎ ፣ ብሩክ ግርማ አማካይ ከአዲስ አበባ ፣ ምትኩ ጌታቸው አጥቂ ከነገሌ አርሲ ፣ ዮናስ ሰለሞን አማካይ ከሀምበሪቾ ፣ ፣ መታሰቢያ ገዛኸኝ ተከላካይ ከለገጣፎ ፣ በረከት ግዛው አማካይ ከጅማ አባቡና ፣ ዮሐንስ አድማሴ ተከላካይ ከየካ አዲሶቹ ናቸው፡፡

ክለቡ ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ ገዛኸኝ ባልጉዳ አጥቂ ፣ አለምለንተ ካሳ አማካይ ፣ ዮናስ አቡሌ አማካይ ፣ ጌታሁን ዳዲ ተከላካይ ፣ አስቻለው እና ሀምዛ የተባሉ ተጫዋቾችን ውልም አራዝሟል፡፡