ወላይታ ድቻ መቻልን በቃልኪዳን ዘላለም ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ጎል በማሸነፍ የዓመቱ የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥቡን አሳክቷል፡፡
መቻሎች በኢትዮጵያ መድን ከተረቱበት ጨዋታቸው በሦስት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ አድርገዋል፡፡ አህመድ ረሺድ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና እስራኤል እሸቱ ወጥተው ዳዊት ማሞ ፣ ግርማ ዲሳሳ እና ምንይሉ ወንድሙ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል፡፡ ከሀድያ ሆሳዕናው ጨዋታ አንፃር ወላይታ ድቻዎች በጉዳት በሌለው ስንታየው መንግሥቱ ምትክ ሀብታሙ ንጉሴን ብቸኛው ቅያሪያቸው አድርገው ቀርበዋል፡፡
10 ሰዓት ሲል የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አርባ አምስት የጨዋታ ጊዜ አሰልቺ ይዘትን የተላበሰ ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር፡፡ ወጥነት የጎደላቸው ቅብብሎች ተበራክተው በታዩበት አጋማሽ መቻሎች የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው በመውሰድ በቀኝ በኩል ወደ ተሰለፈው በረከት ደስታ በማድላት ለመጫወት ቢጥሩም የመጨረሻው ውሳኔያቸው ደካማ በመሆኑ እንደያዙት የቁጥጥር ድርሻ የጠራ አጋጣሚን ለመፍጠር አልታደሉም፡፡ በመከላከል የጨዋታ መንገድ የሚታወቁት ድቻዎች በበኩላቸው ይህንኑ የአጨዋወት መንገድ ቀጥለው ነገር ግን ኳስን በሚያገኙበት ወቅት በተሻጋሪ ረጃጅም ኳስ ወደ አጥቂ ክፍሉ በማሻገር ለመጫወት በተወሰነ መልኩ ሲጥሩ ታይተዋል፡፡
ጥራት ባለው መልኩ በማጥቃት የጠሩ ዕድሎችን ለመፍጠር የሰነፉት ሁለቱ ቡድኖች እንዳሳዩት የሜዳ ቆይታቸው ሁሉ የግብ ዕድልንም ለመፍጠር የነበራቸው ትጋት ደካማ በመሆኑ ሙከራን ለመመልከት ሰላሳ ደቂቃዎችን እንድንጠብቅ አስገድዶናል፡፡ በዚህም ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል የመቻል የግብ ክልል የደረሱት ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻም ንጋቱ ገብረስላሴ እግር ስር የደረሰችን ኳስ ተጫዋቹ ወደ ሳጥን ይዞ ለመግባት ሲሞክር ተከላካዩ የአብስራ ሙሉጌታ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ቃልኪዳን ዘላለም በዳግም ተፈራ መረብ ላይ አሳርፎ ቡድኑን ወደ መሪነት አሸጋግሯል፡፡
ከጎሉ መቆጠር በኋላ የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኙ መቻል በተለይ መሀል ሜዳው ላይ ከከነዐን ማርክነህ እና ፍፁም ዓለሙ በሚነሱ እና በሁለቱ የመስመር ቦታዎች በግርማ እና በረከት አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ትጋት ማድረግን ቢጀምሩም የጦና ንቦቹን የመከላከል አደረጃጀት ሰብሮ ለመግባት ባለመቻላቸው አጋማሹ እንደነበረው የሙከራ ድክመት ታግዞ በ1-0 ተገባዷል፡፡
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ መቻሎች በቶሎ ጎል ለማግኘት የአጥቂ ተጫዋቹ እስራኤል እሸቱን በማስገባት ግርማ ዲሳሳን ሲያስወጡ ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው ንጋቱ ገብረስላሴ ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ በመሳይ ኒኮል ሊተኩ ተገደዋል፡፡ አጋማሹ የመቻል የእንቅስቃሴ የበላይነት እና የወላይታ ድቻ በተቃራኒው የጥብቅ መከላከል አጨዋወትን ያየንበት ነበር፡፡ ተቀይሮ የገባውን እስራኤል እሸቱን ፍጥነት ለመጠቀም በተደጋጋሚ ቢሞክሩም የድቻን የግብ ክልል በቀላሉ ማስከፈት አልቻሉም።
ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በኃይሉ ተሻገርን ከአማካይ ክፍሉ አስወጥተው በመከላከል አመዝኖ የሚጫወተውን ዮናታን ኤልያስን ቀይረው በማስገባት ከመከላከሉ በዘለለ የመቻልን ስህተት እየጠበቁ በሚያገኙት አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም የጠራ አጋጣሚን መፍጠር ግን የሚያስችላቸው አልነበረም፡፡
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ የድቻው ግብ ጠባቂ ቢኒያም ገነቱ ‘ሰዓት ለመግደል ሆን ብለህ ወድቀሀል’ በሚል የዕለቱ ዳኛ አባይነህ ሙላት በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ በምትኩም ተቀይሮ ገብቶ የነበረው ፍቃዱ መኮንን ወጥቶ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ የገባ ሲሆን ጨዋታው በቀሩት ደቂቃዎች ግብ ሳያስተናግድ በወላይታ ድቻ 1-0 ድል አድራጊነት ተጠናቋል፡፡
ሽንፈት የገጠመው መቻል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጨዋታውን እንደጠበቁት ማግኘታቸውን ከተናገሩ በኋላ ተጋጣሚያቸው የሚመጣበትን መንገድ አውቀው ለመስበር አስበው ለጨዋታው ቢቀርቡም ባሰቡት ልክ ማድረግ አለመቻላቸውን ገልፀው ከመሀል ክፍል ለአጥቂ በአግባቡ ኳስ አለመድረሱ ጎል እንዳያገኙ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል፡፡ የመጀመሪያውን ሙሉ ነጥብ ያገኙት የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው ስሜታዊነት የበዛበት ጨዋታ እንደነበር ጠቁመው ጨዋታው ማራኪ ባይሆንም ወደ ማሸነፍ ለመምጣት ቡድናቸው ተርቦ ስለነበር ወሳኝ ነጥብን ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው እና ድሬዳዋ ተገኝተው የደገፏቸውን ደጋፊዎች እንዲሁም ደግሞ የክለቡ አመራሮች ለዚህ ውጤት መሳካት ላደረጉት ሁሉ አመስግነዋል፡፡