ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ ወደ ድል ተመልሷል

ምሽት ላይ በተደረገው የስድስተኛ ሳምንት አራተኛ ጨዋታ ሠራተኞቹ በጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-1 መርታት ችለዋል።

ምሽት 1፡00 ላይ የወልቂጤ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ሲደረግ ሠራተኞቹ በአምስተኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና 1-0 በተረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ጀማል ጣሰው ፣ ፍፁም ግርማ እና ጌታነህ ከበደ በሮበርት ኦዶንካራ ፣ ብርሃኑ ቦጋለ እና ተመስገን በጅሮንድ ተተክተው ጀምረዋል። ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው በአምስተኛው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር 2-2 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ አንዳርጋቸው ይላቅን ጉዳት ላይ በሚገኘው ተስፋዬ በቀለ ቦታ ተክተው ጀምረዋል።

መጠነኛ የኳስ ቁጥጥር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል ሠራተኞቹ ፍጹም የበላይ የነበሩ ሲሆን በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ምንም ዓይነት የግብ ሙከራ ያልተደረገበት ነበር። 3ኛው ደቂቃ ላይ ጀማል ጣሰው ሲጀምር ያሻማውን ኳስ ያገኘው አቡበከር ሳኒ ለጌታነህ ከበደ ሲያቀብል ኳሱን አቋርጦ ያገኘው አንዳርጋቸው ይላቅ ለማራቅ ሲሞክር ተደርቦ መመለስ የቻለው ጌታነህ ከበደ ወደግብ የሞከረው ኳስ የግራውን ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል።

ከኳስ ውጪ በተለይም የአማካይ ስፍራ ላይ ድንቅ እንቅስቃሴ የነበራቸው እና በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት ሠራተኞቹ 21ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። የኋላሸት ሰለሞን ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ግብ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው እና ነፃ ሆኖ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል።

በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ጌታነህ ከበደ በአንድ ንክኪ በግንባሩ ያቀበለውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ ሆኖ ያገኘው የኋላሸት ሰለሞን በጥሩ ሁኔታ ኳሱን መቆጣጠር ቢችልም ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ መልሶበታል በዚህም ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል።

ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ኳሱን እግራቸው ስር ለማቆየት እጅግ ሲቸገሩ ታይተዋል። 43ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ሳሙኤል አስፈሪ ሲያሻማ ያገኘው ዋሃብ አዳምስ በግንባሩ በመግጨት ለአቡበከር ሳኒ ሲያቀብል አቡበከር ያደረገውን ሙከራም ተከላካዮች ተደርበው አስወጥተውታል።

ከዕረፍት መልስ ሠራተኞቹ ከኳስ ውጪ እንደቡድን የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሲያስቀጥሉ ኢትዮ ኤሌክትሪኮችም ከመጀመሪያው አጋማሽ በመጠኑም ቢሆን ተሻሽለው መቅረብ ችለዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ወደቀኙ የሜዳ ክፍል ካመዘነ ቦታ ላይ ስንታየሁ ዋለጬ የኋላሸት ሰለሞን ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ የሠራተኞቹን መሪነት ማጠናከር ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ የተሻለ ወደፊት ተጠግተው የተጫወቱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረጉት 66ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ጌቱ ኃይለማርያም በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት ያሻማው ኳስ ማንም ሳይነካው ነጥሮ ግብ ለመሆን ተቃርቦ የነበረ ሲሆን ጀማል ጣሰው በላይኛው አግዳሚ ወደማዕዘን ሊያስወጣው ችሏል።

ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ሠራተኞቹ ወደኋላ ተጠግተው ጨዋታውን ለማረጋጋት ሲጥሩ ባልተደራጀ መልኩ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የሚደርሱት ኤሌክትሪኮች በፀጋ ደርቤ እና ሙሴ ከበላ የተወሰኑ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም የመጨረሻ ኳሳቸው ፍጹም ደካማ ነበር። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የባከኑ ደቂቃዎች ሲቀሩ አድናን ፈይሠል አቤል ነጋሽን ከግብጠባቂ ጋር ያገናኘ ኳስ አመቻችቶ ቢያቀብልም አቤል ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ዘሪሁን ታደለ የኳሱ ኃይል – የለሽነት ተጨምሮበት በጥሩ ቅልጥፍና ይዞታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩ ኢብራሂም ከድር ከቅጣት ምት የሞከረው ኳስ የላይኛውን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ ያገኘው ታፈሰ ሰርካ በግንባሩ በመግጨት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ለባዶ ከመሸነፍ ያዳነች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውም በወልቂጤ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በጨዋታው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ እንደነበሩ እና በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ጥሩ እንደነበሩ ገልፀው ካለፈው ጨዋታ በኋላ የነበረው የ 10 ቀናት ልዩነት እንዲዘናጉ ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል።

ወደ ድል የተመለሱት ወልቂጤ ከተማዎች አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው ጨዋታው ባሰቡት መንገድ መሄዱን ጠቁመው ጌታነህ ከበደን ከጠበቁት በላይ እንዳገኙት እና ውጤት ይዘው እንዲወጡ ስላደረጋቸውም ሲያመሰግኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው የግራ ተከላካዩ ፍፁም ግርማም ጥሩ እንደነበር እና ወደፊትም የተሻለ ያሳየናል ብለው እንደሚያምኑ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ያጋሩ