በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዩጋንዳን 1-0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው አምርቷል።
ሱዳን ላይ እየተደረገ ባለው የሴካፋ ዞን ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ከዩጋንዳ ጋር ሲያደርግ አሰልጣኝ ዕድሉ ደረጄ ከመጀመሪያው የታንዛኒያ ጨዋታ አንፃር በአሰላለፋቸው ላይ ባደረጉት ለውጥ ቡጣቃ ሸመና ፣ ከድር ዓሊ እና አማኑኤል አድማሱ በዮሴፍ ታረቀኝ ፣ ተገኑ ተሾመ እና ይታገሱ ታሪኩ ምትክ በመጀመሪያው አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል።
በጨዋታው በከድር ዓሊ እና ዘላለም አባቴ ሙከራዎች የዩጋንዳውን ግብ ጠባቂ በመፈተን የተነቃቃ አጀማመር ያደረጉት ኢትዮጵያዊያኑ በጀመሩበት አኳኋን ብልጫ ወስደው መቀጠል ባይችሉም የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ችለዋል።
በተመጣጠነ እንቅስቃሴ በቀጠለው ጨዋታ የአሰልታኝ ዕድሉ ደረጄ ቡድን በአማኑኤል አድማሱ አማካይነት ኳስ እና መረብን ቢያገናኝም በጎሉ ሂደት ላይ ጥፋት በመሰራቱ ሳይፀድቅ ቀርቷል። በአንፃሩ ታንዛኒያን 2-0 በመርታት ለዚህ ጨዋታ የደረሱት ዩጋንዳዊያኑ የተሻለውን የኳስ ቁጥጥር ይዘው ቢዘልቁም የጠራ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ቀዳሚውን አጋማሽ አገባደዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ 60ኛው ደቂቃ ላይ በታንዛኒያው ጨዋታ ግብ አስቆጥሮ የነበረው ከድር ዓሊ ዛሬም ዋሳኟን ጎል አስመዝግቧል። ቡድኑ በቀኝ መስመር በከፈተው ጥቃት ከድር የግብ ጠባቂውን የአቋቃም ስህተት ተመልክቶ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ መትቶ ያስቆጠራት ይህች ግብ ኢትዮጵያ ምድቧን የበላይ ሆና እንድታጠናቅቅ ምክንያት ሆናለች።
ዩጋንዳዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው ቢጫወቱም 85ኛው ደቂቃ ላይ በቁጥር በርክተው ሳጥን ውስጥ ከደረሱበት እና አባሴ ኬዩኒ ራሱ ተደርቦ ባወጣው ኳስ ለግብ ከመቅረባቸው ውጪ ያሰቡትን ሳያሳኩ ጨዋታው በኢትዮጵያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።