መረጃዎች | 24ኛ የጨዋታ ቀን

ስድስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር ነገም በሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልክ ቀርበዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

በተለያየ የጨዋታ መጠን በእኩል ሰባት ነጥቦች በሰንጠረዡ ወገብ አካባቢ የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው የነገ 10 ሰዓቱ መርሃግብር ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መንገድ በሚቀርቡ ሁለት ቡድኖች መካከል የተሻለ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ባስመዘገቧቸው አራት ነጥቦች ታግዘው ውጥረቶችን ማለዘብ የቻሉት ሀዋሳዎች በ7 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ሀዋሳ ከተማዎች በሰንጠረዡ ከወገብ በላይ የሚገኙ ቡድኖችን ሲገጥሙ በብዛት እንደሚያደርጉት በነገውም ጨዋታም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ይቀርባሉ ተብለው ይጠበቃሉ።

በሊጉ ከወላይታ ድቻ ቀጥሎ በአማካይ 44% የኳስ ቁጥጥር ድርሻ 15ኛ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከሀዲያ ሆሳዕናም ቀጥሎ 87 ጥፋቶችን በመፈፀም ሁለተኛው ከፍተኛ የጥፋት(Foul) መጠን ያስመዘገበው ቡድኑ መሆኑ ሀዋሳ በአሉታዊ መከላከል (reactive defending) የመጫወት ዝንባሌ ያለው ስለመሆኑ የሚያስረዳ ሲሆን በነገውም ጨዋታ ወደ ራሳቸው ሜዳ ተስበው በጥልቀት በመከላከል በሚገኙ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ሊጫወቱ እንደሚችሉ ይገመታል። በመልሶ ማጥቃት ወቅትም ቡድኑ የሙጂብ ቃሲም እና ዓሊ ሱሌይማንን ጥሩ የጨዋታ ቀን ማሳለፍን ይጠባበቃሉ።

ከአህጉራዊ ውድድሮች መልስ ዳግም ፊታቸውን ወደ ሊጉ የመለሱት ፋሲል ከነማዎች በተከታታይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማን ከገጠሙባቸው ሁለት ፈታኝ መርሃግብሮች አራት ነጥብ ሰብስበው ወደ ነገው ጨዋታ የሚያመሩ ይሆናል። እርግጥ ከጊዮርጊሱ ጨዋታ አንፃር በተወሰነ መልኩ በባህር ዳሩ ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ ሆነው የታዩት ፋሲል ከነማዎች በነገው ጨዋታም ውጤት ይዘው ለመውጣት እንደ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ከፍ ባለ ፍላጎት መጫወት ይጠበቅባቸዋል።

ምንም እንኳን እስካሁን በሊጉ አራት ጨዋታዎችን ያደረጉት ፋሲሎች የማጥቃት ጨዋታቸው ግን ብዙ መሻሻሎችን ይሻል። በሊጉ እስካሁን ሦስት ግቦችን ያስቆጠረው ቡድኑ ጥቅል እድሎችን ሆነ ዒላማቸውን በጠበቁ ሙከራዎች ረገድ በአራቱ ጨዋታ የነበረው አፈፃፀም በሚጠበቀው ልክ አይደለም። በክረምቱ በርከት ያሉ ተቀዳሚ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹን ያጣው ቡድኑ አሁን ላይ እየተጠቀመባቸው ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል በተለይ ፍቃዱ ዓለሙ እና ሀብታሙ ገዛኸኝን ይበልጥ የሚሻሻሉበትን መንገድ መፈለግ የግድ ይላቸዋል።

በነገው ጨዋታ በሃዋሳ ከተማ በኩል ከፋሲል ከነማ ያለፉት ዓመታት ስኬት በስተጀርባ ትልቅ አበርክቶ የነበራቸው አጥቂው ሙጂብ ቃሲም እና ሁለገቡ ተከላካይ ሰዒድ ሀሰን በነገው ጨዋታ በሃዋሳ ከተማ መለያ ታሪክ የሰሩበትን ፋሲልን በተቃራኒ የመግጠማቸው ጉዳይ ጨዋታውን ለሁለቱ ተጫዋቾች ይበልጥ ታሪካዊ ያደርግላቸዋል።

በሀዋሳ ከተማዎች በኩል በነገውን ጨዋታ ወንድማገኝ ኃይሉ በግል ጉዳይ የማይኖር ሲሆን አዲሱ አቱላም በጉዳት ምክንያት የመሰለፉ ነገር አጠራጥሯል። በአንፃሩ ዐፄዎቹ ባለፉት ጨዋታዎች ያልነበሩት ሃብታሙ ተከስተ እና ሱራፌል ዳኛቸው አሁንም ከነገው የጨዋታ ዕለት ስብስብ ውጪ መሆናቸው ተረጋግጧል።

ከዚህ ቀደም በአስር አጋጣሚዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች እኩል ሦስት ጊዜ ሲሸናነፉ የተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተቋጭተዋል። አስር ሰዓት ሲል የሚጀምረውን ይህን ጨዋታ አዳነ ወርቁ በዋና ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አርባምንጭ ከተማ

ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሪነታቸውን ለማስቀጠል እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ በሰንጠረዡ ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት የነገ ምሽቱ ጨዋታ ይጠበቃል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት ፍፁም የሆነ የበላይነት ቢኖረውም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀደመው ዘመን የአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የፉክክር ታሪክ ጋር በማያያዝ የተሻለ ፉክክር መንፈስ የሚታይበት ጨዋታ እንደሆነ እያስተዋልን እንገኛለን።

የውድድር ዘመኑን በአስደናቂ የማሸነፍ ግስጋሴ የጀመሩት ፈረሰኞቹ በ5ኛ የጨዋታ ሳምንት ግን በጠንካራው ፋሲል ከነማ የመጀመሪያ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል። አሁንም ቢሆን በ12 ነጥቦች በግቦች ልቀው ሊጉን እየመሩ የሚገኙ ሲሆን በፍጥነት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከአርባምንጩ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ስለማሳካት ያልማሉ።

በአውንታዊ የቡድን መለኪያዎች የተሻሉ ቁጥሮች ባለቤት የሆነው ቡድኑ በተለይ መሀል ክፍል ላይ ሦስት ለግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል የተሻለ ጊዜ እያሳለፈ የነበረውን ዳዊት ተፈራ በጉዳት ማጣታቸውን ተክሎ በተለይ በፋሲሉ ጨዋታ መሀል ክፍል ላይ እንቅስቃሴዎችን ለማደራጀት ተቸግረው የተመለከትን ሲሆን ይህም ቡድኑ ይበልጥ ቀጥተኛ እንዲሆን አስገድዶት ተመልክተናል። ይህን ክፍተት ለመድፈን ከመስመር ተጫዋቾቹ አብዝቶ የሚጠብቀው ቡድኑ በነገው ጨዋታ በሁለቱ መስመሮች ጥቃቶችን ሊሰነዝር እንደሚችል ይገመታል።

በአንፃሩ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ በአራት ነጥቦች በሰንጠረዡ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አዞዎቹ በመጨረሻ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና ካስተናገዱት ሽንፈት ማግስት ከጠንካራው ቅዱስ ጊዮርጊስ አውንታዊ ውጤት ይዘው ለመውጣት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተከታታይ ጠንካራ ጨዋታዎች የሚጠብቁት ቡድኑ አሁንም የወጥነት ችግር አብሮት እየዘለቀ ይገኛል በነገውም ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው ጥራት አንፃር ሊያገኟቸው የሚችሏቸውን ዕድሎች በመጠቀም ሆነ በመከላከሉ ረገድም እንከን የለሽ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

ኤሪክ ካፓይቶን ከጉዳት መልስ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ በመጨረሻው ጨዋታ ለ60 ደቂቃዎች የተጠቀሙት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የተጫዋቹ መመለስ የቡድኑን የራስ መተማመን ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ለቡድኑ ሰባት ግቦችን በማስቆጠር የቡድኑ ከፍተኛ አስቆጣሪ የነበረው ኤሪክ ካፓይቶ ቡድኑን ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በነገው ጨዋታ የቁርጭምጭሚት ጉዳት ላይ ከሚገኘውን ዳዊት ተፈራ እና በጡንቻ መሰንጠቅ ለተጨማሪ አንድ ወር ከሜዳ እንደሚርቅ ከሚጠበቀው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ተመስገን ዮሐንስ ውጭ የተቀረው ስብስብ በሙሉ ጤንነት ድሬዳዋ ስለመድረሱ የሰማን ሲሆን በአንፃሩ ተጋጣሚያቸው አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በሙሉ ስብስብ የነገውን ጨዋታ ያደርጋል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በ16 አጋጣሚዎች እርስ በእርስ የተፋለሙ ሲሆን በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አርባምንጭ ከተማ በአንፃሩ 2 ጊዜ ሲያሸንፍ የተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል። ይህንን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ እንደምትመራው ይጠበቃል።