በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ኃይቆቹ በሙጂብ ቃሲም እና ኤፍሬም አሻሞ ጎሎች ዐፄዎቹን 2-0 መርታት ችለዋል።
10፡00 ላይ የሀዋሳ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ ሲደረግ ኃይቆቹ በአምስተኛው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 2-2 ከተለያዩበት ጨዋታ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ መሐመድ ሙንታሪ ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣ ዳዊት ታደሠ እና መድኃኔ ብርሃኔ በአላዛር ማርቆስ ፣ ላውረንስ ላርቴ ፣ አቤኔዘር ኦቴ እና ወንድማገኝ ኃይሉ ተተክተው ጀምረዋል። ዐፄዎቹ በበኩላቸው በአምስተኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን በታፈሰ ሰለሞን ብቸኛ ግብ 1-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም መናፍ ዐወል ፣ በዛብህ መለዮ እና ጉልላት ተሾመ በይሁን እንደሻው ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ፍቃዱ ዓለሙ ተተክተው ጀምረዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ እና የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል ፋሲሎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በሀዋሳዎች ተደርጓል። 14ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ሳሙኤል ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ሚኬል ሳማኪ ወደማዕዘን አስወጥቶታል። እንዳሳዩት እንቅስቃሴ ግብ ማስቆጠር የነበረባቸው አፄዎቹ የተሻለውን የመጀመሪያ ሙከራ 21ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ሽመክት ጉግሣ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ታፈሰ ሰለሞን በድንቅ ሁኔታ ኳሱን ተቆጣጥሮ ተከላካዮችን በረከት ሳሙኤልን እና መድኃኔ ብርሃኔን አታሎ ማለፍ ቢችልም ያደረገው ሙከራ ግን ዒላማውን ባለመጠበቁ የግቡን የቀኙ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ይሄም ፋሲሎችን ያስቆጨ ትልቁ አጋጣሚ ነበር።
በሰከንዶች ልዩነት ከግብ ጠባቂው በጀመሩት ኳስ የመልሶ ማጥቃት ያደረጉት ኃይቆቹ መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። በዚህም በቃሉ ገነነ ያሻገረለትን ኳስ ከተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ በቀኝ በኩል ሆኖ ያገኘው ሙጅብ ቃሲም ማስቆጠር ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ የተሻለ ወደፊት የተጠጉት ዐፄዎቹ የተለያዩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ 24ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ያገኘው ሽመክት ጉግሳ በግንባሩ አንጥሮ ለማስቆጠር ቢሞክርም ኳሱ ኃይል ስለነበረው ዒላማውን ሳይጠብቅ ሊወጣ ችሏል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት በግራ መስመር ድንቅ ሩጫ ያደረገው ኤፍሬም አሻሞ ያሻማውን ኳስ ሙጅብ ቃሲም በአንድ ንክኪ በግንባሩ ለዓሊ ሱሌይማን ሲያቀብል ዓሊ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኪ በአስደናቂ ፍጥነት ወደ ማዕዘን ሊያስወጣበት ችሏል።
ከዚህ አጋጣሚ በኋላ በኳስ ቁጥጥሩም የግብ ዕድል በመፍጠሩም በኩል ዐፄዎቹ ፍጹም የበላይነቱን ወስደዋል። በጥሩ የኳስ ቅብብል የታጀበ የማጥቃት ሂደት የተከተሉት አፄዎቹ በታፈሰ ሰለሞን እና በበዛብህ መለዩ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም የመጨረሻ ኳሳቸው ደካማ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩ በዛብህ መለዩ ከታፈሰ ሰለሞን የተቀበለውን ኳስ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮበታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ሀዋሳዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደኋላ ጥቅጥቅ ብለው መጫወትን ሲመርጡ ፋሲሎች በበኩላቸው የማጥቂያ ሚዛናቸውን በቀኙ የሜዳ ክፍል ላይ አበርተትተዋል። ጨዋታው ፈታኝ የግብ ሙከራ ሳንመለከትበት ሲቀጥል 79ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልባሲጥ ከማል ያሻገረለትን ኳስ የተቀበለው ኤፍሬም አሻሞ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኪ መውጣት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮ የሀዋሳ ከተማን መሪነት ወደ 2-0 ከፍ ማድረግ ችሏል።
88ኛው ደቂቃ ላይ መድኃኔ ብርሃኔ ተስፋዬ ነጋሽ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ወጥቷል። በባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ አፄዎቹ በአምሳሉ ጥላሁን እና በፍቃዱ ዓለሙ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ውጤታማ መሆን አልቻሉም። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ተጫዋቾቹ ላይ የአቋቋም ስህተት መኖሩንና በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንዳልነበሩ ሲገልፁ የዚህም ምክንያት የከድር ኩሊባሊ የተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ ጥሩ አለመሆን እንደነበር አንስተዋል። በተጨማሪም ጫናዎች ሊመጡ እንደሚችሉ ግን ደግሞ ጠንክረው እየሰሩ እንደሆነ እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ጨዋታውን የረቱት የሀዋሳ ከተማዎች አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ያገኙት ነጥብ ከመሪዎች ላለመራቅ እንደሚያግዛቸው እና ተከላካይ መስመር ላይ የነበሩ ተጫዋቾች ዛሬ ከሌላው ጊዜ የተሻሉ እንደነበሩ ተናግረዋል። ሙጅብ ቃሲም አጥቂ ቦታ ላይ ሲያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ ለድል እንደረዳቸውም ጠቁመዋል።