የ6ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ ቅድመ መረጃዎች እነሆ!

ሲዳማ ቡና ከ አዳማ ከተማ

በነገው ጨዋታ በ5ኛ የጨዋታ ሳምንት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ያገኘው ሲዳማ ቡና ተከታታይ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ሲጥር በተቃራኒው ከሁለት ተከታታይ ድል በኋላ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው አዳማ ከተማ ደግሞ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ይጠበቃል።

ከ2 ሳምንታት በፊት የቀጠራቸውን ሥዩም ከበደ ግልጋሎት በነገው ጨዋታ በሜዳ ላይ የሚያገኘው ሲዳማ ቡና የባህር ዳር ቆይታው በመጥፎነት የሚፈረጅ ቢሆንም በመጨረሻው የወልቂጤ ፍልሚያ ከናፈቀው ድል ጋር ተገናኝቷል። ከምንም በላይ በ4ቱ ጨዋታዎች በድምሩ 12 ግቦችን ያስተናገደው የኋላ ክፍሉ ከተገኘው ሦስት ነጥብ እኩል አንፃራዊ እርጋታ ማሳየቱ እና ቡድናዊም ሆነ ግለሰባዊ ስህተቶችን ቀንሶ መታየቱ ለቡድኑ አባላት ደስታን የሚቸር ነው። ምናልባት ግን የነገ ተጋጣሚው አዳማ በማጥቃቱ ረገድ የተዋጣለት ስለሆነ የመከላከል መዋቅሩን የበለጠ ማጠናከር ይገባዋል።

በአሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመራው አዳማ ከተማ በባህር ዳር በነበረው ቆይታ በአንፃራዊነት ጠንከር ያሉ ተጋጣሚዎችን ተፋልሞ ማግኘት ከሚገባው 15 ነጥቦች ሰባቱን አሳክቷል። ሚዛናዊ የሚመስለው ቡድኑ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ወሳኝ ተከላላዮቹን በጉዳት እና በቤተሰብ ችግር ምክንያት ሲያጣ በመጠኑ የመከላከል መሠረቱ የተናጋበት መስሏል። በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግብ ብቻ አስተናግዶ የነበረ ሲሆን በጠቀስናቸው ሁለት ጨዋታዎች ግን አራት ጊዜ ግቡን አስደፍሯል። ይህ የመከላከል አደረጃጀት ተሻሽሎ የሚቀርብ ካልሆነ ተከታታይ ድል ለማግኘት በሚጥረው ሲዳማ ሊፈተን ይችላል። በተቃራኒው ግን ፈጣኖቹ አጥቂዎች ቡድኑ ከጨዋታው አንዳች ነገር እንዲያገኝ እንደሚያደርጉ ይታሰባል።

ሲዳማ ቡና ከላይ እንደገለፅነው አዲሱ አሠልጣኛቸው ሥዩም የወረቀት ጉዳዮቻቸው በመገባደዳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳ ላይ እንደሚመሯቸው ታውቋል። የቡድኑ አምበል ሳላዲን ሰዒድ ግን አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ተገልጿል። አዳማ ከተማ በበኩሉ ወሳኞቹን ተጫዋቾች ዳዋ ሁቴሳ እና ሚሊዮን ሰለሞን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም።

አዳማ እና ሲዳማ ከዚህ ቀደም 22 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 8 አዳማ ከተማ ደግሞ 5 ጊዜ ያሸነፉ ሲሆን ቀሪዎቹን 9 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በሀያ አንዱ ጨዋታዎች ሲዳማ 19 አዳማ 18 ጎሎችን አስመዝግበዋል።

ይህንን ጨዋታ አባይነህ ሙላት በዋና ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ በመገኘት ካለፉት አራት የሊጉ ጨዋታዎች 10 ነጥቦችን የሰበሰበው ሀዲያ ሆሳዕና እና ካለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በማግኘት አሉታዊ የውጤት ጉዞ ላይ የሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ የሚያደርጉት የምሽት 1 ሰዓት ጨዋታ የ6ኛ ሳምንት የማሳረጊያ መርሐ-ግብር ነው።

የውድድር ዓመቱን በሽንፈት የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ወዲያው በማገገም በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥቦችን ይዘው በላይኛው የደረጃ ሰንጠረዥ ፉክክር ራሳቸውን አስገብተዋል። ከኳስ ጋር ፈጣን እንቅስቃሴ የሚያደርገው ቡድኑ በተለይ ሽግግሮች ላይ ያለው አፈፃፀም የተሻለ መሆኑ የስኬቱ ተጠቃሽ ምክንያት ነው። በተለይ ፈጣኖቹን የወገብ በላይ ተጫዋቾች የሚያገኙትን ኳስ በቶሎ የተጋጣሚ ተጫዋቾች ሳይደራጁ ለመጠቀም የሚጥሩበት መንገድ መልካም የሚባል ነው። ከዚህ ባለፈም የማጥቃት አጨዋወቱ ግለሰቦች ላይ ጥገኛ አለመሆኑ እና ከየአቅጣጫው ግቦችን ማግኘቱ ተገማች እንዳይሆን አድርጎታል። ነገም በመከላከል ወቅት ክፍተቶችን ለሚሰጡት ለገጣፎዎች ከባድ የቤት ስራን እንደሚሰጥ መገመት ይቻላል።

አዲስ አዳጊው ለገጣፎ ለገዳዲ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ጨዋታ በአስገራሚ ሁኔታ በማሸነፍ የታሪኩን የመጀመሪያ ተሳትፎ በጥሩ ጅማሮ ቢከፍትም በቀጣዮቹ ጨዋታዎች በውጤትም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ እየወረደ መጥቷል። ካርሎስ ዳምጠው ላይ የተንጠለጠለው የማጥቃት አጨዋወቱም ሌሎች አማራጮች የሌሉት እና ለተጋጣሚ ተገማች እንዲሆን አድርጎታል። በመከላከሉም ሚዛኑን እያጣ የሚገኝ ሲሆን በአማካይ ከሁለት በላይ ግቦችንም እያስተናገደ ይገኛል። ነገም በዚሁ ብቃቱ የሚገኝ ከሆነ በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች የተሻሉ በሆኑት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ሊቀጣ ይችላል። ይህ ቢሆንም ግን እንደተለመደው ግዙፉን አጥቂ ካርሎስ ያማከሉ ረጃጅም ኳሶች በመጠቀም ከውጤት ጋር ለመታረቅ እንደሚጥር ይታሰባል።

ሀዲያ ሆሳዕና በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን ለገጣፎ ለገዳዲ ግን ዮናስ በርታን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ አድርጓል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ የሚገናኙትን ሁለቱን ቡድኖች ተስፋዬ ግሩሙ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

ያጋሩ