ከፍተኛ ሊግ | ሻሸመኔ ከተማ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል

በአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ የሚመራው ሻሸመኔ ከተማ የአስራ ሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቆ ወደ ዝግጅት ገብቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዘግ ያለ የተሳትፎ ቆይታ ያለው ሻሸመኔ ከተማ በሊጉ ላይ የዘንድሮው ተሳታፊነቱን በጠንካራ አቅም ተገንብቶ ለመቅረብ ከቀናት በፊት አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠረ ሲሆን አሁን ደግሞ ከተለያዩ ክለቦች በቀጥታ እና በምልመላ አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

አዲስዓለም ደበበ የክለቡ የመጀመሪያ ፈራሚ ነው፡፡ የቀድሞው የሲዳማ ቡና ፣ ደቡብ ፓሊስ እና ሀምበሪቾ አማካይ ወደ ቀድሞ ክለቡ ሻሸመኔ የተመለሰ ተጫዋች ሲሆን የቀድሞው የወልድያ ፣ ደሴ እና አርባምንጭ አጥቂ በድሩ ኑርሁሴንን ጨምሮ ሳምሶን ተሾመ አማካይ ፣ ቴዲ አጋ አማካይ ፣ ዮናስ ባቤና አጥቂ ፣ ሔኖክ አስጨናቂ ግብ ጠባቂ እና አብዱርቃድር ናስር ተከላካይ ከአቃቂ እንዲሁም ጌትነት ታፈሰ ተከላካይ እና ጌትነት ተስፋዬ አማካይ ከመድን ፣ ታምራት ዳኜ ግብ ጠባቂ ከጅማ አባጅፋር ፣ ያዕቆብ ማሞ አጥቂ ከገጣፎ እና አሻግሬ ኪባሞ ተከላካይ ከሆለታ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ከአዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ የነባሮች ውልም ስለ መራዘሙ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡