ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል

ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን በይገዙ ቦጋለ ግቦች 2ለ0 በማሸነፍ የዓመቱ ሁለተኛ ድሉን አሳክቷል።

ሲዳማ ቡና የዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን በወልቂጤ ላይ ሲያስመዘግብ ከተጠቀመበት አሰላለፍ አቤል እንዳለን በሙሉቀን አዲሱ ብቻ መተካት ሲችል ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር አቻ የተለያየው አዳማ ከተማ በአንፃሩ ዳንኤል ደምሱ እና ዳዋ ሆቴሳን በአዲሱ ተስፋዬ እና አሜ መሀመድ ለውጧል፡፡

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተመጣጠነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን የተላበሰ ይመስል የነበረ ቢሆንም ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ግን የአዳማ ከተማ የወጥነት ችግሮች እየበረቱ በመምጣቱ ሲዳማ ቡናዎች መሀል ሜዳው ላይ ኳስን በመያዝ አጥቂው ይገዙ ቦጋለን የትኩረት ማዕከል አድርገው ጥቃቶችን ለመሰንዘር ብርቱ ትጋቶችን ማድረግን ጀምረዋል፡፡ በዚህም መሀል ክፍሉ ላይ የሙሉቀን እና የፍሬው ሰለሞንን ጥምረት የተጠቀሙበት መንገድ ፍሬ አስገኝቶላቸዋል፡፡ በዚህም 9ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች ከኋላ ክፍላቸው ኳስን መስርተው ለመውጣት በሚሞክሩበት ወቅት ደስታ ዮሃንስ ስህተት በመስራቱ ፍሬው ሰለሞን በብልጠት ኳሷን በመንጠቅ ነፃ አቋቋም ለነበረው ይገዙ ሰጥቶት አጥቂው ወደ ጎል ለውጧት ሲዳማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ የተገደበ እንቅስቃሴን ሲያደርጉ መታየት ቢችልም ጎል ካስተናገዱ በኋላ በይበልጥ ከመሱዑድ መሀመድ እግር ስር በሚነሱ እና ወደ መስመር ተጥለው በሚሻገሩ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር የጣሩት አዳማዎች ተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያሳዩም የሲዳማ የግብ ክልል ሲደርሱ ግን ፍፁም ስልነት ይጎላቸው ነበር።

28ኛው ደቂቃ ላይ በቅብብል ፍሬው ሰለሞን የደረሰችውን ኳስ ሁለት የአዳማ ተጫዋቾችን በማለፍ በድጋሚ ይገዙ ነፃ ቦታ መሆኑን ተመልክቶ ሲሰጠው አጥቂው በጥሩ አጨራረስ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል፡፡ በሚሰሯቸው የመከላከል ስህተት ሁለት ጎሎች ከመረባቸው ያረፈባቸው አዳማዎች ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት በመስመሮች በኩል በተለይ አሜ እና ዊሊያምን ተጠቅመው ጎል ለማግኘት ጥረትን ጀምረዋል፡፡ ከማዕዘን ምት 31ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሃንስ ያሻገረውን ኳስ ዊሊያም ሰለሞን በቀጥታ ሲመታ ፊሊፕ ኦቮኖ በድንቅ ሁኔታ አውጥቷል፡፡ በሌላ ሙከራ አዳማዎች በተመሳሳይ ከማዕዘን የተሻገረን ኳስ አሜ ተቀልብሶ ሞክሮ ወደ ውጪ የተወጣችበት አጋጣሚ ሌላኛዋ በጨዋታው የፈጠሩት ዕድል ነበረች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች ሲዳማዎች አማኑኤል እና መሀሪን ወደ ማጥቃቱ በማሳተፍ ተጨማሪ ጎልን ለማግኘት የጣሩበት የነበረ ቢሆንም በ2ለ0 ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል ጨዋታው አምርቷል፡፡

ከዕረፍት ጨዋታው ሲቀጥል አዳማ ከተማዎች በቀዳሚው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩ ሁለት ተጫዋቾች ለውጠዋል፡፡ አብዲሳ ጀማል እና ፍሪድሪድ ሀንሳ አስወጥተው ቢኒያም አይተን እና አድናን ረሻድን ወደ ሜዳ በማስገባት የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን መረከብ ቢችሉም ኳስ ሲይዙ ጫና ውስጥ ይገቡ ስለነበር በቀላሉ የሚያገኟቸውን ዕድሎችን ወደ ጎልነት ለመለወጥ ፍፁም ተቸግረው ተስተውሏል፡፡ በግራ አቅጣጫ ሲዳማዎችን አስከፍቶ ግብ ለማግኘት ወደ ዊሊያም ሰለሞን በይበልጥ ተስበው የማጥቂያ መንገዳቸው አድርገው የተንቀሳቀሱት አዳማዎች 52ኛው ደቂቃ ላይ ዊሊያም ሰለሞን በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ውስጥ ያሻገረውን አሜ መሀመድ በግንባር ገጭቶ ኢኳቶሪያል ጊኒያዊው ግብ ጠባቂ ፊሊፕ ኦቮኖ ባወጣበት አጋጣሚ ወደ ግብ መድረስ ችለዋል፡፡ ፈጠን ያለ እና ለዕይታ ሳቢ የሆኑ እንቅስቃሴዎች በተበራከቱበት ሁለተኛው አጋማሽ ቶሎ ቶሎ ኳሶች ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ደርሰው መመልከት ብንችልም ኳስን ከመረብ ጋር የሚያገናኝ ሁነኛ ተጫዋችን አጋማሹ አላገኘም፡፡

አዳማዎች ኳስን በሚይዙበት ወቅት ጥቅጥቅ ብለው ለመንጠቅ በተደጋጋሚ ስጋት ሲሆኑ የታዩት ሲዳማዎች በዚህ የጨዋታ መንገዳቸው 67ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ አግኝቶ አስቆጠረው ሲባል በቀላሉ ክዋሜ ባህ የያዘበት አጋጣሚ ለሦስተኛ ጎል የተቃረቡበት ነበር፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች አዳማዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ በማስገባት ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ሌላ ተጨማሪ አማራጭን ወስደዋል፡፡ 82ኛ ደቂቃ ላይ ዊሊያም ሰለሞን በጥሩ የዕይታ ብቃት በሲዳማ ተከላካዮች መሀል ያሾለከለትን ኳስ ተቀይሮ የገባው ቦና ዓሊ ከግቡ ትይዩ አግኝቶት በቀጥታ መቶ ወደ ጎልነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ ኦቮኖን አሳቅፎታል፡፡ አዳማ ከተማዎች በተሻለ እንቅስቃሴ ጎልን ለማግኘት በተደጋጋሚ በሲዳማ ቡና የግብ ክልል ሲያንዣብቡ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ መታየት ቢችሉም ከዕረፍት በፊት በይገዙ ቦጋለ አማካኝነት ሁለት ጎሎችን የሸመቱት ሲዳማዎች 2ለ0 በማሸነፍ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

ሽንፈት ያስተናገደው አዳማ ከተማ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በስህተቶች የተነሳ ጎሎች እንደገባባቸው ገልፀው በፈጠነ ሰዓት ጎል መግባት መቻሉ በኋላ ላይ ለመቆጣጠር እንደ ከባደቸውም ጠቁመው፡፡ በፍላጎት የተጫወቱት ሲዳማዎች ተበልጠው ጎል ተቆጥሮባቸው እንደተሸነፉም ተናግረዋል። ቡድናቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ እየመሩ ድል የተጎናፀፉት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በበኩላቸው ድሉ ትልቅ ነገር መሆኑን እና ነጥቡን ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው አስረድተው በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ በመሆናቸው ጎሎችን እንዳገኙ ገልፀዋል። ነገር ግን አሁንም የሚቀር ነገር እንዳለ ተናግረው አዳማን ለመቆጣጠር የተሄደበት ሂደት ግን መልካም እንደነበር በማስረፋት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡