ሪፖርት | ነብሮቹ ጣፋጭ ድል ከለገጣፎ ለገዳዲ አግኝተዋል

የጨዋታ ሳምንቱ የማሳረጊያ ፍልሚያ በ99ኛው ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ሀዲያ ሆሳዕናን አሸናፊ አድርጓል።

የባህር ዳር ቆይታቸውን በድል ያጠናቀቁት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ሦስት ነጥብ ካሳኩበት የወላይታ ድቻ ፍልሚያ ፀጋዬ ብርሃኑን ብቻ በሠመረ ሀፍታይ ተክተው ጨዋታውን ሲቀርቡ በተቃራኒው በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት በውድድሩ አስተናጋጅ ከተማ ክለብ ባህር ዳር ከተማ የሁለት ለምንም ሽንፈት ያስተናገዱት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በበኩላቸው የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። በዚህም የበረከት ተሰማ እና ኦካይ ጁልን ቦታ ፍቅሩ አለማየሁ እና አንዋር አብዱልጀባር ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

የጨዋታ ሳምንቱ የማሳረጊያ ፍልሚያ በሦስተኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ካስተናገደ በኋላ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የጠራ ሙከራ አልነበረውም። በተጠቀሰው ደቂቃም ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ሳጥኑ ጫፍ ያገኙትን የቅጣት ምት ኪሩቤል ወንድሙ በግራ እግሩ ግብ ለማድረግ ሞክሮ የግብ ዘቡ ፔፕ ሰይዶ አምክኖታል። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላም ከወደ ግራ ካደላ ቦታ ሌላ የቅጣት ምትን ለግብ ምንጭነት ለመጠቀም ሞክረዋል። ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫዎችን በማድረግ የጣፎን የግብ ክልል ለመጎብኘት የሞከሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው በ25ኛው ደቂቃ ቀጣዩን ለግብ የቀረበ ሙከራ አስመልክተዋል። በዚህም ጣፎዎች ራሳቸውን ለመልሶ ማጥቃት አጋልጠው የተሸነፉትን ሁለተኛ ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን አምልጦ ከወጣ በኋላ በግብ ጠባቂው ወንድወሰን ገረመው አናት ላይ በመላክ ለማስቆጠር ጥሮ ዒላማውም ስቶበታል።

አሁንም ከሙከራዎች የራቀው ጨዋታው የተመጣጠነ እንቅስቃሴ ቢያሳይም አንፃራዊ ብልጫ ያሳዩት ሀዲያዎች በ38ኛው ደቂቃ ባዬ ከሳጥን ውጪ በሞከረው ኳስ ወደ መሪነት ሊሸጋገሩበት ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ለገጣፎ ተፈራ አንለይ ዳግም ንጉሴን ቀድሞ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ ተስተናግዶበት የዕለቱ ዳኛ ተስፋዬ ጉርሙ ፊሽካ ተሰምቶ ቀዳሚው ክፍለ ጊዜ ተገባዷል።

ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ገና በተጀመረ በሰከንዶች ውስጥ የሀዲያው አምበል ሔኖክ አርፊጮ ከግራ መስመር በማሻማት እና መሞከር ሀሳብ ውስጥ ሆኖ የላከው ኳስ ሳይጠበቅ መረብ ላይ ለማረፍ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ወንድወሰን በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶታል። ረጃጅም ኳሶችን በአብዛኛው ለመጠቀም መጣራቸውን የቀጠሉት ጣፎዎች በበኩላቸው በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ መታተር ይዘዋል። በ63ኛው ደቂቃም ካርሎስ ዳምጠው የጨዋታውን ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ይሁ ግዙፍ አጥቂ ፔፕ ሰይዶ ኳስ በእግሩ ለመጠቀም ያደረገው ጥረት ለስህተት ሲዳርገው አግኝቶ ከመረብ ጋር አገናኘው ተብሎ ሲጠበቅ በድጋሜ ዕድሉን አምክኖታል።

በአብዛኛው ሽግግሮች የተስተዋሉበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ የጥራት ችግር መኖሩ ብቻ በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ፉክክር ያሳየው ፍልሚያ በግቦች እንዳይታጀብ አድርጎታል። የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ የሰነዘረው ሔኖክ ግን በ77ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አንተነህ በሚገባ ያላፀዳውን ኳስ ተጠቅሞ ወንድወሰንን ፈትኖ ሀዲያን መሪ ሊያደርግ ነበር።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመሩት 5 ደቂቃዎች አጋማሽ ላይ የጨዋታው ውጤት የወሰኑ ሁለት ወሳኝ ቅፅበቶች ተስተናግደዋል። በቅድሚያም ሀዲያዎች ከግራ መስመር ያሻሙትን ኳስ ሪችሞንድ ኦዶንጎ እንዳይጠቀመው ለማገድ የዘለሉት ግብ ጠባቂው ወንድወሰን እና ተከላካዩ መዝገቡ ተጋጭተው ጨዋታው ለደቂቃዎች ተቋርጧል። የጭንቅላት ግጭቱን ተከትሎ የግብ ዘቡ ህክምና ተደርጎለት ጨዋታውን ሲቀጥል መዝገቡ ግን መቀጠል ሳይችል በጎዶሎ ተጫዋች ጣፎ የቆመውን ጨዋታ አስቀጥሏል። ጣፎዎች የጀመሩት ኳስ በደቂቃ ልዩነት በ98ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝን ቀይሮ የገባው ተመስገን ብርሃኑ እግር ስር ደርሶ ወጣቱ ተጫዋች ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ሀዲያን የጣፋጭ ድል ባለቤት አድርጓል። ጨዋታውም ባለቀ ሰዓት አሸናፊ አግኝቶ ተጠናቋል።

የባለ ድሉ ክለብ ሀዲያ ሆሳዕና አሠልጣኝ ያሬድ ገመቹ ሙሉ 90 ደቂቃው ጠንካራ ፉክክር እንደተደረገበት ገልፀው ያሰቡት ድል በመጨረሻው ደቂቃ እንደተገኘ በማስረዳት በጨዋታው ላይ የታየውን የአጨራረስ ክፍተት ግን በቀጣይ ጨዋታዎች አሻሽለው እንደሚመጡ ተናግረዋል። የማሸነፊያውን ግብ ያስቆጠረው ተመስገን ያለውን አቅም እንዲጠቀም ከዚህም በላይ የመጫወቻ ዕድሎች እንደሚሰጡት ሲናገሩ ተደምጠዋል። ባለቀ ሰዓት በእጃቸው የነበረውን አንድ ነጥብ የተነጠቁትን ለገጣፎ ለገዳዲ የሚመሩት አሠልጣኝ ጥላሁን ተሾመ በበኩላቸው በጨዋታው ጥሩ ቢንቀሳቀሱም በመጨረሻው ደቂቃ በተፈጠረው የግብ ጠባቂ እና ተከላካይ ግጭት ትኩረታቸውን በማጣታቸው ግብ አስተናግደው እንደተሸነፉ ገልፀው አሁንም ቡድናቸው ውስጥ እየታየ የሚገኘው የልምድ ማጣት ችግር ዋጋ እያስከፈላቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል።