ከፍተኛ ሊግ | ቤንች ማጂ ቡና የበርካታ ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የተጠናቀቀውን ዓመት ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ የፈፀመው ቤንች ማጂ ቡና አስር አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሞ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡

በከፍተኛ ሊጉ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን አጋማሽ በምድብ ለ ስር ተደልድሎ በተለይ ሁለተኛው ዙር ላይ አሰልጣኝ መሐመድ ኑርንማን ከቀጠረ በኋላ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ምድቡን በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ላይ ተቀምጦ መፈፀም የቻለው ቤንች ማጂ ቡና አሁንም በአሰልጣኝ መሐመድ እየተመራ በሊጉ ላይ ጠንክሮ ለመቅረብ የአስር አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሞ በቡድኑ ካሉ አስራ አራት ነባሮች ጋር በማዋሀድ በክለቡ መቀመጫ ከተማ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡

ቡድኑ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ የቀድሞው የአዳማ ከተማ ፣ ወልዋሎ እና ያለፉትን ሁለት ዓመታት በመከላከል ያሳለፈው ጃፋር ደሊል ፣ ከሀዋሳ ከተማ የተገኘው እና በኢኮስኮ ፣ ወልድያ እና አምና ባቱ የተጫወተው ግብ ጠባቂው መስፍን ቡዜ ፣ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና በተጠናቀቀው ዓመት በኮልፌ ቀራኒዮ ያሳለፈው የመስመር አጥቂው እሱባለው ሙሉጌታ ፣ በሰበታ ከተማ እና በወልቂጤ የምናውቀው የአቡበከር ናስር ታላቅ ወንድም አማካዩ ጅብሪል ናስርን ጨምሮ ፣ ፉአድ ነስሮ ተከላካይ ከገላን ፣ አቡበከር ካሚል ተከላካይ ከኮልፌ ፣ ረጂብ ሚፍታህ ከኮልፌ ፣ ጴጥሮስ እንያለማው አማካይ ከኮልፌ ፣ ሙሉአለም በየነ አጥቂ ከጌዲኦ ዲላ እና ሀሰን ሁሴን ከባሌ ሮቤ የክለቡ አዳዲሶቹ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ያጋሩ