ሴካፋ | ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን በመለያ ምት በማሸነፍ ለአፍሪካ ዋንጫው በቅታለች

እልህ አስጨራሽ ትግል በተደረገበት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን በመለያ ምት በመርታት ለሴካፋ ውድድር ፍፃሜ እና ለአፍሪካ ዋንጫው መብቃቷን አረጋግጣለች።

በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ዩጋንዳን አንድ ለምንም የረታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምድቡን በበላይነት ያጠናቀቀበትን ውጤት ሲያገኝ ከተጠቀመው የመጀመሪያ አሰላለፍ ዮሴፍ ታረቀኝን ብቻ በአማኑኤል አድማሱ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

ጨዋታው በተጀመረ ገና በ2ኛው ደቂቃ በፈጣን ሽግግር ደቡብ ሱዳኖች ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ተመልሰዋል። የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወስደው መጫወት የጀመሩት ኢትዮጵያዎች በበኩላቸው በመጀመሪያው ፈጣን ጥቃት ሳይደናገጡ ወደ ፊት በመሄድ ግብ ለማግኘት ሲጥሩ በ9ኛው ደቂቃ በሳጥን ውስጥ ጥፋት ተሰርቶባቸው የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም የቡድኑ አምበል ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ግብነት ቀይሮት ኢትዮጵያ መሪ ሆናለች።

የኢትዮጵያ መሪነት ግን ከ9 ደቂቃዎች በላይ መዝለቅ አልቻለም። በ17ኛው ደቂቃም የግብ ዘቡ ውብሸት ጭላሎ በሰራው ጥፋት ደቡብ ሱዳኖች አቻ የሚሆኑበትን የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው በጆሴፍ ጄል አማካኝነት ተጠቅመውት ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። ጨዋታው በእኩል ውጤት ከቀጠለ በኋላም የአሠልጣኝ እድሉ ደረጄ ተጫዋቾች የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው በመጫወት ዳግም ወደ መሪነት ለመሸጋገር ጥረዋል። ነገርግን ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተው አጋማሹ ተጠናቋል።

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ አሁንም ኳስን በማንሸራሸር ለመንቀሳቀስ ስትሞክር ደቡብ ሱዳኖች ግን ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ወረድ ብለው በመከላከል የሚገኙ ኳሶችን በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ሲጥሩ ተስተውሏል። በተለይ በሁለቱ መስመሮች በኩል ትኩረት ሰጥተው ሲያጠቁ የነበሩት ኢትዮጵያዎች በ72ኛው ደቂቃ በፉዐድ አብደላ እንዲሁም በ73ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ታረቀኝ በሞከሯቸው ኳሶች እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። ከምንም በላይ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ላይ የግቡ ባለቤት ዮሴፍ ከዘላለም አባቴ የተሻማውን ኳስ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ወደ ግብ ቢልከውም ግብ ጠባቂው ያዳነበት አስቆጪ ዕድል ነበር። 90 ደቂቃው በአቻ ውጤት ተጠናቆ ተጨማሪ 30 ደቂቃዎች ተሰጥተዋል።

አሸናፊውን ለመለየት በተጨመረው 30 ደቂቃ ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ግቦች በ4 ደቂቃዎች ልዩነት ተቆጥረዋል። በቅድሚያም ዘላለም አባቴ በ107ኛው ደቂቃ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ግብ ሲያስቆጥር አጉዊምቦኪ አቢሻይ ደግሞ በ111ኛው ደቂቃ ከኢማኑኤል ሎቦካ የተላከለትን ኳስ በመጠቀም ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ጨዋታውም በዚሁ የአቻ ውጤት ተጠናቆ አሸናፊውን ለመለየት የመለያ ምት ተሰጥቷል። በመለያ ምቱም ደቡብ ሱዳን 4ለ2 አሸንፋ ለሴካፋ ውድድር ፍፃሜ እና ለአፍሪካ ዋንጫው መብቃቷን አረጋግጣለች።

በፍፃሜው ደቡብ ሱዳን ዩጋንዳን ስትገጥም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ የደረጃ ጨዋታውን ከውድድሩ አዘጋጅ ሱዳን ጋር የሚያደርግ ይሆናል።