የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ከጣራ ውጪ ያሉ ሥራዎችን በአንድ ዓመት ለማጠናቀቅ እና የካፍን 16 መሠረታዊ መስፈርቶች ለማሟላት የግንባታ ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
ኅዳር 2002 በ780 ሚሊዮን ብር በጀት 52 ሺህ ተመልካቾች እንዲይዝ ታስቦ ወደ ግንባታ የገባው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለግንባታው ማስጀመሪያ 389 ሚሊዮን ብር ተፈርሞ የነበር ሲሆን እስካሁንም 758 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበት ያለንበት ጊዜ ላይ ደርሷል። በዛሬው ዕለትም የስታዲየሙ ሁለተኛ ዙር ቀሪ ሥራ ግንባታ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።
በማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ፣ የኢፌዴሪ መረጃ እና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጀኔራል ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ ፣ የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ፣ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ፣ አትሌት ሞስነት ገረመው እና የክልሉ ባለሃብቶች እና ሌሎች በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በ MH ኢንጀነሪንግ አማካሪነት እና በሚድሮክ ኮንስትራክሽን ለሚደረገው ግንባታ 1 ቢሊየን 74 ሚሊዮን የተሰበሰበ ሲሆን ከጣራ ውጪ ያሉትን ሙሉ ሥራዎች የሚያጠቃልል እና በአንድ ዓመት የሚጠናቀቅ ይሆናል።
የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ቀጀላ መርዳሳ የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ ከሁሉ ስታዲየሞች በፊት ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳላቸው እና በቶሎ እንዲጠናቀቅ ያላቸውን ፍላጎት በማሳየት ድምጻቸውን ለማሰማት መምጣታቸውን ሲናገሩ ግንባታውን ለማጠናቀቅ የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉም አበክረው ገልጸዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው ብሔራዊ ቡድናችን በስታዲየም ዕጥረት ምክንያት ተሰዶ መጫወቱን ኮንነው ድርጅታቸው ስታዲየም ግንባታዎች በመሥራት እንደሚታወቅ ሲናገሩ ለባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምም ከተበጀተው 740 ሚሊዮን ብር ላይ 300 ሚሊየን ብር ጨምረው ግንባታውን እንደሚያሳልጡ አሳውቀዋል።
የክልሉ ርዕስ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ደግሞ ፕሮጀክቱ የሀገራችንን ስፖርት አንድ እርምጃ የሚያስኬድ መሆኑን ጠቁመው ግባቸው ግንባታውን ማስጀመር ሳይሆን ማጠናቀቅ እንደሆነ ገልጸዋል። ስታዲየሙን ብቻ ሳይሆን ከውጪ ያሉትን ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች አሻሽሎ በመሥራት ለወጣቶች ምቹ መዝናኛ ለማድረግ እንደሚሠሩም አስታውቀዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም “ሀገራችን ውስጥ ግንባታ ይጀመራል እንጂ አይጨረስም” የሚሉ የሕዝብ አስተያየቶችን በማስተካከል ግንባታውን ለመጨረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
ግንባታው 16 የካፍ መስፈርቶችን ለማሟላት የሚደረግ ሲሆን በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና የአማራ ክልል ወጣት እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዕርዚቅ ኢሳ መካከል የስምምነት ፊርማ ተደርጓል።
በመጨረሻም ግንባታውን በተግባር የማስጀመር ሥራ ተከናውኖ መርሃ – ግብሩ ተጠናቋል።