ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ6ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ6ኛ የጨዋታ ሳምንት በአንፃራዊነት የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው መርጠናል።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ : 4-2-1-3

ግብ ጠባቂ


ፍሊፕ ኦቮኖ – ሲዳማ ቡና

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የነጠረ ብቃት ያሳዩ የግብ ዘቦችን መመልከት ባንችልም በአንፃራዊነት ለግብ የቀረቡ ኳሶችን ሲያድን የተመለከትነውን ፍሊፕ ኦቮኖ በምርጥ ቡድናችን በግብ ብረቶቹ መካከል እንዲቆም አድርገነዋል። ተጫዋቹ ያን ያህል በአዳማ አጥቂዎች ባይፈተንም ሁለት ለግብነት የቀረቡ ኳሶችን ያዳነበት መንገድ ተመራጭ አድርጎታል።

ተከላካዮች


አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቶ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን ባሳካበት ጨዋታ ላይ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በመከላከሉ እና በማጥቃቱም በኩል የተሳካ ጊዜን ሲያሳልፍ አሳንቴ ጎድፍሬድ እና ቢንያም ጌታቸው ያስቆጠሯቸው ግቦችንም አመቻችቶ አቀብሏል። በዚህም ያለ ተቀናቃኝ የሳምንቱ ምርጥ ውስጥ መካተት ችሏል።

ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻ መቻልን ድል አድርጎ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን ሲያሳካ ደጉ የቡድኑን የኋላ መስመር አስተማማኝ በማድረግ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች የበላይነት በመውሰዱ በኩል እጅግ የተሳካ ጊዜን በማሳለፍ ቡድኑ ግብ እንዳይቆጠርበት እና የመቻል ተጫዋቾች በምቾት እንዳያጠቁ በማድረግ የተሳካ ጊዜን አሳልፏል።

አሳንቴ ጎድፍሬድ – ድሬዳዋ ከተማ

ግዙፉ የመሐል ተከላካይ አሳንቴ ቡድኑ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል እንዲያገኝ የመጀመሪያውን ጎል በግንባሩ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ዋነኛ ኃላፊነቱ በሆነው መከላከል በዐየርም ሆነ በምድር ኳሶች ከፍተኛ ንቃት በማሳየት የቡናን ጥቃቶች ሲመክት የነበረበት ሂደት ተመራጭ አድርጎታል።

ሄኖክ አርፌጮ – ሀዲያ ሆሳዕና

የግራ መስመር ተከላካዩ ሔኖክ በፈታኙ የጣፎ ጨዋታ ቡድኑን በምሳሌ በአምበልነት ከመምራቱ በተጨማሪ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ አበርክቶ ሲሰጥ ነበር። በተለይ ወደ ሳጥን ከሚልካቸው ተሻጋሪ ኳሶች ባለፈም ራሱ በቀጥታ የግብ ምንጭ ለመሆን ሲጥር ተመልክተናል።

አማካዮች


ዮሴፍ ዮሀንስ – ድሬዳዋ ከተማ

በተለያዩ ምክንያቶች በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ በተጠባባቂ ወንበር ለመቀመጥ ተገዶ የነበረው አማካዩ ለቡድኑ ከለገጣፎ ለገዳዲው ጨዋታ በኋላ በመጀመሪያ ተሰላፊነት በጀመረበት ጨዋታ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት ችሏል። በጨዋታው የድሬዳዋን የመሀል ሜዳ በድንቅ ብቃት ሲቆጣጠር የነበረው ዮሴፍ በተለይ የተጋጣሚን ጥቃት ሲያቋርጥበት የነበረበት መንገድ አድናቆት የሚያስቸረው ሲሆን አንድ ግብም ከፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።

አብዱልባሲጥ ከማል – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ፋሲልን ሁለት ለምንም ሲረታ በመሐል ሜዳው ላይ እጅግ አስደናቂ ብቃት ያሳየው አብዱልባሲጥ ከማል የምርጥ ቡድናችን አካል ሆኗል። የተከላካዮችን ስራ በማቃለል ከፍተኛ ሽፋን ሲሰጥ የነበረው አማካዩ ሰንጣቂ ኳሶችን ወደፊት እየላከ ቡድኑን ሲጠቅም ነበር። በ78ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ላስቆጠረው ጎል መገኘትም የበኩሉን ተወጥቷል።

ፍሬው ሰለሞን – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን በረታበት ጨዋታ ምንም እንኳን ይገዙ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ርዕሰ ዜናዎችን ሁሉ ቢወስድም በጨዋታው ፍሬው ሰለሞን የነበረው አበርክቶ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። በጨዋታው ይገዙ ላስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ኳሶቹን አመቻችቶ ማቀበል የቻለው ፍሬው በአጠቃላይ በውድድር ዘመኑ አመቻችቶ ያቀበላቸውን ኳሶች መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል።

አጥቂዎች

ይገዙ ቦጋለ – ሲዳማ ቡና

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው ይገዙ ቦጋለ በአዲሱ የውድድር ዘመን ግን ቀዝቀዝ ያለ አጀማመርን ያደረገበት ነበር። በአምስት ጨዋታዎች አንድ የሊግ ግብ ብቻ የነበረው አጥቂው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወሳኝ ሁለት የማሸነፍያ ግቦችን ለቡድኑ ማስቆጠር ችሏል። ይህም የራስ መተማመኑን ለመመለስ በቀጣይ ይበልጥ ያግዘዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ

ከዓመት ዓመት ወጥ አቋም በማሳየት የቀጠለው ጌታነህ ልዩነት ፈጣሪነቱን ዳግም አሳይቷል። ወልቂጤ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ላሳየው ብልጫ የተጋጣሚ ተከላካይ መስመር እንዳይረጋጋ በማድረግ በእንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋፅዖ የነበረው ጌታነህ በግንባር እና በቅጣት ምት ሁለቱንም የቡድኑን ጎሎች ከመረብ ማገናኘት ችሏል።

ኤፍሬም አሻሞ – ሀዋሳ ከተማ

ኃይቆቹ ዐፄዎቹን በመርታት ወደ ድል በተመለሱበት ጨዋታ የፋሲል ተከላካዮችን ዕረፍት በመንሳት ብዙ ቦታዎችን በማካለል ድንቅ በሆኑ ሩጫዎቹ የተለያዩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችል የነበረው ኤፍሬም የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶም በግሩም አጨራረስ አንድ ግብ በስሙ ማስመዝገቡም ያለ ከልካይ በምርጥ ቡድናችን ቦታ እንዲኖረው አድርጓል።

አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ – ድሬዳዋ ከተማ

አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ድሬዳዋ ወደ መቀመጫ ከተማው በመምጣት ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ሦስት ነጥብ እንዲያሳካ ማድረግ ችለዋል። ቡድኑ የኢትዮጵያ ቡናን እንቅስቃሴ በማርገብ በጥሩ የጨዋታ ቁጥጥር በተፋለመበት ጨዋታ ከወትሮው በተለየ ተነሳሽነት እና ታታሪነት ብልጫ በመውሰድ ተጋጣሚውን 3-1 ረቷል።

ተጠባባቂዎች

ዳንኤል ተሾመ
ተስፋዬ ታምራት
አማኑኤል እንዳለ
ኢማኑኤል ላርዬ
ብዙዓየሁ ሰይፈ
ፉዐድ ፈረጃ
ሀብታሙ ታደሰ
ሙጅብ ቃሲም