ሪፖርት | ጥሩ ፉክክር ያስተናገደው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተቋጭቷል

የሰባተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

10፡00 ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ፈረሰኞቹ በስድስተኛው ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 1-1 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አማኑኤል ተርፉ ፣ ሱሌማን ሀሚድ እና ሀይደር ሸረፋ በምኞት ደበበ ፣ ረመዳን የሱፍ እና በረከት ወልዴ ተተክተው ጀምረዋል። ሠራተኞቹ በበኩላቸው በስድስተኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-1 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ቀርበዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ጊዮርጊሶች በኳስ ቁጥጥሩ እና የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል የበላይነቱን መውሰድ ሲችሉ ወልቂጤዎች 12ኛው ደቂቃ ላይ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር ችለው ነበር። የኋላሸት ሰለሞን እና ጌታነህ ከበደ በጥሩ ቅብብል በወሰዱት ኳስ ጌታነህ ከበደ በግሩም እይታ የኋላሸትን ሰለሞንን ከግብ ጠባቂው ጋር ያገናኘ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ቢችልም የኋላሸት ከተጋጣሚ የሳጥን ጫፍ ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ የአጨራረሱ ድክመት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ቻርልስ ሉክዋጎ ሊያግደው ችሏል።

ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ውስጥ በቁጥር በዝተው በሚያገኙት ኳስ በመልሶ ማጥቃት ጥቃት ለመሰንዘር ያለሙ የሚመስሉት ወልቂጤዎች 30ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ጌታነህ ከበደ ከግራ መስመር ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዝግጁ አለመሆኑ ተጨምሮ ኳሱን መቆጣጠር ባለመቻሉ የማዕዘን ምት ሊሆን ችሏል።

እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ፈረሰኞቹ 35ኛው ደቂቃ ላይ ባደረጉት በመጀመሪያው የተሻለ ሙከራቸው ግብ ማስቆጠር ችለዋል። እስማኤል ኦሮ አጎሮ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ነፃሆኖ ያገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል በግራ እግሩ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ በድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ፈረሰኞቹ በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ ከቢንያም በላይ የተቀበለው አማኑኤል ገብረሚካኤል ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ሊያወጣው ችሏል።

ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ፈረሰኞቹ በተሻለ መልኩ ወደፊት ተጠግተው መጫወት ሲችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ የባከኑ ደቂቃዎች ሲቀሩ ረጅም ርቀት ላይ ከተገኘ የቅጣት ምት ሱሌማን ሀሚድ ሲያሻማ ያገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል ተገልብጦ የግብ ሙከራ ቢያደርግም የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞታል።

በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በፈጣን ሽግግሮች የታገዙ ሙከራዎችን ሲያስመለክተን ሠራተኞቹ አጋማሹ ከተጀመረ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ፈጣን የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ የኋላሸት ሰለሞን ከረጅም ርቀት ያሻማውን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግንባሩ ገጭቶት ግብ ጠባቂው ሲመልሰው ያገኘው አቡበከር ሳኒ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በጊዮርጊስ ተከላካዮች ተመልሶበታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ፈረሰኞቹ በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ ጋቶች ፓኖም በግራ መስመር ላይ ለነበረው ቸርነት ጉግሣ ሲያቀብል ቸርነት ያደረገው ሙከራ ዒላማውን መጠበቅ ሳይችል ቀርቷል።

ወልቂጤ ከተማዎች ከረፍት መልስ እጅግ ተሻሽለው ሲቀርቡ 70ኛው ደቂቃ ላይ በተከታታይ ጨዋታዎች ደካማ እንቅስቃሴ ያሳየው የግብ ጠባቂው ቻርልስ ሉክዋጎ በሠራው ስህተት በትክክል ያላራቀውን ኳስ ያገኘው በዕለቱ ኮከብ የነበረው አቡበከር ሳኒ በቀላሉ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በአራት ደቂቃዎች ልዩነት የፈረሰኞቹን የኋላ መስመር አለመረጋጋት ተከትሎ የተገኘውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ከቀኝ መስመር ሲያሻማ ያገኘው አቡበከር ሳኒ የግብ ጠባቂው የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮበት በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ሠራተኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች የተሻለ ወደፊት ተጠግተው የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ 90ኛው ደቂቃ ላይ ከተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ የተገኘውን ኳስ ጋቶች ፓኖም በግራ እግሩ ወደ ግብ ሞክሮት ዋሃብ አዳምስ ተደርቦ የመለሰውን ኳስ ያገኘው እስማኤል ኦሮ አጎሮ ወደ ግብ ሲሞክር ኳሱ የላዩን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል። ፈረሰኞቹ ተስፋ ባለመቁረጥ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዝሩ በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ሱለይማን ሀሚድ ያሻማውን ኳስ ያገኘው እስማኤል ኦሮ አጎሮ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን አቻ ማድረግ ችሏል። የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ የወልቂጤ ከተማ ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው ሰዓት አባክነሃል በሚል በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል። ጨዋታውም 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጨዋታው ክፍት እና በሁለቱም በኩል ጥሩ እንደነበር ገልፀው በጨዋታው በሠሯቸው ስህተቶች ግብ እንደተቆጠረባቸው እና በቀጣይም እዚህ ላይ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው ተገቢውን ውጤት እንዳላገኙ እና የተወሰኑ የዳኛ ውሳኔዎች ላይ ደስተኛ እንዳልነበሩ ሲናገሩ ያለፉት ጨዋታዎች ላይ ሲሠሯቸው የነበሩ ስህተቶችን እያረሙ እንደመጡም ጠቁመዋል።