በሁለተኛው አጋማሽ የተቆጠሩት ሁለት ግቦች ድሬዳዋ ከተማ እና መቻልን ነጥብ አጋርተዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን የረታበት ቀዳሚ አሰላለፍ ላይ ለውጥ ሳያደርግ ለጨዋታው ሲቀርብ መቻል በበኩሉ ከወላይታ ድቻው ሽንፈት ሦስት ለውጦችን አድርጓል። በዚህም መሰረት ቶማስ ስምረቱ በየአብስራ ሙሉጌታ ፣ ምንተስኖት አዳነ በከነዓን ማርክነህ እንዲሁም ሳሙኤል ሳሊሶ በግርማ ዲሳሳ ተተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ባለሜዳው ድሬዳዋ ከተማ ክለብ በክቡር ዶ/ር አርቲስት ዓሊ ቢራ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን የአርቲስቱ ምስል ያረፈበት ቲ-ሸርት እና ባነር ይዞ በመግባት ከገለፀ በኋላ በስታዲየሙ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።
በተሻለ የማጥቃት ተነሳሽነት መጫወት የጀመሩት መቻሎች በፈጣኖቹ አጥቂዎች ትጋት በጊዜ መሪ ለመሆን ሲጥር ነበር። በ12ኛው ደቂቃም ወደ ቀኝ ካደላ መስመር ሳሙኤል ሳሊሶ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ የጨዋታው ቀዳሚ ሙከራ ሆኗል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ወዲያው ምላሽ ለመስጠት የወጡት ድሬዳዋዎች በበኩላቸው ከደቂቃ በኋላ ጥሩ ዕድል ፈጥረው ነበር። በዚህም አቤል አሰበ በተከላካዮች መካከል ከያሬድ ታደሰ የደረሰውን ኳስ ለመጠቀም ጥሮ ቶማስ ስምረቱ አውጥቶበታል።
በአንፃራዊነት ተመጣጣኝ የመሐል ሜዳ ፉክክር ማስመልከት የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቀጣዩን ሙከራ በ24ኛው ደቂቃ አስተናግዷል። በዚህም ፍፁም ዓለሙ በመስመሮች መካከል ያገኘውን ኳስ እየገፋ ሄዶ ሲያሻማው የመሐል አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ ዒላማውን ስቶበታል። ትናንትና እና ዛሬ በድሬዳዋ የዘነበውን ዝናብ ተከትሎ ጨቅየት ያለው ሜዳ ኳስን በሚገባ ለማንሸራሸር አልመች ብሎ በርከት ያሉ የቅብብል ሂደቶች ሲበላሽ አስተውለናል።
በማጥቃቱ ረገድ የተሻሉት መቻሎች ግን አሁንም የድሬን የግብ ክልል መፈተሽ ይዘዋል። በመጀመሪያ በ37ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ከመስመር መሬት ለመሬት የላከውን ኳስ ምንይሉ ሳይጠበቅ ጨርፎት አቅጣጫውን ወደ መረብ ቢያደርግም የግብ ዘቡ ዳንኤል ተሾመ በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በረከት በግራ እግሩ ከሳጥን ውጪ የአጋማሹን ሁለተኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጓል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ምንይሉ ከፍፁም ጋር አንድ ሁለት ተጫውቶ የደረሰውን የመጨረሻ ኳስ መትቶት የግቡ ቋሚ ከግብነት አግዶበታል።
ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጠራ የግብ ሙከራዎችን ለማስተናገድ 23 ደቂቃዎች ወስደውበታል። እስከዛ ግን በአጋማሹ የአማካይ መስመር ለውጥ ያደረጉት ድሬዳዋዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ለመቻሎች የፈቀዱላቸውን የግብ ዕድል መፍጠሪያ ክፍተቶች በመዝጋት ዘለግ ያለውን ደቂቃ ከኳስ ጋር ሲጫወቱ አስተውለናል። አልፎ አልፎም ቢኒያም ጌታቸውን ዒላማ ያደረጉ ኳሶችን ወደ ሳጥን እየላኩ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በተለይ የአጥቂ አማካዩ ኤሊያስ አህመድ በማጥቃቱ ረገድ የተሻለውን አበርክቶ ሲሰጥ ነበር።
ጨዋታው 68ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ እንደገለፅነው በአጋማሹ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ ተስተናግዷል። በዚህም ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ የድሬዳዋ ተከላካዮች አንደኛውንም ሆነ ሁለተኛውን ኳስ ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተው ሳሙኤል ሳሊሶ አግኝቶት በቀጥታ በግራ እግሩ መረብ ላይ አሳርፎታል። ከ8 ደቂቃዎች በኋላ ግን በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ፊት እየተጫወቱ የሚገኙት ድሬዎች አቻ ሆነዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ቶማስ ስምረቱ ቢኒያም ጌታቸው ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ያሬድ ታደሠ ወደ ግብነት ቀይሮታል።
በአቻነቱ ግብ የተነቃቁት ድሬዎች በ77ኛው ደቂቃ ቢኒያም ከወደ ግራ ካደላ የሳጥኑ ክፍል አክርሮ በመታው እና ግብ ጠባቂው ዳግም ባዳነበት ኳስ ወደ መሪነት ሊሸጋገሩ ተቃርበው ነበር። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጭነው ለመጫወት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። መቻሎችም አጥቂ በመቀየር ዳግም መሪ ለመሆን ቢያስቡም ውጥናቸው ሳይሰምር ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች በጭቃ መጫወታቸው ጨዋታውን ከባድ እንዳደረገው የገለፁት አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ከመመራት ተነስተው ውጤት መጋራታቸው ሜዳ ላይ ከነበራቸው ተነሳሽነት እንደመነጨ ጠቁመው ቡድናቸው ወደ ሜዳ ሲገባ አስቦት ስለገባው የድምፃዊ ዓሊ ቢራ ህልፈት ለቀረበላቸው ጥያቄ ለመግለፅ እንደሚከብዳቸው ተናግረዋል። የመቻሉ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው ቡድናቸው ዕድሎችን ለመጨረስ መረጋጋት እንዳልነበረው ያም ቢሆን የሚችለውን ማድረጉ እና አሁን ላይ ካለበት የሥነልቦና ጫና አንፃር አንድ ነጥብ ማግኘቱ የማያስከፋ ቢሆንም ለተከታታይ ጊዜ የተሰጠባቸው ፍፁም ቅጣት ምት አሳማኝ አለመሆኑን ገልፀዋል።