በሰባተኛው የጨዋታ ሳምንት የሚስተናገዱ የነገ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በሊጉ የቆየ ታሪክ የነበራቸው እና ላለፉት ዓመታት ግን በከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ የቆዩት ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዘንድሮ አብረው አድገው ነገ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ሁለቱም የድሬዳዋ ቆይታቸውን በሽንፈት መጀመራቸው ደግሞ ከነገው ፍልሚያ በፊት የሚያመሳስላቸው ሌላኛው ነጥብ ሆኗል።

በስድስተኛው ሳምንት ካስመዘገቡት ሽንፈት በተጨማሪ መድንም ሆነ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቀደሙት ጨዋታዎች የነበራቸውን ጠንካራ ጎን በጎላ ሁኔታ የጡባቸውን ጨዋታዎች ነበር የከወኑት። ከመምራት ተነስቶ በባህር ዳር ሙሉ ነጥብ የተነጠቀው መድን ከዚያ ቀደም ተከታታይ ድሎችን ሲያስመዘግብ ጠንካራ ጎኑ የነበረው አማካይ ክፍሉ በጣና ሞገዶቹ የተወሰደበት ብልጫ ለሽንፈቱ ዋና ምክንያት ነበር ማለት ይቻላል። በተመሳሳይ ወልቂጤ ከተማ ከኳስ ውጪ በነበረው ትጋት የተቆራረጡ ቅብብሎችን ለማድረግ የተገደደው ኢትዮ ኤሌክትሪክም እንዲሁ የወትሮውን የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ማግኘት ተስኖት ታይቷል።

በመሆኑም በነገው ጨዋታ አማካይ ክፍሉን ከመጨረሻው ጨዋታ በተሻለ ሁኔታ ከተዕዕኖ ነፃ አድርጎ መንቀሳቀስ የሚችለው ቡድን የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ዕድል ይኖረዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በወቅታዊ ዝናባማ የዓየር ሁኔታ ምክንያት የድሬዳዋ ስታድየም የመጫወቻ ሜዳ ለሁለቱ ተጋጣሚዎች በተለይም ይበልጥ በአጫጭር ቅብብሎች ላይ ተመስርቶ ለሚንቀሳቀሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የራሱን ፈተና ሊሰጥ ይችላል ተብሎ ይገመታል።

ነገ 10:00 ሲል በፌደራል ዳኛ ሀብታሙ መንግሥቴ መሪነት በሚጀምረው በዚህ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን የመስመር ተከላካዩ ሳሙኤል ዮሐንስን በጉዳት የማያገኝ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ እያገገመ የሚገኘው ተስፋዬ በቀለን ጨምሮ ሚኪያስ መኮንን እና ሔኖክ አየለን በጉዳት ምክንያት እንደሚያጣ ታውቋል።

ሲዳማ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ

በፕሪምየር ሊጉ 25ኛ የሆነው የሮድዋ ድረቢ ነገ በኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ መሪነት 10:00 ላይ ይጀምራል። ቡድኖቹ ካላቸው የፉክክር መንፈስ በተጨማሪ ከድል መልስ የሚገናኙ መሆኑ ደግሞ የደርቢው ፍልሚያ በጉጉት እንዲጠበቅ በር ከፍቷል።

በስድስተኛው ሳምንት ባሳኩት ድል ውስጥ ሁለቱም ተጋጣሚዎች የመከላከል አደረጃጀታቸው ተሻሽሎ ታይቷል። የአምናውን የጊትጋት ጉት እና ያኩቡ መሐመድ ጥምረት መልሰው ያገኙ የሚመስሉት ሲዳማዎች በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል። በባህር ዳር ቆይታው በስብስቡ ውስጥ ያሉት ተከካካዮችን በመሉ አፈራርቆ የተጠቀመው ሀዋሳ ከተማም በበረከት ሳሙኤል እና ሰዒድ ሁሴን ጥምረት በዘንድሮው ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ሳያስተናግድ ጨዋታውን ጨርሷል። በመሆኑም የነገው ጨዋታ ቡድኖቹ ከሳምንታት በኋላ ያገኙትን የኋላ መስመር ብርታት የማስቀጠል የቤት ሥራን የሚሰጣቸው ይሆናል።

በነገው ጨዋታ ትኩረት የሚስበው ዋነኛው ጉዳይ ግን የማጥቃት ሽግግር ይሆናል። መሀል ላይ የሙሉዓለም መስፍን እና ሙሉቀን አዲሱ ጥምረት የሰመረለት ሲዳማ ለኋላ ክፍሉ ጥሩ ሽፋን ከመስጠት ባለፈ የፈጠራ ምንጩ የሆነው ፍሬው ሰለሞን በነፃነት በመንቀሳቀስ ተፅዕኖው እንዲጎላ አድርጎታል። ይህም ቡድኑ ኳሶችን አቋርጦ በቶሎ ወደማጥቃት ለመሸጋገር ነገሮችን ምቹ አድርጎለታል። በተመሳሳይ መልኩ ሀዋሳ ከተማ በፋሲሉ ጨዋታ በእነአብዱልባስጥ ከማል መሪነት የተጋጣሚውን ጫና የሚያረግብ የመከላከል አደረጃጀት ተግብሮ መታየቱ ራሱን ለሙከራዎች ላለማጋለጥ የረዳው ከመሆኑ ባለፈ የኤፍሬም አሻሞ እና ዓሊ ሱለይማንን ፍጥነት በመጠቀም ፈጣን የማጥቃት ሽግግርን መተግበሩ በየትኛውም ሰዓት ጎል የማግኘት ባህሪን አላብሶት ታይቷል። ይህም የነገው ጨዋታ የተሳከ የማጥቃት ሽግግሮችን በማድረግ ላይ ሊወሰን እንደሚችል ይነግረናል። ይህንን በስኬት መወጣት የቻለ እና ለይገዙ ቦጋለ አልያም መጂብ ቃሲም የተሻሉ ዕድሎችን መፍጠር የቻለ ቡድን ብልጫ ሊወስድ የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው።

መድኃኔ ብርሀኔን በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ሀዋሳ ከተማ አዲሱ አቱላን ከጉዳት እንዲሁም ወንድምአገኝ ኃይሉን ከክለቡ ጋር ከገባበት ውዝግብ መልስ የሚያገኝ ሲሆን በሲዳማ ቡና በኩል በጉዳት ሳቢያ ጨዋታው የሚያመልጠው ብቸኛው ተጫዋች ሳላዲን ሰዒድ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በ24 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ሲዳማ ቡና ዘጠኝ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ሰባት ጊዜ ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በጨዋታዎቹ በድምሩ 55 ኳሶች መረብ ላይ ሲያርፉ ሲዳማ 30 ሀዋሳ ደግሞ 25 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ያጋሩ