ወልቂጤ ከተማ ለፕሪምየር ሊጉ የበላይ አካል ደብዳቤ አስገብቷል

በትናንትናው ዕለት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ የተጋራው ወልቂጤ ከተማ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የጨዋታ ክስ ደብዳቤ ማስገባቱን ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቋል።

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ድሬዳዋ ከተማ እየተደረጉ እንደሚገኝ ይታወቃል። በትናንትናው ዕለትም የ7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ ፍልሚያም ጥሩ ፉክክር ተደርጎበት ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በጨዋታው ደስተኛ ያልሆኑት ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ ከዳኝነት ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን የገለፁበት የጨዋታ ክስ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ማስገባታቸውን አሳውቀውናል።

በክለቡ ቡድን መሪ ስም እና ፊርማ በተፃፈው ደብዳቤ የዕለቱ ዳኛ ያለአግባብ 6 ደቂቃ መጨመራቸውን እና ግብ ጠባቂያቸው ጀማል ጣሰው ሰዓት አባክኗል በሚል በሁለት ቢጫ ከሜዳ እንደወጣ በመጥቀስ አክሲዮን ማኅበሩ ማጣራት አድርጎ ተገቢ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።