ከሀገሪቱ ሦስተኛው የሊግ ዕርከን ወደ ከፍተኛ ሊጉ ያደገው ቦዲቲ ከተማ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሀያ ነባር ተጫዋቾችንም ውል አድሷል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት የአንደኛ ሊግ ተሳታፊ የነበረው እና ድሬዳዋ ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው የማጠቃለያ ውድድር ላይ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ማደግ የቻለው ቦዲቲ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚሳተፍበት ውድድር ራሱን ለማጠናከር በአዳዲስ ተጫዋቾች እና በነባሮቹ ስብስቡን እያጠናከረው ይገኛል፡፡ ቀደም ብሎ የአሰልጣኝ ደረጀ ከሹን ውል ያደሰው ቡድኑም ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሀያ ተጫዋቾችን ውልም ማራዘሙ ታውቋል፡፡
ክለቡን የተቀላቀሉ አዳዲስ ፈራሚዎችን ስንመለከት ውብሸት ክፍሌ ተከላካይ ከስልጤ ወራቤ ፣ ሳሙኤል በቀለ ተከላካይ ከሶዶ ከተማ ፣ ማንዴላ መለሰ ተከላካይ ከአረካ ከተማ ፣ አቦነህ ገነቱ አማካይ ከሀላባ ከተማ ፣ ዮርዳኖስ እያሱ አጥቂ ከአርባምንጭ በውሰት ውል እና ናትናኤል ዳንኤል አጥቂ ከሾኔ ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡