ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማን ያገናኘው የሩዱዋ ደርቢ ድራማዊ በሆነ ሁለተኛ አጋማሽ ታጅቦ በእዮብ ዓለማየሁ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል ሀዋሳን አሸናፊ አድርጓል፡፡
ሲዳማ ቡና አዳማን ያሸነፈበትን ስብስብ ሳይለውጥ ለጨዋታው ሲቀርብ ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ በፋሲሉ ጨዋታ በቀይ በወጣው መድሀኔ ብርሀኔ ምትክ ሰለሞን ወዴሳን በብቸኝነት ቀይሮ ገብቷል፡፡
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ለዕይታ ማራኪ ነበር ለማለት አያስችልም፡፡ ኳስን በማንሸራሸር በወጥነት ለመጫወት ቡድኖቹ ከጅምሩ ጥረት ቢያደርጉም በጣለው ዝናብ ምክንያት ሜዳው ምቹ አለመሆኑን ተከትሎ ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር ረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ ለመንቀሳቀስ ተገደዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ አብዱልባሲጥ ከማል ከግራ የሲዳማ የግብ አቅጣጫ ወደ ሳጥን ሲያሻማ ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ ወደ ጎል ስትንደረደር ፊሊፕ ኦቮኖ ባወጣበት ሙከራ ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል በመድረሱ ረገድ ባይቸገሩም በቀላሉ ጥቅጥቅ ባለ የመከላከል አደረጃጀትን ሲተገብሩ የነበሩትን የሀዋሳ ተከላካዮችን አልፈው ግብ ለማስቆጠር ተቸግረው ታይተዋል፡፡
ከሜዳው ምቹ አለመሆን ጋር በተገናኘ የሚቆራረጡ ኳሶች በበዙበት በዚህኛው አጋማሽ ሀዋሳዎች የኋላ መስመራቸውን በማስጠበቅ በመልሶ ማጥቃት ረጃጅም ኳስን በመጠቀም የግብ ዕድልን ለመፍጠር ታትረዋል፡፡ 27ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ኤፍሬም ያሻማለትን ዓሊ ሱለይማን አግኝቶ በቀላሉ አስቆጠረው ሲባል ኳሷን ወደ ላይ ሰዷታል፡፡ ጨዋታውን በራሳቸው እግር ስር በማቆየቱ ሲዳማ ቡናዎች መሻል ቢችሉም በጨዋታው የፈጠሩት የግብ ዕድል ግን አንድ ብቻ ነበር፡፡ 43ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ ላይ ዳንኤል ደርቤ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን ወደ ጎል መቶ መሀመድ ሙንታሪ ያወጣበት የምትጠቀሰዋ ሙከራ ነበረች፡፡
ሁለተኛውን አጋማሽ በፍጥነት የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በቅብብል የሀዋሳ የጎል ክልል ደርሰው በቡልቻ ሹራ ተቀይሮ የገባው ጉድዊን ከእንዳለ የደረሰውን ኳስ ከግቡ ትይዩ ሆኖ ቢያገኘውም ጭቃን የተላበሰው ሜዳ አቅጣጫ አስቀይሮት ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ይዘቱ የተስካከለ የሚመስለው ጨዋታው በርካታ ክስተቶችን ያስመለከተን ነበር፡፡ 55ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ ፊሊፕ ኦቮኖ ዓሊ ሱለይማን ወደ ግብ ሲሞክር ከግብ ክልሉ ውጥቶ ኳስን በእጅ ነክቷል በሚል በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ጨዋታው ስድስት ያህል ደቂቃዎችን ከዘገየ በኋላ እንዳለ ከበደን በማስወጣት መክብብ ደገፉን ካስገቡ በኋላ ቀጥሏል፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ጥንቃቄ አዘል ጨዋታን ከመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጋር መርጠው መንቀሳቀስን ከጀመሩ በኋላ ጎል አስቆጥረዋል፡፡
66ኛው ደቂቃ ላይ ጊት ጋትኩት በሙጂብ ቃሲም ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ በግምት ከ35 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን የቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው እዮብ አለማየሁ አክርሮ በመምታት ጎል አስቆጥሮ ሀዋሳን መሪ አድርጓል፡፡
ከእንቅስቃሴ ይልቅ ጥፋቶች እየተበራከቱ የመጡበትን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 72ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጣሪው እዮብ አለማየሁ ከደግፌ ዓለሙ ጋር በፈጠረው እሰጣ አገባ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል፡፡
76ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ተባረክ ሄፋሞ የደረሰው ኳስ ወደ ጎል ሲመታው የግቡን ቋሚ ገጭታ ገባች ሲባል ደግፌ ዓለሙ ከግቡ ውስጥ ተንሸራቶ አውጥቷታል፡፡ ኳሷ መስመር አልፋለች በሚል የሀዋሳ ተጫዋቾች በዕለቱ ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ላይ ተቃውሞ ቢያሰሙም ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅጉን በተሻለ የፉክክር መንፈስ የተንፀባረቀበት ጨዋታም በሀዋሳ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ሜዳው ለጨዋታ ምቹ አለመሆኑን ገልፀው በጨዋታው ላይ ግን ጥሩ እንደነበሩ እና የተጫዋች ቁጥርን በመጨመር ለማጥቃት አስበው እንዳልተሳካ እንዲሁም የግብ ጠባቂው ፊሊፕ ኦቮኖ በቀይ ካርድ መውጣት የጨዋታውን መንገድ እንዳበላሸባቸው ጠቁመዋል። ድል የቀናው ሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የጭቃ ጨዋታ ከባድ መሆኑን ከገለፁ በኋላ ጨዋታው የጭቃ ጨዋታ እንደማይመስል እና ለመሸናነፍ ጠንካራ እና ፈታኝ ፉክክር የታየበት መሆኑን ካስረዱ በኋላ ከዕረፍት በኋላ ረጃጅም እና በቆመ ኳስ ለመጫወት አቅደው ያም እንደተሳካላቸው ተናግረዋል፡፡