የ7ኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች በሚከተለው መልኩ ቀርበዋል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ
በተቀራራቢ የጨዋታ መንገድ አዎንታዊ ውጤትን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ያሳኩትን አርባምንጭ ከተማዎችን ከባህር ዳር ከተማ የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ የመጀመሪያ መርሃግብር ነው።
በሊጉ በአምስት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች በተከታታይ ከኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ካደረጓቸው ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ማግኘት የቻሉ ሲሆን አሁን ደግሞ በተከታታይ ባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማን የሚገጥሙ ይሆናል። በሊጉ እስካሁን በአንድ ጨዋታ ብቻ ድል የቀናቸው አርባምንጭ ከተማዎች አሁንም የመጀመሪያ ተመራጭ ተሰላፊ ተጫዋቾቻቸውን ፍለጋ ለውጦችን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። እስካሁን በስብስባቸው ከያዟቸው ተጫዋቾች መካከል ሃያ አራቱን የተጠቀሙት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከተጫዋቾች ባለፈ በጨዋታዎች ቡድኑ የተለያዩ ነገሮችን ለመሞከር ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን ውጤታማውን መንገድ በመፈለግ ላይ ይገኛሉ።
በጨዋታው አርባምንጭ ከተማ ሦስት አማካዮቹን አይጠቀምም። እንዳልካቸው መስፍንን በጉዳት እንዲሁም አቡበከር ሻሚል እና ቡጣቃ ሸመና ደግሞ በ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ በመሆናቸው ለነገው የአዞዎቹ ጨዋታ አይደርሱም።
በሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት በወልቂጤ ከተማ ከተረቱ ወዲህ ከጨዋታ ጨዋታ የተሻሻለን እንቅስቃሴን እያደረጉ ነጥቦችን እየሰበሰቡ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች አሁን ላይ በሊጉ በአስራ አንድ ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በቡድኑ ውስጥ በተለይ የአጥቂ አማካዩ ፉዓድ ፈረጃ ተፅዕኖ በሰሞኑ ጨዋታዎች ይበልጥ እያደገ ይገኛል። በአዲሱ የውድድር ዘመን ከአማራጭነት ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት ራሱን እያሳደገ የሚገኘው አማካዩ ከኳስ ውጭ የተጋጣሚ ተጫዋቾች ላይ ጫና በማሳደር ሆነ ቡድኑ ከኳስ ጋር ሲሆን እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥ እና ሳጥን ውስጥ እንቅስቃሴዎችን ለመጨረስ በመገኘት ረገድ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን ከወዲሁ ለቡድኑ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር መቻሉ በባህር ዳር ቤት ከአምና አንፃር ፍፁም የተሻለ ጊዜ እያሳለፈ እንደሚገኝ ማሳያ ነው።
በነገው ጨዋታ በባህር ዳር ከተማዎች በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት በረከት ጥጋቡ እና ኦሲ ማውሊ ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ሜዳ የሚመለሱ ሲሆን የአምበላቸው ያሬድ ባየህ እና አደም አባስ ግን ቀለል ያለ ልምምድ ቢጀምሩም ለነገው ጨዋታ የመድረሳቸው ጉዳይ አጠራጥሯል።
ሁለቱም ቡድኖች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከተጋጣሚዎቻቸው አውንታዊ ውጤትን ይዘው ለመውጣት በግልፅ የሚታዩ ግቦችን አስቀምጠው ተጋጣሚዎቻቸውን በሜዳው የላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ጫና ውስጥ በመክተት ከሚሰሯቸው ስህተቶች ለማትረፍ ሲሞክሩ የተመለከትን ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በምን መልኩ ይቀርባሉ የሚለው ይጠበቃል።
በከፍተኛው የሊግ ዕርከን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ጨዋታችን ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች አርባምንጭ ከተማዎች በሁለቱም ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን የነገውን ሦስተኛ ግንኙነታቸውን ሚካኤል ጣዕመ በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ፋሲል ከነማ
አስደናቂ ግስጋሴ ላይ የሚገኙትን ሀዲያ ሆሳዕናዎችን እየተንገራገጩ ከሚገኙት ፋሲል ከነማዎች ጋር የሚያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።
የውድድር ዘመኑ ሲጀመር ሁለቱ ቡድኖች በ7ኛው የጨዋታ ሳምንት ሲገናኙ በዚህ መልኩ ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ አናት ፋሲል ደግሞ በሊጉ ወገብ በታች ሆነው ይገናኛሉ ብሎ መገመት ትንሽ አስቸጋሪ ይመስል ነበር። ነገርግን አሁናዊው እውነታ ግን ሀዲያ ሆሳዕና 3ኛ ደረጃ እንዲሁም ፋሲል ከነማ ደግሞ 10ኛ ደረጃ ላይ ሆነው ይገናኛሉ።
በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች አዲሱን የውድድር ዘመን የጀመሩበት መንገድ አድናቆት የሚቸረው ነው። በክረምቱ የዝውውር መስኮት እንደ ቀደሙት ዓመታት ያን ያህል ትልልቅ ስሞችን ወደ ስብስባቸው ያልቀላቀሉት ሆሳዕናዎች ሊጉን በሽንፈት ቢከፍቱም በተከታታይ ባስመዘገቧቸው አስደናቂ ውጤቶች አሁን ላይ በአስራ ሦስት ነጥቦች በሰንጠረዡ በ3ኛ ደረጃ ይገኛሉ።
በሊጉ የእስካሁኑ ጉዞ 3 ግቦችን ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ ከወላይታ ድቻ ጋር በጣምራ የሊጉ ምርጡ መከላከል ባለቤት ሲሆኑ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያስፈረሙት አይቬሪኮስታዊው የግብ ዘብ ፔፕ ሰይዱ ኒዲያዬ ደግሞ በሦስት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር በመውጣት በሊጉ ከበረከት አማረ ቀጥሎ በ2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በህብረት የሚከላከለው ቡድኑ በዚህ የመከላከል ጥንካሬ ታግዞ በሊጉ መልካም አጀማመር እያደረገ ይገኛል። በማጥቃቱ ረገድ ብዙ የተጠበቀበት የቡድኑ የአጥቂ መስመር እስካሁን ለቡድኑ በቂ አገልግሎት መስጠት አልጀመረም። ቡድኑ በስብስቡ ከያዛቸው የአጥቂ ተሰላፊዎች እስካሁን ሁለት ግብ ብቻ ማግኘቱ ሪችሞንድ አዶንጎን እና ባዬ ገዛኸኝን ለያዘው አጥቂ መስመር በቂ የሚባል ቁጥር አይደለም። በአንፃሩ የቡድኑ የአማካይ ክፍል ይህን ክፍተት በሚገባ እየደፈነ ይገኛል። ሆሳዕና እስካሁኑ በሊጉ ካስቆጠራቸው ዘጠኝ ግቦች ስድስቱ በአማካይ ተጫዋቾች የተመዘገቡ መሆናቸው በጥንካሬነት የሚነሳ ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሊጉ በወጥነት በሰንጠረዡ አናት ሲፎካከሩ የምናውቃቸው ፋሲል ከነማዎች እርግጥ ገና የውድድር ዘመኑ ጅማሬ ላይ ቢገኝም የዘንድሮ አጀማመራቸው አመርቂ አልሆነላቸውም። አምሰት ጨዋታዎችን እስካሁን ያደረገው ቡድኑ በ7 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ዕድሎችን በመፍጠር ሆነ ግቦችን በማስቆጠር ረገድ እየተቸገረ የሚገኘው ቡድኑ ከፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ወጥ የሆነ ግልጋሎትን ለማግኘት ተቸግሯል። የውድድር ዘመኑን በፍቃዱ ዓለሙ ሁለት ግቦች ታግዘው የጀመሩት ፋሲሎች በቀጣይ በነበሩት ጨዋታዎች የፍቃዱ ዓለሙን መቀዛቀዝ ተከትሎ አማራጮችን እያሰሱ ይገኛሉ። በመጨረሻው ጨዋታም ጉልላት ተሾመን በፊት አጥቂነት እስከ ማስጀመር የደረሰ የፊት መስመር ውስንነት እየተስተዋለባቸው ይገኛል።
ከማጥቃቱ ጀርባ በነፃ ስምንት ቁጥር ሚና የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የነበሩትን ሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መለዮን በዘንድሮው የውድድር ዘመን በጉዳት ምክንያት ማጣመር ያልቻሉት ፋሲሎች በተቀሩት ድሬዳዋ ከተማ ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ውጤቶችን በመሰብሰብ የውድድር ዘመኑ ጉዟቸውን መስመር ማስያዝ የግድ ይላቸዋል።
ዐፄዎቹ ነገም የሱራፌል ዳኛቸው እና ሀብታሙ ተከስተን አገልግሎት በጉዳት የማያገኙ ሲሆን አማካዩ ይሁን እንዳሻውም ከጉዳት መመለስ አጠራጣሪ ሆኗል።
ከዚህ ቀደም በአራት ጨዋታዎች በሊጉ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ፋሲል ከነማዎች ሁለቱን ጨዋታዎች በበላይነት ሲቋጩ ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በነጥብ መጋራት የተጠናቀቁ ናቸው። ምሽት 1 ሰዓት ሲል የሚጀምረውን አምስተኛ ግንኙታቸውን ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።