በሰሞነኛው ወቅታዊ የአየር ሁኔታ የድሬዳዋ ስታዲየም መጫወቻው ሜዳ አመቺ ባለመሆኑ ቀጣይ ጨዋታዎች ተራዝመዋል።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከስድስተኛ ሳምንት ጀምሮ ተረኛ አስተናጋጅ በሆነችው ድሬደዋ ከተማ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ሆኖም ታዲያ ከሰሞኑን በተደጋጋሚ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በከተማዋ እየጣለ መሆኑን ተከትሎ የመጫወቻው ሜዳ ለጨዋታ ምቹ ሳይሆን ቀርቷል።
የፕሪሚየር ሊጉ አክስዮን ማህበር የውድድር ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ትናንት እኩለ ሌሊት ባወጣው መረጃ መሠረት የ7ኛ ሳምንት ቀሪ 4 ጨዋታዎች በድሬዳዋ አየር ሁኔታ ምክንያት የመጫወቻ ሜዳው ለማጫወት ምቹ ስላልሆነ ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘሙ መሆኑን ገልጿል። በዚህም መሠረት የተራዘሙ ጨዋታዎች ቅዳሜ 10:00 አርባምንጭ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ እና 01:00 ሀዲያ ሆሳዕና ከ ፋሲል ከነማ እንዲሁም እሁድ10:00 አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና እና 01፡00 ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታዎች መራዘማቸውን ተናግሯል። አወዳዳሪው አካል ጨዋታዎቹ ስለመራዘማቸው እንጂ መቼ ጨዋታዎቹ እንደሚደረጉ የገለፀው ነገር የለም።