በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በተከታታይ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የፈፀመው ሀዋሳ ከተማ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሰባት ነባሮችን ውልም አድሷል፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነው ሀዋሳ ከተማ በዘንድሮ የ2015 የውድድር ዘመን ራሱን ለማጠናከር በአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረ መሪነት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኝ ሲሆን አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረምም ስብስቡን አጠናክሯል፡፡
የቀድሞው የመከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማ አማካይ ኤልሳቤት ብርሀኑ ፣ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ አዳማ እና ጌዲኦ ዲላ የተጫወተችው የመስመር አጥቂዋ ጤናዬ ወመሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማዋ የመስመር አጥቂ በሻዱ ረጋሳ እና የአርባምንጭ ከተማዋ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች መቅደስ ብርሀኑ የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎች መሆን ችለዋል፡፡
ክለቡ ከአዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪም ተከላካዩዋ ቅድስት ዘለቀ እና አጥቂዋ ረድኤት አስረሳኸኝን ጨምሮ ፀሀይነሽ ጁላ ተከላካይ ፣ መሀሪ በቀለ አጥቂ ፣ በረከት ጴጥሮስ አማካይ ፣ ታሪኳ ጴጥሮስ እና ማሳንቱ ኤቢሶን ውል ማራዘሙ ታውቋል። በተጨማሪም ከርቲና ፊላ የተባለች ታዳጊንም ከታችኛው ቡድኑ ወደ ዋናው ስብስብ ቀላቅሏል።