ዛሬ ረፋድ በተለያዩ ጉዳዮች ስብሰባ የተቀመጠው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የስራ አመራር ቦርድ ቡድን መሪ እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኝን መሾሙ ታውቋል።
በወቅታዊ የቡድኑ ጉዳይ ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገው የክለቡ ስራ አመራር ቦርድ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በስራው ገበታ እንዲቀጥል እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ መሐመድ የተስፋ ቡድኑን እንዲያሰለጥን ማድረጉን መዘገባችን ይታወቃል። ቦርዱ በተጨማሪም የክለቡ ቡድን መሪ የነበሩትን አቶ በድሉ ኃይለሚካኤል ያነሳ ሲሆን በምትካቸውም ቀደሞ በተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት የሰራውን ኤርሚያስ ተፈሪን በቦታው ሾሟል።
የወረቀት ጉዳዮች ያልተጠናቀቀ በመሆኑ እንጂ የቀደሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለ ታሪክ ተጫዋች እና አሰልጣኝ እንዲሁም በተለያዩ ክለቦች ያሰለጠነው ቅጣው ሙሉ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ በመሆን መሾሙንም የዝግጅት ክፍላችን ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። በዛሬው ዕለትም በክለቡ ቢሮ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና አዲስ ከተሾሙቱ ቡድን መሪ ኤርሚያስ ተፈሪን እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ ጋር በመሆን ውይይት ማድረጋቸውንም አውቀናል።