ከቀናት በፊት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታድየም መጫወቻ ሜዳ ላይ ባደረሰው ጉዳት ምክንያት አራት ጨዋታዎችን በይደር ያሳለፈው ፕሪምየር ሊጉ ነገ ሲቀጥል ችግሩ በዛው እንዳይዘነጋ ስንል ቀጣዩን ፅሁፍ አዘጋጅተናል።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች የምስል መብቱን በገዛው ሱፐር ስፖርት በቀጥታ መተላለፍ ከጀመረ ሦስተኛ ዓመቱን ይዟል። መተላለፉም ሊጉ ላይ ብዙ አዎንታዊ ነገሮችን ፈጥሯል። ለአብነት ያህል ተጫዋቾች በትላልቅ ሊጎች ዐይን ውስጥ እንዲገቡ ዕድሎችን መፍጠሩ ፣ ክለቦች ከቀጥታ ስርጭት ሽፋን በዓመቱ መጨረሻ ላይ ገቢ ወደ ካዝናቸው ማስገባታቸው እና የጨዋታ ምስሎችን በማየት የጨዋታ መንገዳቸውን ለማስተካከል ትልቅ አጋዥ መሆኑ ከብዙ በጥቂቱ ይነሳሉ።
ሊጉ በተጠበቀበት የዕድገት ፍጥነት እንዳይሄድ ዕክል እየፈጠሩ ያሉ ነገሮችም በሰፊው እየተስተዋሉ ነው። ከሁሉም በፊት አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ ባለመቻላችን ብሔራዊ ቡድኑ እና የሀገራችን ተወካይ ክለቦች ተሰደው እንዲጫወቱ ምክንያት የሆነው የመጫወቻ ሜዳ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ እግርኳስን እንደጀመረችበት ዓመት ዘመናዊ ስታዲየሞች አለመገንባቷ ግርምትን ይጭራል። በርካታ መስፈርቶችን ማሟላት የተሳናቸው ስታድየሞቿ የመጫወቻ ሜዳ ችግራቸውም ከሌሎች ጉድለቶች ጋር አብሮ ሲንከባለል እዚህ ደርሷል። ይኸው ችግር በተመረጡ ስታዲየሞች ላይ ብቻ እየተደረገ ባለው የሀገሪቷ ትልቁ ሊግ ላይ ይበልጥ ተፅዕኖ መፍጠሩም አልቀረም። የዘንድሮው ውድድርም ከተጀመረ በሰባተኛው ሳምንት ላይ ደርሶ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መዝነቡን ተከትሎ በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የመጫወቻ ሳር ላይ ባጋጠመ ብልሽት መደረግ ከሚገባቸው ስምንት ጨዋታዎች አራቱ እንዲራዘሙ አስገድዷል። ውድድሩ ወደ ምስራቅ ከመጓዙ አስቀስሞ ስታዲየሙ ውስጥ ለመልሶ ምልከታ የሚረዱ ስክሪኖች እና ዲጅታል ማስታወቂያዎች መገጠማቸው የሊጉ ተመልካች ብዙ እንዲጠብቅ ቢያደርጉትም የሜዳው ገፅታ በቀናት ልዩነት እንዳልነበር መሆኑ አሁንም ባለንበት እየረገጥን እንደሆነ ዳግም አሳብቋል።
እርግጥ የመጫወቻ ሜዳን በወጥነት ለጨዋታ ምቹ አድርጎ ማዘጋጀት በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም እንደታየው የዲጅታል የማስታወቂያ እና መልሶ ማሳያ ስክሪኖችን ከመትከል በላይ የገንዘብ እና የሰው ኃይል ሊጠይቅ ይችላል። አንድ ጊዜ ተተክለው በመጠነኛ ክትትል ስራቻውን እንዲቀጥሉ ማድረግ የሚቻል መሆኑ መሰል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መተግበር ከአንገብጋቢው የሜዳ ይዘት ጋር ሲነፃፀር ቅንጦት ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል። የድሬዳዋ አዲስ መልኮች ሆነው ብቅ ያሉት ቴክኖሎጂዎች በግንባታ ላይ ሳሉ የፈጠሩት አዎንታዊ ዜና ውድድሩ ወደ ከተማዋ ሄዶና በተግባር ውለው ሲታዩም የቀጠለ ነበር። ሁኔታው በበጎ መወሰዱ ሜዳው ላይ ቅሬታ እንዳይሰማ የአስታየት ሰጪዎችን ሀሳብ የሰወረም ይመስላል። በቀጣይ ቀናት በከተማዋ መጣል የጀመረው ዝናብ ግን ዓይኖች ሁሉ ከአዲሶቹ ቴክኖሎጂዎች ይልቅ መጫወቻ ሜዳው ላይ እንዲያተኩሩ ያስገደደ ሆኗል። ሁኔታው ተባብሶ ውድድሩን እስከማቋረጥ ሲደርስ ደግሞ አፎች ሁሉ ቴክኖሎጂዎቹን ከሜዳው ጋር በማነፃፀር ስለ ቅደም ተከተል በማውራት የወትሮው ከችግሮች በኋላ የሚመጣ ትንተና ላይ ተጠምደው ሰንብተዋል።
በሁኔታው ላይ የቅደም ተከተል ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ቢሆንም በስታድየሙ ላይ በሳምንታት ልዩነት የተሰጡ አስተያየቶች ግን ሁኔታውን ከድሬዳዋ አልፎ አጠቃላይ የሀገራችን እግርኳስ ምልከታ ችግር አድርገን እንድንወስደው ይጋብዛል። በመሰረተ ልማትም ሆነ በአጠቃላይ በእግርኳሱ ውስጥ ባሉ ዝርዝር ጉዳዮች ሁሌም ችግሮቻችንን የሚያጋልጡ ፈተናዎች እስኪመጡ ድረስ ራሳችንን ብቁ አድርገን የመቁጠር አባዜ እንዳለብን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ አጋጣሚ ነው ማለት ይቻላል። ቡድኖች ሽንፈት እስኪያገኛቸው የሰሞንኛ ድላቸውን ምክንያት በአግባቡ ባለማወቅ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንደሚያስቡት ፣ ተጫዋቾች ሁለት ወይ ሦስት ሳምንታት ጥሩ ስለተንቀሳቀሱ ብቻ ትልቅ ዕድገት ላይ እንደሚገኙ እንደሚያስቡት ወይም አሰልጣኞች በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ቡድናቸው ባሳየው ውጤት እንደሚሞካሹት ሁሉ ሜዳዎችም ከባድ ፈተና እስኪያገኛቸው ድረስ በቴሌቪዥን ስክሪኖች ላይ አረንጓዴ መልክ ተላብሰው በመታየታቸው ብቻ ገበናቸው ይሸፈናል። እንደ ሰሞንኛው የድሬዳዋ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሲከሰት ግን የተሰራላቸው ሥራ እጅጉን ከበቂ በታች እንደነበር ያሉበት ወቅታዊ ሁኔታም ‘ኢንተርናሽናል’ የሚል ቅፅል በስማቸው ኋላ ላስከተሉ ስታዲየሞች የማይመጥኑ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።
የእግርኳስ አመራሮቻችንም ሆኑ የተቺዎቻቸው ዕይታ ወቅታዊ ሁነቶች ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ ለዚህ ህመም ዋነኛው መንስኤ ነው። ወቅቱን እንዳልጠበቀው ዝናብ ያልታሰቡ ፈተናዎች እስኪጋረጡ ድረስ በመሪነት ኃላፊነት ላይ ያሉ የእግርኳሱ ሰዎችም ሆኑ በሌሎች ዘንድ ስለመጫወቻ ሜዳው ሲነሳ አልተሰማም። በድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ውድድሩ ወደ አዲስ ስታዲየሞች ባመራ ቁጥር “የመጫወቻ ሜዳው ላይ የማሻሻያ ስራ ተሰርቷል” የሚለው ሀረግ ከመሰማቱ ውጪ ‘ምን ምን ጉዳዮች በምን በምን መጠን ተሰሩ ?’ የሚለው ነጥብ ማብራሪያ ሲሰጥበት አይስተዋልም። እንደዝናቡ ድንገተኛ ዕክል ካልተፈጠረ እና ውድድሩ ከተገባደደ ደግሞ እንደስኬት ተወስዶ ሜዳው ሊሞካሽም ይችላል። ይህ እውነታ ዕይታችን እስከምን ድረስ እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በአዲስ አበባ ስታዲየምም ሆነ በክልል ስታዲየሞች ተዘዋውሮ ለተመለከተ ደረጃቸው የወረዱ ሜዳዎችን ማየት ብርቅ አይደለም። ስለሜዳ ጥራት በሰፊው ማውራት የጀመርነው ግን የዲ ኤስ ቲቪ ቀጥታ ስርጭት ከመጣ በኋላ ገመናችን ለዓለም መጋለጡ ሲቆጠቁጠን ብቻ ነው። ይህ ሁለተኛ እውነታም ሌላኛው የተንሸዋረረ እይታችን ማስረጃ ነው። እግርኳስ እስካለ እና ውድድር አለን ብለን እስካሰብን ድረስ ከሊጉ ጅማሮ አንስቶ ስለሜዳ ጥራት ብናስብ ኖሮ ዛሬ 25ኛ የውድድር ዓመቱ ላይ የሚገኘው ሊጋችን ስሙ ከዚህ ችግር ጋር ባልተያያዘ ነበር። አሳሳቢው ግን ይህ አለመሆኑ ሳይሆን አሁንም የቅርብ የቅርቡን ማሰባችን ነው።
አሁንም ሰሞንኛው የድሬዳዋ ሜዳ መጨቅየት ችግሩ ጊዜያዊ መፍትሄ ተሰጥቶት ውድድሩ ነገ ሲቀጥል አይበለው እና ሌላ ዝናብ እስኪጥል ድረስ የሜዳ ጉዳይ ተዘንግቶ መቆየቱ የሚቀር አይመስልም። የሚበጀን ግን ሀገራችን ውስጥ የትኞቹም ሜዳዎች ጥራት እንደሌላቸው እና ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልጋቸው ማመኑ ነው። ከወር ባልዘለለ ጊዜ ውስጥ 40 ጨዋታ ለማስተናገድ የተገደዱ ሜዳዎቻችን በበቂ ሁኔታ ቢሰናዱ ራሱ ይህንን ጫና መቋቋም ይችላሉ ወይ ? የሚለው ጥያቄ በራሱ አነጋጋሪ ቢሆንም ቢያንስ ግን ባሉበት ደረጃቸውን ብቁ ማድረግ ለነገ የማይባል ሥራ ነው።
ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ ስታዲየሞቹን ከሚያስተዳድሩት የከተማ አስተዳደሮች በላይ የፕሪምየር ሉጉ አክሲዮን ማህበር ይበልጥ ራሱን ተጠያቂ ማድረግ ይገባዋል። የሜዳዎቹ ጥራት የካምፓኒው የገቢ ምንጭ ከሆነው የቴሌቭዢን ሽፋን ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለው እንደመሆኑ ከግምገማ እና ከቁጥጥር ባለፈ በቀጥታ ግንባታው ላይ ባይሳተፍ እንኳን የሜዳ ችግር ከፍ ያለ ትኩረት እንዲያገኝ እና የመፍትሄው አቅጣጫው ምን መምሰል እንዳለበት በማመላከት ጭምር ስታዲየሞቹን በባለቤትነት ከሚያስተዳድሩ አካላት ጋር አብሮ መስራት የሚገደድበት ጊዜ ላይ ደርሷል።
የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን ወጣ ብሎ ከማየት ጀምሮ በሜዳ ግንባታም ሆነ ወጥ የሆነ ክትትል የማድረግ አቅም ያላቸውን ድርጅቶች ፈልጎም ይሁን አወዳድሮ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ከፍ ሲልም የእውቀት ሽግግር በመፍጠር በሂደት ወደ ሀገር ውስጥ ተቋሞች በማስተላለፍ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ይህንን ርዕስ ለመዝጋት ቀዳሚውን እርምጃ መራመድ እና የማስተባበር ኃላፊነቱን መውሰድ ከውጤቱ ዋነኛ ተጠቃሚ ከሚሆነው የሊግ አስተዳደር ይጠበቃል።
ይህ መሆን ካልቻለ እና ችግሩን ብቻ እያወራን መፍትሄውን ከሌላ አካል ብቻ ከጠበቅን የብሔራዊ ቡድናችን ስደት ሳያንስ ሜዳዎቹ ለሀገር ውስጥም ውድድር ብቁ አለመሆናቸው የቀጥታ ስርጭት ሽፋናችንንም እንዳያሳጣን ያሰጋል። በመሆኑም ይህ ችግር ቢያንስ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ፈር እንዲይዝ ከአሁኑ ሰፊ ዕቅድ ተይዞ መንቀሳሰቅስ መጀመር የግድ ይላል። ሜዳዎቻችንም በውድድር መክፈቻ ላይ አምሮባቸው እንዲታዩ እንደሚደረገው ሁሉ በየትኛውም የዓየር ሁኔታ ውስጥ በቂ ግልጋሎት የሚሰጡ ሆነው እንዲገኙ ጊዜያዊ መፍትሄዎችን ትተን የማይቀርልንን የስር ነቀል ሥራ ‘ሀ !’ ብለን ብንጀምር ይበጃል እንላለን።