👉”የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ሊግ ነው። እንደ ፔፕ፣ ክሎፕ እና ቬንገር የኳስ ቅብብል ላይ ትኩረት የሚያደርጉ አሰልጣኞች የሚበዙበት ሊግ ነው”
👉”እኔ ሁሌ ሜዳ ላይ ለማድረግ የምፈልገው ቀላሉን እና መሠረታዊውን ነገር ነው”
👉”በቀን ውስጥ 5 ጊዜ የምፀልይ ሰው ነኝ ፤ ሁሌ ፈጣሪዬን መቅረብ ነው የምፈልገው”
👉”አብዛኞቹ አዲስ አዳጊ ክለቦች በሊጉ መቆየትን ቀዳሚ እቅዳቸው ቢያደርጉም እኔን ጨምሮ ሁሉም ተጫዋቾች በራሳችን ከተማመንን ለሊጉ ዋንጫ የማንፎካከርበት ምንም ምክንያት የለም”
ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና ኩማሲ ከተማ ዞንጎ ማኅበረሰብ የተገኘው የዛሬው እንግዳችን ባሲሩ ኦማር ገና ዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በኢትዮጵያ መድን መለያ ቢተዋወቅም እጅግ ድንቅ አጀማመር በማድረግ የብዙዎች ልብ ውስጥ መግባት ችሏል። በርካታ ጋናዊያን የእግርኳስ ተጫዋቾች በሚፈልቁባት ኩማሲ የተወለደው ቁመታሙ አማካይ እንደ አብዛኛው እግርኳስ ተጫዋች ገና በጨቅላነቱ የእግርኳስ ፍቅር ውስጡ እንዳደረ ይናገራል። ባሲሩ በ8 ዓመቱ ፍቅሩን ለማስታገስ ባገኘው አጋጣሚ እግርኳስን መጫወት ቢጀምርም ወላጅ እናቱ እና አጠቃላይ ቤተሰቡ በቀለም ትምህርት እንዲገፋ ፍላጎት ስለነበራቸው እገዛ አላደረጉለትም ነበር። በተለይ በአሁኑ ሰዓት በቻይና የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቱን እየተከታተለ እንደሚገኘው ወንድሙ እና ኤሌክትሪካል ኢንጂነር ፣ የሒሳብ እና ሶሻል መምህር እንዲሁም ነርስ የሆኑትን የአክስት እና አጎት ልጆቹን የትምህርት መንገድ እንዲከተል ጫና ቢፈጠርበትም እርሱ ግን ህልሙን ከመከተል ወደኋላ አላለም። የሁለተኛ ደረጃ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም ለዌስት አፍሪካ አካዳሚ የመጫወት ዕድሉን አግኝቶ ሙሉ ለሙሉ ፊቱን ወደ እግርኳስ ዓለም አዞረ።
ባሲሩ በዌስት አፍሪካ አካዳሚ ራሱን እያጎለበተ ከመጣ በኋላ ገና አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላው በፍጥነት ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ ወደ ዋናው ቡድን አደገ። ከ2014-2018 ድረስ በዋናው ቡድን በጋና ከፍተኛ የሊግ ዕርከን እየተጫወተ ከቆየ በኋላ 2018 ላይ ለሀገሪቱ ኃያል ክለብ አሳንቴ ኮቶኮ ፊርማውን አኖረ። በኮቶኮም በብዙ የጋና የስፖርት ቤተሰብ ዓይን ውስጥ ከመግባቱ ባለፈ ለጋና ከ23 ዓመት በታች እና የቻን ብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት የመስጠት ዕድል አገኘ። ከዚህ ባለፈም በክለብ አህጉራዊ ውድድሮች ከኮቶኮ ጋር በኮንፌደሬሽን ዋንጫ እስከ ምድብ ድልድል ድረስ መጓዝ ችሎ ነበር። ከዛም 2020 ላይ ካሬላ ለተሰኘው ቡድን ለሁለት ዓመታት ተጫውቶ የተሳካ ቆይታን ያደረገ ሲሆን በተለይ ዓምና እርሱም እንደሚለው እጅግ ድንቅ ጊዜን አሳልፎ ከጋና አልፎ እስከ አውሮፓ ድረስ የናኘ ስም በማግኘት የበርካታ ክለቦች የእናስፈርምልህ ጥያቄ ማስተናገድ ያዘ። እርሱ ግን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ምርጫው እንዳደረገ በመግለፅ ለአዲስ አዳጊው ኢትዮጰያ መድን የአንድ ዓመት ውል በመፈረም የእግርኳስ ህይወቱን በኢትዮጵያ ለመቀጠል ወደ ሀገራችን መጣ።
ተጫዋቹ ከመኖሪያ ፍቃድ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ መዘግየት የመጀመሪያዎቹን ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ማድረግ ባይችልም ከሦስተኛው የጨዋታ ሳምንት ጀምሮ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የማይጠፋ ተጫዋች ሆኗል። ከኳስ ጋር በምቾት መጫወት የሚችለው ባሲሩ የቡድኑን የአማካይ መስመር ብርታት ከማሳደጉ በተጨማሪ በመከላከሉ እና በማጥቃቱ ትልቅ አበርክቶ እየሰጠ ይገኛል። እስካሁን በ432 ደቂቃዎች ሁለት ግቦች እና አንድ አሲስት ያስመዘገበው ተጫዋቹ የተሳካ ስለሚመስለው አጀማመሩ እና የእግርኳስ ህይወቱን የተመለከተ ቆይታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አድርጓል።
በክረምቱ ከተፈፀሙ ዝውውሮች እስካሁን ባየነው የተሳካ ዝውውር ከሚባሉት ውስጥ ያንተ ይጠቀሳል። ከሀገርህ ጋና ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ልትመጣ ቻልክ?
“ከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን መጨረሻ በኋላ ከኢትዮጵያ አንድ የተጫዋቾች ወኪል ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ለመጫወት ፍላጎት እንዳለኝ ሲጠይቀኝ ነበር። እኔም እሺ ብዬው ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ በቂ እውቀት እንደሌለኝ ግን ነገርኩት። ነገርግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም በተለያዩ አህጉራዊ ውድድሮች ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በተወሰነ መልኩ በተለይም ከጋና ጋር ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ተመልክቻለሁ። በእነዚህም ጨዋታዎች ምንም እንኳን ብሔራዊ ቡድኑ በጋና ሽንፈት ቢያስተናግድም ኳስ መስርቶ ኳስ ተቆጣጥሮ ጥሩ ኳስ እንደሚጫወት አስተውል ነበር። ከዛ ጥያቄው ሲመጣልኝ ኢትዮጵያ የተጫወቱ ጓደኞቼ ጋር እየደወልኩ ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ ማጠያየቅ ጀመርኩ። ከእነሱ የሰማሁት ነገር የሊጉ የጨዋታ መንገድ ከእኔ ጋር እንደሚስማማ እና ቴክኒካል የሆነ ሊግ ስለመሆኑ ነበር። እኛ ጋር ጋና ከቴክኒክ ባለፈ ፍጥነት ፣ ጥንካሬ እና ተክለ ሰውነት ላይ መሰረት ያደረገ እግርኳስ ነው በብዛት የሚተገበረው ፤ በመሆኑም እነሱም ወደዚህ ብትመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይበልጥ ቴክኒክ እንደሚፈለግ ስኬታማ ትሆናለህ ይሉኝ ነበር። እውነት ለመናገር በቅድሚያ ወኪሉ ሲያናግረኝ ብዙ ፍላጎት አልነበረኝም ምክንያቱም ጓደኞች በደንብ ስለ ሊጉ መጠየቅ ነበረበኝ። ከዛ ባለፈም በርከት ያሉ ፍላጎቶች የአውሮፓ ክለቦችን (ሰርቢያ ፣ አልባኒያ ፣ ቆጵሮስ፣ መቄዶንያ) ጨምሮ ከመካከለኛው ምስራቅ ጭምር ይቀርብልኝ ስለነበር በግሌ ተወዛግቤ ነበር። ከኢትዮጵያ የነበረው ወኪል ግን በጣም በተደጋጋሚ እየደወለ ይጠይቀኝ ነበር። ታድያ በዚህ ወቅት ይህ ወኪል ለምን በዚህ ደረጃ እኔን ሊያወራ ፈለገ የተወሰነ ያየብኝ ነገር ሊኖር ይችላል ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። እሱም ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ ውጤታማ ልሆን እንደምችል ይነግረኝ ነበር። በእሱ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ሊግ ለእኔ ትክክለኛው ምርጫ እንደሚሆን ይነገረኝ ነበር። ከሌሎች ወኪሎች በኩል ግፊቶች ቢኖሩም በፀጥታ ችግሮች እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የሌሎች ሀገራት ጥሪዎች ብዙ ሳያማልሉኝ ቀሩ። በእግርኳስ ሁሌም ቢሆን ሰላም የሚሰጥህ እንዲሁም ደስተኛ ሊያደርግህ የሚችለውን ነገር መምረጥ ለአዕምሮህ ሰላም አግኝተህ በተሻለ መልኩ እንድትጫወት ያግዛል ፤ በመሆኑም እኔም ኢትዮጵያን ከዚህ አንፃር መርጫለሁ።”
ኢትዮጵያን እንዴት አገኘሀት ታዲያ…?
“እውነቱን ለመናገር ወደ ኢትዮጵያ ከመጣው በኋላ አንድም መጥፎ ነገር አላየሁም። እንደ ቅሬታም የማነሳው ምንም ነገር አልገጠመኝም። ሀገራችሁ በጣም አሪፍ ሀገር ናት። እስካሁን ያየኋቸው ከተሞችም ሰላማዊ እና የፍቅር ናቸው። ማኅበረሰቡም እጅግ በጣም ተግባቢ እና ሰው ወዳድ ነው። እስካሁን ያለው ለእኔ በጣም ተመችቶኛል።”
እንደነገርከን ከአውሮፓ ሁሉ የቀረቡልህን ጥያቄዎች ውድቅ አድርገህ ወደ ኢትዮጵያ መጥተካል። ታዲያ የኢትዮጵያን ፕሪምየር ሊግ እንዴት አገኘከው? እንደሰማከው ላንተ አጨዋወት ተስማሚ ነው? ጓደኞችህ እንዳሉትስ ኳስን መሰረት ያደረገ አጨዋወት የሚዘወተርበት ሊግ ነው?
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ሊግ ነው። ቴክኒካሊ እና ታክቲካሊ ጥሩ የሆነ ሊግ ነው። ከምንም በላይ በርካታ ቴክኒካሊ የተሻለ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች አይቻለው። ደግሞም የሚገርመው አብዛኞቹ የሊጉ ቡድኖች ከኋላ መስርተው መውጣት የሚፈልጉ እና እንደ ፔፕ፣ ክሎፕ እና ቬንገር የኳስ ቅብብል ላይ ትኩረት የሚያደርጉ አሰልጣኞች የሚበዙበት ሊግ ነው። ይሄ ለሊጉም ሆነ ለብሔራዊ ቡድኑ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል። ከኳስ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚፈልጉ ቡድኖች የሚበዙበት ሊግ ስለሆነ እኔ በግሌ ተመችቶኛል። ሜዳ ላይ ካለው ነገር በዘለለ ደግሞ ሊጉ የቀጥታ የቴሌቭዢን ስርጭት ያገኛል። ማስታወቂያዎችንም አልፎ አልፎ እመለከታለው። ይሄ ትልቅ ነገር ነው። እኔም የዚህ ትልቅ ሊግ አካል በመሆኔ ደስታ ይሰማኛል።”
አይደለም የሌላ ሀገር ተጫዋቾች እዚሁ የሚገኙ ተጫዋቾችም አዲስ ክለብ ሲቀይሩ ያንን ከባቢ ለመልመድ ጊዜ ይፈጅባቸዋል። አንተ ግን ክለብህን፣ ሊጉን እና ሀገሩን ቶሎ ተላምደሀል። ይህ እንዴት ሆነ?
“ምናልባት የኢትዮጵያን ሊግ በቶሎ እንድላመድ ያደረገኝ የአጨዋወት መንገዱ ይመስለኛል። ምክንያቱም እኔ ኳስን መሰረት ያደረገ አጨዋወት ነው መከተል የምፈልገው። ክለቤ መድንም ኳስን መሠረት ያደረገ አጨዋወት ነው የሚከተለው። እኔ ከአካዳሚ ጀምሮ ኳስን ማንሸራሸር ላይ ያተኮረ ስልጠና ወስጄ ነው የተገራሁት። በእግርኳስ እድገቴም የማጥቃት ፍላጎት ያላቸው እና ኳስን ማንሸራሸር በሚወዱ አሠልጣኖች ነው የሰለጠንኩት። እዚህም ከመጣው በኋላ ይሄ ነው የገጠመኝ። በእግርኳስ ጥሩ እንድትጫወት ቀላሉን እና መሰረታዊውን ነገር መከወን ነው ያለብህ። በእንቅስቃሴ ውስጥ ትክክለኛውን ነገር በትክክለኛው ሰዓት ነው ማድረግ ያለብህ። እኔ ሁሌ ሜዳ ላይ ለማድረግ የምፈልገው ቀላሉን እና መሠረታዊውን ነገር ነው። ኳስን ማቀበል ባለብኝ ጊዜ አቀብላለው ፤ መግፋት ባለብኝ ሰዓት እገፋለው እንዲሁም መያዝ ባለብኝ ወቅት እይዛለው። ይሄ በእግርኳስ መሰረታዊ ነገር ነው። የትኛውም ተጫዋች ይሄንን ማድረግ ከቻለ ውጤታማ መሆን ይችላል። እኔም ይሄንን በቻልኩት መጠን ስለማደርግ ነው የኢትዮጵያን ሊግ በቶሎ የለመድኩት።”
ራስህን እንዴት ነው ጥሩ ተጫዋች ለማድረግ የምታበቃው?
“እንዳልኩት እኔ ሁል ጊዜ ቀላሉን እና መሰረታዊውን ነገር ነው ማድረግ የምፈልገው። ቀላሉን ነገር በትክክለኛው ጊዜ እና ቦታ ለማድረግ ነው ሁሌ ጥረቴ። እኔ የተሟላው ተጫዋች አይደለሁም። ግን ሁሌ የምለውን ነገር ለማሻሻል እጥራለው። ፈጣሪ ፈቅዶ ከጎበዝ አሠልጣኞች ጋር ሰርቻለው። እነሱም የሚነግሩኝ ይሄንን ነው። ብዙ ጊዜዬን ደግሞ የእግርኳስ ጨዋታዎችን በማየት አሳልፋለው። ከማየው ነገር ደግሞ ትምህርት እወስዳለው። ከዚህ በተጨማሪ ልምምድ ሜዳ ላይ ድክመትህን ለመቅረፍ እና ጠንካራ ጎንህን ለማዳበር መልፋት ወሳኝ ነው።”
ገና በጊዜም ቢሆን ብዙዎች ጥሩ ተጫዋች እንደሆንክ ሲናገሩ ይደመጣል። አጨዋወትህም በብዙዎች ተደንቋል። ይሄ በአጭር ጊዜ እንዴት የሆነ ይመስልሀል?
“ብዙ ሰው አጨዋወቴን ስለወደደው ደስ ብሎኛል። በጣምም አመሰግናለሁ። ይሄ ቀላል ነገር አይደለም። ጨዋታን ማንበብ አንደኛው ብቃቴ ነው። እግርኳስ ስትጫወት ሁል ጊዜ አንቲሲፔት ማድረግ አለብህ። ኳስ እንዴት እየሄደ እንዳለና መጨረሻው የት ጋር እንደሚሆን ሂደቱን እያነበብክ መንቀሳቀስ አለብህ። በዚህ መንገድ ጨዋታን የምታነብ ከሆነ ያለምንም ጥያቄ ጎበዝ ተጫዋች ትሆናለህ። በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ይሄንን ነገር ማድረግ አለባቸው። ቡድንህ ኳስ በሚይዝበት ጊዜ ራስህን በተሻለ የማጥቂያ ቦታ ላይ ማድረግ አለብህ ፤ ኳስ በሚታጣ ጊዜ ደግሞ በተሻለ የመከላከል ቦታ ላይ መገኘት ይገባል። ይሄንን ለማድረግ መብሰል እና በተቻለ መጠን ሜዳውን በደንብ መቃኘት ያስፈልጋል። የራስህንም ሆነ የተጋጣሚን ቡድን ተጫዋቾች ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል። በቅድሚያ ይሄንን በተሻለ እንዳደርግ ለረዳኝ ፈጣሪ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው። ከፈጣሪ በኋላ ግን አሠልጣኞቼን ማመስገን እፈልጋለው። ከዚህ ውጪ ቀድሜ እንዳልኩት ብዙ ጨዋታዎችን ስለማይ ከዛ እማራለው። አብዛኛውን ጊዜዬን ደግሞ ሜዳ ላይ ስለማሳልፍ የተማርኩትን ለመተግበር እጥራለው።”
ብዙዎች ጨዋታዎች ላይ ነው የሚመለከቱህ። ልምምድ ሜዳ ላይ ምን አይነት ሰው ነህ? በምን አይነት ስራዎች ነው ራስህን ለማብቃት የምትጥረው?
“በጋራ ልምምዶችን ማድረግ ደስ ይለኛል። በጋራ ስትሰራ ብትደክም እንኳን አንዱ እያበረታህ የተሻለ ለመስራት ትሞክራለህ። በግሌ ስሰራ ግን የፍጥነት እና ጥንካሬ ስራዎች ላይ ትኩረት አደርጋለው። እንደምታዩኝ ብዙም ፍጥነት የለኝም። ይህንን ተከትሎ ፍጥነቴን ለማሻሻል እሞክራለው።”
የእግርኳስ አርዓያህ ማነው?
“አንድን ተጫዋች አርዓያዬ ነው ብሎ ለመምረጥ ትንሽ ይቸግረኛል።አሁን ድረስ ብዙ የምማርባቸው ተጫዋቾች አሉ። በታዳጊነት ብዙ የፍራንክ ላምፓርድን ቪዳዮዎች እመለከት ነበር። በግሌ በጣም እወደዋለሁ። ሁሌም ቢሆን ለጎል ያለው ዕይታ ይገርመኛል። ቀጥሎ ደግሞ ከዣቪ ፣ ኢንዬሽታ እና ቡስኬትስ ብዙ ተምርያለሁ።አሁን ላይ ከኬቨን ደብሮይነ ፣ ጆርጂንሆ ፣ ቶኒ ክሮስ እና ሉካ ሞድሪች እንቅስቃሴ ብዙ እየተማርኩ ነው። ስለዚህ አንዱን መምረጥ ይቸግረኛል።”
ቅፅል ስም አለህ?
“አዎ! የተለያዩ ሰዎች በተለያየ ሥም ይጠሩኛል። ጋና ላይ ግን አብዛኞቹ ከአጨዋወቴ ጋር በተገናኘ ነው መሰለኝ ላምፓርድ ይሉኛል።”
ስለኢትዮጵያ ተጫዋቾች ምን ትላለህ?
“የኢትዮጵያ ተጫዋቾች አብዛኞቹ በጣም ጥሩ ናቸው። ቴክኒካሊ እና ታክቲካሊ ጥሩ ናቸው። በተለይ ቴክኒካሊ የተሻሉ ናቸው። ከኳስ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚፈልጉ ናቸው። ብዙ የተሻለ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች አይቻለው። ግን ያንን ብቃት መጠበቅ እና ማሳደግ የግድ የሚል ይመስለኛል።”
ባሲሩ ምን አይነት ሰው ነው? ከእግርኳስ ተጫዋችነት ውጪ ያለህን ህይወት በአጭሩ አስተዋውቀን እስኪ?
“ሙስሊም ነኝ ፤ ፈጣሪዬን በጣም ለመቅረብ የምጥር ሰው ነኝ። በጣም ሀይማኖተኛ ሰው ነኝ። በቀን ውስጥ 5 ጊዜ የምፀልይ ሰው ነኝ። መጠጥ ምናምን የሚባሉ ምንም ሱሶች የሉብኝም። ብዙም መጥፎ ነገሮች ላይም መሳተፍ በፍፁም አልፈልግም። ሁሌ ለፈጣሪዬ መቅረብ ነው የምፈልገው። ሰው በጣም እወዳለው። ከሰዎች ጋር ማውራት ደስ ይለኛል ፤ ግን መጥፎ ጓደኞችም በፍፁም አላቀርብም። በተረፈ ቀለል ያልኩኝ ሰው ነኝ።”
ክለቡህ መድን በመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታ አሰቃቂ ሽንፈት አስተናግዶ ወዲያው በማገገም በአሁኑ ሰዓት የሊጉ መሪ ሆኗል። የክለብህን ጉዞ እንዴት ታየዋለህ?
“በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ 7 ግቦችን አስተናግደናል። ከዛ ጨዋታ በኋላ ግን በደንብ እየተሻሻልን ነው የመጣነው። በተለይ አሠልጣኙ ከዛ ጨዋታ በኋላ ነገሮችን የተሻለ ለማድረግ ጥሯል። የተጫዋቾቹንም የራስ መተማመን በማሳደግ ታክቲካሊ ቡድኑን ለማሻሻል ጥሯል። ሁሉም እንደሚለው የመጀመሪያው ጨዋታ መጥፎ ውጤት የተገኘበት ቢሆንም ለዛ በኋላ ግን በጥሩ መንገድ እየተጓዝን ነው። በዚህ መንገድም እንደምንቀጥል አስባለው።”
ከክለብህ ጋር ያለህ እቅድ ምንድን ነው?
“በአዲሱ ክለቤ ኢትዮጵያ መድን መለያ ያለኝ የዘንድሮ የግል እቅድ በምችለው አቅም ብዙ ጎሎችን እና አሲስቶችን ማስመዝገብ ነው። ዋናው የእኔ ሀሳብ ግን ቡድኑ ነው። ሁሌ የማስበው ቡድኔን ማገዝ ላይ ነው። መድን አዲስ አዳጊ ክለብ ነው። ይህ ቢሆንም ግን ጥሩ ቦታ ላይ ይገኛል። የሊጉም መሪ ነው። አብዛኞቹ አዲስ አዳጊ ክለቦች በሊጉ መቆየትን ቀዳሚ እቅዳቸው ቢያደርጉም እኔን ጨምሮ ሁሉም ተጫዋቾች በራሳችን ከተማመንን ለሊጉ ዋንጫ የማንፎካከርበት ምንም ምክንያት የለም። በግሌ ግን ግቦች ላይ በተሻለ በቀጥታ መሳተፍ እቅዴ ነው።”