ከመጫወቻ ሜዳ ምቹነት ጋር በተያያዘ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አራት መርሐ-ግብሮችን ላልተወሰነ ጊዜ ያስተላለፈው ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በ8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይመለሳል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሀዋሳ ከተማ
ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ያሸነፉት እና በምርጥ ወቅታዊ ብቃት ላይ በመገኘት በደረጃ ሰንጠረዡ እኩል 13 ነጥቦችን በመያዝ በግብ ክፍያ በመበላለጥ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዲያ እና ሀዋሳ ነገ የሚያደርጉት የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሠልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ የመክፈቻ ሳምንት ጨዋታ በመቻል በፍፁም ቅጣት ምት በተቆጠረበት ብቸኛ ግብ ከተረታ በኋላ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ ራሱን በደረጃ ሰንጠረዡ የላይኛው ፉክክር አስገብቷል። እንደ ቡድን ሁሉንም የጨዋታ ምዕራፎች ለማሸነፍ ሲጥር የሚታየው ሀዲያ በተለይ በመከላከሉ ረገድ ያለው ጥንካሬ ለተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ግብ ለማስቆጠር የራስ ምታት ሲሆን ይታያል። ቡድኑም በሊጉ ጥቂት ጎል ያስተናገደ የተከላካይ ክፍል ባለቤት የሆነ ሲሆን ከተቆጠሩት 3 ግቦች ደግሞ ሁለቱ የቆመ ኳስን መነሻ ያደረጉ መሆኑን ስናስብ በእንቅስቃሴ ውስጥ ለተጋጣሚ ግቡን በቀላሉ የሚከፍት እንዳልሆነ እንረዳለን። በማጥቃቱ ረገድም በዋናነት ሽግግሮችን ለመጠቀም የሚጥር ነው። ምናልባት የነገው ተጋጣሚ በዚህ የሽግግር አጨዋወት የተዋጣለት ስለሆነ ግን የትኛው ቡድን ይሄንን ምዕራፍ ያሸንፋል የሚለውም ይጠበቃል።
ያለፉትን አራት ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት ያላስተናገደው ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በፈታኞቹ ሁለት ጨዋታዎች ያገኘው ወሳኝ ስድስት ነጥብ ያለበትን አሁናዊ አቋም ፍንትው አድርጎ የሚገልፅ ይመስላል። በተለይ ፋሲል ከነማን ሁለት ለምንም ያሸነፈበት ፍልሚያ ቡድኑ በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ የነበሩበትን በርካታ ክፍተቶች እያሻሻለ እንደመጣ ማሳያ ነበር። ከምንም በላይ ቡድናዊ እና ግለሰባዊ ስህተቶች የማይጠፉበት የተከላካይ ክፍል ሽንቁሩን በሚገባ ደፍኖ መጥቷል። በማጥቃቱም ቢሆን በአብዛኛው ኳስን በማንሸራሸር የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ውስንነት ቢኖርበትም ፈጣኖቹን አጥቂዎች ያማከለ ጥቃት በመሰንዘር የተዋጣለት ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ምናልባት ነገ ግን ከላይ እንደገለፅነው ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለውን ሀዲያን ስለሚገጥም የማጥቂያ አማራጮቹን ማስፋት የግድ ይለዋል።
ሀድያ ሆሳዕና በነገው ጨዋታ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በጉዳት እና ቅጣት ምክንያት አያሰልፍም። በዚህም ባዬ ገዛኸኝ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ቤዛ መድህን በጉዳት ግርማ በቀለ ደግሞ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ሆነዋል፡፡ በሀዋሳ በኩል ደግሞ ወንድማገኝ ኃይሉ ከክለቡ ጋር ከተፈጠረው የውል ውዝግብ ተመልሶ ልምምድ ቢጀምርም የመሰለፉ ነገር አጠራጥሯል፡፡ በተቃራኒ አዲሱ አቱላ ከጉዳቱ መድሀኔ ብርሃኔ ደግሞ ከቅጣት ሲመለሱ እዮብ አለማየሁ ግን በቅጣት ግልጋሎት አይሰጥም።
የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ መሪነት ይከወናል።
ቡድኖቹ እስካሁን ስድስት ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ ሁለቱ ሲረታ ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አንዱን አሸንፏል። ቀሪዎቹን ሦስት ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ፈፅመዋል። በጨዋታዎቹም ሀዋሳ 10 ሀዲያ 8 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ መድን
እንደ መጀመሪያው ጨዋታ ሁሉ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚታሰበው የሲዳማ ቡና እና የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ደግሞ 1 ሰዓት ሲል ጅማሮውን ያደርጋል።
በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመራው ሲዳማ ቡና ሊጉን ከጀመረበት መጥፎ መንገድ በመጠኑ እየወጣ ይመስላል። በተለይ በ6ኛ የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማን በረታበት ፍልሚያ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የተሳካ ጊዜን በማሳለፍ ለ2ኛ ጊዜ ግቡን ሳያስደፍር ከመጀመሪያው የድሬዳዋ ጨዋታ በኋላ ሁለት ግብ ያገኘበትን ዕለት በማሳለፍ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ድል አሳክቶ ነበር። ይህ መሻሻል ግን በቀጣዩ የሀዋሳ ጨዋታ በውጤት መታጀብ ሳይችል ቀርቶ ዳግም ለተጋጣሚ ሦስት ነጥብ ለማስረከብ ተገዷል። ይህ ቢሆንም ግን በተለይ ሚዛኑን ያገኘ የሚመስለው የቡድኑ የአማካይ መስመር ለተጋጣሚ ፈታኝ ሆኗል። ነገም ሁለቱ በ”ሙሉ” የሚጀምር ስም ያላቸው ሙሉቀን እና ሙሉዓለም ለተከላካዮች ተገቢውን ሽፋን እየሰጡ ለማጥቃት ባህሪ ላላቸው ተጫዋቾች ወደፊት የመሄድ ነፃነት የሚሰጡበት መንገድ የቡድኑ ወሳኝ ክፍል ሊሆን ይችላል።
የወቅቱ የሊጉ ምርጥ ቡድን የሆነው ኢትዮጵያ መድን ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የደረጃ ሰንጠረዡን በበላይነት የሚመራ አዲሱ ክለብ ሆኗል። እንደ ተጋጣሚው ሲዳማ በመሐል ሜዳ ተጫዋቾቹ ጨዋታዎችን ለመቆጣጠር እና ለመወሰን የሚጥረው መድን ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል በኋላ በባህር ዳር ከተማ ከደረሰበት ሽንፈት ባሳለፍነው ሳምንት አገግሟል። በሽንፈት ድባቴ ብዙ እንደማይቆይ ከአንድም ሁለት ጊዜ የታየ ሲሆን በኤልፓው ጨዋታ ደግሞ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶበት እንኳን በተለያዩ የጨዋታ አማራጮች ግቦችን ማግኘት እንደሚችል ተስተውሏል። ከላይ እንደገለፅነው ሲዳማ በአዲሱ አሠልጣኝ ስር በሁሉም የሜዳ ክፍሎች መሻሻል ስላመጣ ግን ብርቱ ፉክክር ስለሚጠብቀው በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመዝለቅ ጠንከር ብሎ መቅረብ የግድ ይለዋል።
ሲዳማ ቡና ነገም የሳላዲን ሰዒድን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም። በተጨማሪም የግብ ዘቡ ፍሊፕ ኦቮኖ በቅጣት ምክንያት በግብ ብረቶች መሐል አይቆምም። ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ከሳሙኤል ዮሐንስ ውጪ ሁሉንም ተጫዋቾች በጨዋታው ያገኛል።
ይህንን ጨዋታ ደግሞ አባይነህ ሙላት በአልቢትርነት የሚከውኑት ይሆናል።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በሊጉ 6 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 2 ጊዜ ሲያሸንፍ ቀሪዎቹን 4 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ 6 ሲያስቆጥር መድን በበኩሉ 4 አስቆጥሯል።