ዘግይቶ ልምምድ የጀመረው አዳማ ከተማ የአስራ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የሁለት ነባሮችን ኮንትራትም አድሷል፡፡
በአሰልጣኝ ኤፍሬም እሸተ እየተመራ የፊታችን ቅዳሜ በሀዋሳ በሚጀመረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ተካፋይ የሚሆነው አዳማ ከተማ አዳዲስ አስራ ሦስት ተጫዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን ከሌሎች ክለቦች ዘግይቶ ወደ ልምምድ ገብቷል፡፡ ቡድኑ ከአዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ ሁለት ውላቸው ተገባዶ የነበሩ ተጫዋቾችን ውልም አድሶ በምክትል አሰልጣኝነት ቦታ ላይ ደግሞ የቀድሞውን አንጋፋ ተጫዋች ብርሀኑ ቃሲምን ሾሟል፡፡
በዚህም በአዳማ ተጫውታ የነበረችው የቀድሞዋ የደደቢት ተከላካይ ወይንሸት ፀጋዬ በድጋሚ ወደ እግር ኳሱ ተመልሳ ክለቡን ስትቀላቀል የቀድሞው የደደቢት፣ መከላከያ እና ድሬዳዋ ከተማ ተከላካይ ዘቢብ ኃይለስላሴ እና የቀድሞው የድሬዳዋ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ አጥቂ ይታገሱ ተገኝወርቅን ጨምሮ ቤተል ጢባ አጥቂ ከጌዲኦ ዲላ ፣ ሄለን መሰለ አጥቂ ከድሬዳዋ ፣ ሰናይት ሸጎ ተከላካይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ቻይና ግዛቸው ተከላካይ ከድሬዳዋ ፣ ሳሮን ጎሳ ተከላካይ ከአርባምንጭ ፣ ሳባ ኃይለሚካኤል አማካይ ከባህርዳር ፣ ባንቺአየው ታደሰ ተከላካይ ከኤሌክትሪክ ፣ መሠረት ባጫ ግብ ጠባቂ ከልደታ ፣ ሳምራዊት መንገሻ ግብ ጠባቂ ከለገጣፎ እና የትምወርቅ አጥቂ ከለገጣፎ የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎች ሆነዋል፡፡
ቡድኑ ከአዳዲሶቹ ፈራሚዎች በተጨማሪ የፀባኦት መሀመድ እና ሳምራዊት አስፋውን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሟል፡፡