ሪፖርት | ኃይቆቹ በጭማሪ ደቂቃ ጎሎች ከነብሮቹ ነጥብ ተጋርተዋል

አስገራሚ የመጨረሻ ደቂቃ ትዕይንቶች  በታዩበት የስምንተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስቶ በመጨረሻ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ከሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ወስዷል።

10፡00 ላይ የሀድያ ሆሳዕና እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታቸው ለሌላ ጊዜ የተላለፈባቸው ነብሮቹ በስድስተኛው ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲን 1-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አክሊሉ ዋለልኝ ፣ ስቴፈን ንያርኮ ፣ ፀጋዬ ብርሃኑ እና ሪችሞንድ ኦዶንጎ በግርማ በቀለ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና ሠመረ ሀፍታይ ተተክተው ጀምረዋል። ኃይቆቹ በበኩላቸው በሰባተኛው ሳምንት በሮድዋ ደርቢ ሲዳማ ቡናን 1-0 ከረታው ስብስባቸው የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ ሲያደርጉ መድኃኔ ብርሃኔ ከቅጣት መልስ በሠለሞን ወዴሳ ተተክቶ ጀምሯል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር የታየበት ሲሆን የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል ግን ሆሳዕናዎች እጅግ ተሽለው የታዩበት ነበር። የጨዋታው የመጀመሪያ ክስተት የሆነው አጋጣሚ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሲፈጠር ሰዒድ ሀሰን ብርሃኑ በቀለ ላይ በሠራው ጥፋት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የፍፁም ቅጣት ምት ሲያገኙ ሄኖክ አርፊጮ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ መልሶበታል። ይሄም በነብሮቹ በኩል ትልቁ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።

የአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ተሰላፊዎች በተደጋጋሚ በሚያገኟቸው  በተለይም ከብርሃኑ በቀለ በሚነሱ ኳሶች ፈጣን ሽግግር እያደረጉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ 19ኛው ደቂቃ ላይ ስቴፈን ንያርኮ ከረጅም ርቀት በጥሩ ሁኔታ ሞክሮት ዒላማውን ሳይጠብቅ የወጣው እና በአራት ደቂቃዎች ልዩነት የሀዋሳዎች ተከላካይ ዳንኤል ደርቤ ከተጋጣሚ ቡድን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለማስወጣት ሲሞክር ባልታሰበ ሁኔታ ወደራሱ የግብ አቅጣጫ ሄዶ የላዩን አግዳሚ ታክኮ የወጣው ኳስ በነብሮቹ በኩል ሌሎቹ አስቆጪ አጋጣሚ ነበሩ። ሀዋሳ ከተማዎች ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በተሻለ ቅብብል ወደፊት ለመጠጋት ቢሞክሩም የተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ ለመግባት እጅግ ሲቸገሩ ተስተውሏል።

ነብሮቹ 25ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን አጋጣሚ አግኝተዋል። በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ብርሃኑ በቀለ ያሻማውና ዳግም ንጉሤ  በግንባሩ በትንሹ የነካውን ኳስ ያገኘው ፀጋዬ ብርሃኑ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። ሀዋሳዎች በዓሊ ሱሌይማን እና ሙጂብ ቃሲም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ አንድም የግብ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ሀዲያ ሆሳዕናዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደራሳቸው የሜዳ ክፍል ጥቅጥቅ ብለው መጫወትን ሲመርጡ በመጠኑም ቢሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ሀዋሳዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ  ቢሆኑም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ግን መቸገራቸው ቀጥሏል። በአጋማሹ የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ዕድል የፈጠሩት 50ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ዓሊ ሱሌይማን ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሙጅብ ቃሲም ግብ ጠባቂውን አታሎ ማለፍ ቢችልም ኳሱን ከመጠን በላይ በመግፋቱ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ኃይቆቹ በተደጋጋሚ ወደፊት ተጠግተው በዓሊ ሱሌይማን እና ኤፍሬም አሻሞ ጥቃት ለመሰንዘር ቢሞክሩም ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።

የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች አስገራሚ ትዕይንት የታየባቸው ሲሆን 85ኛው ደቂቃ ላይ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከቀኝ መስመር  ያሻገሩትን ኳስ ያገኘው ላውረንስ ላርቴ በትክክል ባለማራቁ የተገኘውና ኢያሱ ታምሩ በጥሩ ሁኔታ በአንድ ንክኪ ማቀበል የቻለውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው መለሰ ሚሻሞ አስቆጥሮ የነብሮቹን መሪነት ማጠናከር ችሏል።

ኃይቆቹ ያሏቸውን የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች እየቀየሩ በማስገባት የተሻለ የማጥቃት ክፍል ለማደራጀት ሲሞክሩ የጨዋታው መደበኛ ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመሩት የባከኑ ደቂቃዎች ላይ ዳንኤል ደርቤ ከቅጣት ምት ኳስ ሲያሻማ ያገኘው ብርሃኑ በቀለ ኳሱን ሲያስወጣ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሙጅብ ቃሲም አስቆጥሮ ሀዋሳን ወደ ጨዋታ መመለስ ችሏል።  በአንድ ደቂቃ ልዩነት ኃይቆቹ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ሲያደርጉ ወደፊት የወሰዱትን እና የተጋጣሚ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ የነብሮቹ ተከላካዮች ባለማራቀቸው ያገኘው አዲሱ አቱላ በአንድ ንክኪ ለኤፍሬም አሻሞ ሲያቀብል ኤፍሬም በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮ ጨዋታውን ባልተጠበቀ መንገድ 2-2 እንዲጠናቀቅ አስችሏል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ተጫዋቾቻቸው በመጨረሻ ደቂቃዎች መዘናጋት እንደታየባቸው እና ይሄም ዋጋ እንዳስከፈላቸው ሲናገሩ ከዕረፍት መልስ ኃይቆቹ ብልጫ የተወሰደባቸው የማጥቃት ክፍላቸውን አጠናክረው መቅረባቸውን አምነዋል። የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው በሁለተኛው አጋማሽ የአጥቂ ቁጥራቸውን ወደ ስድስት ከፍ ማድረጋቸው እንደጠቀማቸው ሲናገሩ ቡድናቸው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ እንዳሳየ ሲያምኑ ለኤፍሬም አሻሞ ያላቸውን አድናቆት “ድካም ቢኖርበት እንኳ በአዕምሮ የሚጫወት ነው” ሲሉ ገልፀውታል።