ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን መሪነቱን አስቀጥሏል

ሲዳማ እና መድንን ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ የመጀመሪያውን አጋማሽ በልዩ ሁኔታ በጨረሱት ኢትዮጵያ መድኖች 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ምሽት 01:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ ከሮድዋ ደርቢ ሽንፈት የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች ቅጣት ያገኘው ግብ ጠባቂው ፍሊፕ ኦቮኖን በመክብብ ደገፉ እንዲሁም ቡልቻ ሹራን በጎድዊን ኦባጄ ለውጠው ወደ ሜዳ ሲገቡ ኢትዮጵያ መድኖች ኢትዮ ኤሌክትሪክን የረቱበትን ቀዳሚ አሰላለፍ ሳይቀይሩ መቅረብን መርጠዋል።

ጨዋታው በመድኖች ወደ ግራ ያደላ የማጥቃት ጫና ጀምሯል። በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ኪቲካ ጀማ ከሀብታሙ ሸዋለም ቅጣት ምት እንዲሁም ባሲሩ ዑመር ካሳለፈለት ኳስ ባደረጋቸው ሁለት ጠንካራ ሙከራዎች መድኖች ወደ ግብ ቀርበው ታይተዋል። ቀስ በቀስ መረጋጋት የጀመሩት ሲዳማዎች በበኩላቸው በረጅሙ ወደ ፊት በመላክ ከሁለተኛ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር በመሞከር ምላሽ ሰጥተዋል።

ሆኖም የሲዳማ የተሻሉ ጥረቶች ሁሉ ከቆሙ ኳሶች የመነጩ ነበሩ። ቡድኑ 11ኛ ደቂቃ ላይ በፍሬው ሰለሞን ለጥቂት ኢላማውን በሳተ የቅጣት ምት ሙከራውን ሲጀምር 18ኛ ደቂቃ ላይ ያኩቡ መሐመድ ከግራ በረጅሙ ከተሻማ የቅጣት ምት ሁለተኛው ቋሚ ላይ ነፃ ሆኖ የመግጨት ዕድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የሲዳማ የቆሙ ኳሶች አስፈሪነት ቀጥሎ 22ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት በተነሳ ኳስ እንዳለ ከበደ በግንባር ጎድዊን ኦባጄ ደግሞ በእግር ያደረጓቸውን ተከታታይ ሙከራዎች አቡበከር ኑራ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ልዩነት በቅልጥፍና አምክኖባቸዋል።

መድኖችም የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው ባያምሩላቸውም በሲዳማ ሜዳ ላይ ከኳስ ውጪ ጫና በማሳደር እና ነጥቆ ጥቃት በመሰንዘር በፈጣን ቅብብሎች ሳጥን ውስጥ እየደረሱ አደጋ ለመጣል ጥረዋል። በተመጣጠነ እንቅስቃሴ በቀጠለው ጨዋታ ግን ሲዳማዎች በማጥቃቱ የተሻሉ ነበሩ። 28ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ከረጅም ርቀት ቅጣት ምት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርግ 34ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከግራ ከይገዙ ቦጋለ እግር ስር የተነሳ ለግብ የቀረበ ኳስ ጎዲን ኦባጄ በግንባሩ ሳይጠቀምበት አልፎታል። ቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ግን ለሲዳማ ቡናዎች እጅግ አስደንጋጭ ለመድኖች ደግሞ ጮቤ የሚያስረግጡ ሆነዋል።

በቅድሚያ ኪቲካ ጀማ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ለማሻገር የሞከረውን ኳስ ያኩቡ መሐመድ በእጁ በመንካቱ የዕለቱ አርቢትር ዓባይነህ ሙላት የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት ሀብታሙ ሸዋለም 37ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብነት ለውጦታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሀብታሙ ከማዕዘን ያሻማውን እና መክብብ ደገፉ በጡጫ ያወጣውን ኳስ አማካዩ ዮናስ ገረመው ከሳጥን ውጪ በቅጥታ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሯል። በዚህ ያላበቃው የሲዳማዎች ችግር ቀጥሎ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮቻቸው በአግባቡ ማራቅ ያልቻሉትን ረጅም ኳስ የመድኑ አጥቂ ሳይመን ፒተር ለመጠቀም ባደረገው ጥረት ውስጥ መክብብ ደገፉ በሰራው አደገኛ ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ መድኖች በደቂቃዎች ልዩነት ያገኙትን ሁለተኛ ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ ሙሉጌታ ሦስተኛ ጎል አድርጎታል።

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ፀጋዬ አበራን ቀጠል አድርገውም ቡልቻ ሹራን ቀይረው በማስገባት ቡድኑ ባለው አቅም ሁሉ እንዲያጠቃ አድርገዋል። በዚህም ሲዳማ በመጀመሪያ 18 ደቂቃዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ፣ ቀጥተኛ ጥቃት እና የቆሙ ኳስ ዕድሎችን በመፍጠር የበላይነቱን ወስዷል። በአንፃሩ መድኖች የጨዋታውን ግለት በማርገብ እና በቅብብሎች ከሜዳ በመውጣት የሲዳማ ጫና በአደገኛ ሙከራዎች እንዳይታጀብ ማድረግ ሲችሉ 66ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ድንገተኛ ቡጢ ሰንዝረዋል። በዚህም ያኩቡ መሐመድ ከግብ ጠባቂው አዱኛ ፀጋዬ የተቀበለውን ኳስ ለማብረድ ሲሞክር ኳስ ያስጣለው ኪቲካ ጀማ ቀለል አድርጎ በማስቆጠር የመድንን የግብ መጠን አራት አድርሶታል።

በቀሩት ደቂቃዎች ሲዳማዎች በይገዙ ቦጋለ ታታሪነት ታጅበው ልዩነቱን ለማጥበብ በቻሉት መጠን ሲንቀሳቀሱ 73ኛው ደቂቃ ላይ መሀሪ መና ከግራ መስመር ካሻገረውን ኳስ ፀጋዬ በግንባር እንዲሁም 75ኛ ደቂቃ ላይ ቡልቻ ከሳጥን ውጪ በመምታት ያደረጓቸው ሙከራዎች በአደገኝነታቸው ቢጠቀሱም በአቡበከር ድነዋል። ጨዋታውን በማቀዝቅዝ አልፎ አልፎ ማጥቃት ሲሰነዝሩ የታዩት የቁጥር ብልጫ የነበራቸው መድኖች የ4-0 መሪነታቸውን አስጠብቀው ጨርሰዋል። በዚህም መሰረት አዲስ አዳጊው ቡድን በ18 ነጥቦች ሊጉን መምራት መቀጠሉን አረጋግጧል።

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ የስህተቶች መበራከት እና የአማካይ ክፍል ድክመት ለሽንፈት እንደዳረጓቸው አስረድተው የግብ ዕድሎችን በመጨረስ ላይ ሰርተው በተሻለ ተነሳሽነት እንደሚመለሱ ጠቁመዋል። አሸናፊው አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በበኩላቸው እንደቡድን በሁሉም ዲፓርትመንቶች ጥሩ እንደነበሩ በመግለፅ ሁሉም ጎሎች በተቆጠሩባቸው ደቂቃዎች የነበራቸው ዋጋ ከፍ ያለ መሆኑን በማንሳት ድሉ በቀድሞው ክለባቸው ሲዳማ ቡና ላይ መሆኑ የተለየ ትርጉም እንደማይሰጣቸው ተናግረዋል።