በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ተካፋይ የሆነው ድሬዳዋ ከተማ አስራ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአራት ነባሮችን ውልም አድሷል፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንካራ ተወዳዳሪ የሆነው ድሬዳዋ ከተማ በአሰልጣኝ እዮብ ተዋበ መሪነት በክለቡ መቀመጫ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲሰራ ቆይቶ ወደ ሀዋሳ ከተማ ለሊጉ ውድድር አምርቷል፡፡ ቡድኑ በክረምቱ የዝውውር መስኮት አስራ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ወደ ስብስቡ ያካተተ ሲሆን አራት ውላቸው ተጠናቆ የነበሩትን ውል ደግሞ አራዝሟል፡፡
የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ እና ኤሌክትሪክ ተከላካይ መስከረም ኢሳያስ ፣ ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ ተጫውታ ያሳለፈችው እና በባህርዳር እና መከላከያ የተጫወተችው አጥቂዋ ስራ ይርዳው ፣ በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ስልጠናዋን አጠናቀ ያለፉትን አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታ የነበራት አጥቂዋ ፎዚያ መሀመድ ፣ የቀድሞዋ የኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ አጥቂ ወርቅነሽ ሜልሜላ ፣ ቤቲ ዘውዴ አማካይ ከኤሌክትሪክ ፣ ትዝታ ፈጠነ አጥቂ ከኤሌክትሪክ ፣ ዕድላዊት ተመስገን አማካይ ኤሌክትሪክ ፣ ሜላት ደመቀ አማካይ ከባህርዳር ፣ ሊዲያ ጌትነት ተከላካይ ከባህርዳር ፣ ቃልኪዳን ተስፋዬ ተከላካይ ከባህርዳር ፣ ዝናሽ መንከረ ግብ ጠባቂ ከአዳማ ፣ ሳራ ብርሀኑ ግብ ጠባቂ ከጌዲኦ ዲላ፣ የመስመር ተጫዋቿ አክበረት ገብረፃዲቅ እና ተከላካዩዋ አብነት ለገሰ የክለቡ አዳዲስ ፈራሚ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ቡድኑ ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች በተጨማሪ ሦስት ተጫዋቾችን ከሁለተኛው ዲቪዚዮን ማሳደጉን ለዝግጅት ክፍላችን የተላከው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም ውላቸው አልቆ የነበሩት ህይወት ዳንኤል ፣ ሊና መሀመድ ፣ አያን ሙሳ እና ቤዛዊት ንጉሴ ውልም ለተጨማሪ ዓመት መታደሱ ታውቋል፡፡