ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የጦና ንቦቹ ከመመራት ተነስተው በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች አዳማ ከተማን 2-1 መርታት ችለዋል።

10፡00 ላይ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታቸው የተራዘመባቸው የአዳማ ከተማ እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ ሲደረግ አዳማዎች በስድስተኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና 2-0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ኢዮብ ማቲዎስ ፣ አድናን ረሻድ እና ቦና ዓሊ በደስታ ዮሐንስ ፣ አማኑኤል ጎበና እና አብዲሳ ጀማል ተተክተው ጀምረዋል። የጦና ንቦቹ በበኩላቸው በስድስተኛው ሳምንት መቻልን 1-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የተሰናበተውን ግብ ጠባቂውን ቢንያም ገነቱን በወንድወሰን አሸናፊ በጉዳት ያጡትን ንጋቱ ገብረሥላሴን በመሳይ ኒኮል ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ በኩል ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ሲሆን የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል ግን አዳማ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ። የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ 4ኛ ደቂቃ ላይ በአዳማ ከተማዎች ሲደረግ ዊልያም ሰለሞን የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከግራ መስመር ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ኃይል ያልነበረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ በቀላሉ ይዞታል። 10ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ተጨማሪ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ ሲያገኙ ከራሳቸው የግብ ክልል የተሻማውን ኳስ ያገኘው አሜ መሐመድ ግብ ጠባቂውን ማለፍ ቢችልም ኳሱ በመርዘሙ ወደ ውጪ ወጥቶበት ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል።

የጦና ንቦቹ ወደ ራሳቸው የሜዳ ክልል ተጠግተው የሚያገኙትን ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም ላይ በማድረስ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲታትሩ 11ኛው ደቂቃ ላይ  ቃልኪዳን ዘላለም እና ሀብታሙ ንጉሤ በግራ መስመር በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም ወደግብ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በተጨማሪም 20ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም እና አበባየሁ ሀጂሶ በድጋሚ በግራ መስመር በጥሩ ቅብብል በወሰዱት ኳስ ቃልኪዳን ፍሬደሪክ ሀንሰንን አታሎ ማለፍ ቢችልም ወደግብ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል። ይሄም የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ የፈጠረው የተሻለው የግብ ዕድል ነበር።

መሃል ሜዳ ላይ እንደነበራቸው ብልጫ በተረጋጋ ሁኔታ የተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ ለመግባት የተቸገሩት አዳማዎች  የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ውጤታማ ለመሆን ተቸግረዋል። 22ኛው ደቂቃ ላይ አድናን ረሻድ ከረጅም ርቀት የተሰጠውን የቅጣት ምት አክርሮ በመምታት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ኳሱ የላዩን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። አዳማ ከተማ በዊልያም ሰለሞን ፣ በአሜ መሐመድ እና መስዑድ መሃመድ ወላይታ ድቻ በቃልኪዳን ዘላለም እና አበባየሁ ሀጂሶ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የአሰልጣኝ ይታገሡ እንዳለ ቡድን  የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከሩ ደቂቃዎች ላይ መሪ መሆን ችሏል። ከመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ፍሬድሪክ ሀንሰን በረጅሙ  በግራ መስመር ላይ ለነበረው ዊልያም ሰለሞን ሲያቀብል ኳሱን በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ የወሰደው ዊልያም ለቦና ዓሊ አመቻችቶለት ቦናም አስቆጥሮ አዳማ የመጀመሪያውን አጋማሽ መርቶ እንዲወጣ አስችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች አዳማዎች የተሻለ ወደፊት ተጠግተው መጫወት ሲችሉ 53ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሀመድ ግሩም ኳስ ለአሜ መሐመድ አመቻችቶ ቢያቀብልም አሜ ኃይል በሌለው ሙከራ ተጨማሪ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል።

ከዚህ ሙከራ በኋላ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድን እጅግ ተሻሽሎ ሲቀርብ 61ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዮናታን ኤልያስ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ የነጠረውን ኳስ በግራ እግሩ ከፍ አድርጎ በድንቅ ሁኔታ በማስቆጠር ድቻን አቻ ማድረግ ችሏል። በአራት ደቂቃዎች ልዩነት የአዳማ ከተማዎችን አለመረጋጋት የተጠቀሙት የጦና ንቦቹ መሪ መሆን ችለዋል። አበባየሁ ሀጂሶ ከግራ መስመር ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ዮናታን ኤልያስ ወደግብ ሲመታ ኢዮብ ማቲያስ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ቃልኪዳን ዘላለም በተረጋጋ ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል።

የግብ ብልጫ በተወሰደባቸው ቅፅበት የአጥቂ መስመራቸውን ያጠናክራል ብለው ያሰቧቸውን ተጫዋቾች ቀይረው ያስገቡት አዳማ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለውን ሙከራ 78ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ መስዑድ መሀመድ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ወንድወሰን በቀላሉ መያዝ ችሏል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ወደራሳቸው የሜዳ ክልል ጥቅጥቅ ብለው ሲጫወቱ አዳማ ከተማዎች የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢቸገሩም ተጭነው መጫወታቸውን ቀጥለዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የባከኑ ደቂቃዎች ሲቀሩ ኢዮብ ማቲያስ በግሩም ሁኔታ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ወንድወሰን ሲመልሰው ያገኘው አናጋው ባደግ በጥሩ ቅልጥፍና ማውጣት ችሏል። ይሄም የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በወላይታ ድቻ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ከዕረፍት በፊት የተሻሉ እንደነበሩ እና ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ቢጠቀሙ ኖሮ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን በመጀመሪያው አጋማሽ መጨረስ ይችሉ እንደነበር እና ያ አለመሆኑ ዋጋ እንዳስከፈላቸው አበክረው ሲናገሩ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው መሃል ሜዳ ላይ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ማጥቃቱ ላይ አስፈሪ እንዳልነበሩ ግን ከዕረፍት መልስ ተጫዋቾቹ ውጤት ተርበው መግባታቸው ለድል እንዳበቃቸው ሲናገሩ በተጨማሪም ወጣት ተጫዋቾችን ኃላፊነት ሰጥተው የሚያስገቡበት ሰዓት እንደሆነ እና ለሁሉም ክለብ ዕኩል ግምት ሰጥተው እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።