ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል ጋር ነጥብ ተጋርተዋል

ሁለቱን የመዲናይቱን ቡድኖች ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከወልቂጤ ከተማ ጋር ካስመዘገቡበት የአቻ ውጤት ጨዋታ በአንድ ተጫዋች ላይ ለውጥ አድርገዋል፡፡ በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ለተደጋጋሚ ስህተት ተጋላጭ የነበረውን ቻርለስ ሉኩዋጎን ወደ ተጠባባቂ በማውረድ ባህሩ ነጋሽን ሲተኩ ፣ በመቻሎች በኩል ከድሬዳዋው ጨዋታ አንፃር በረከት ደስታ እና ፍፁም ዓለሙን በግርማ ዲሳሳ እና ከነዓን ማርክነህ ተክተው ቀርበዋል፡፡

ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ጥድፊያ የበዛበት እንቅስቃሴ የታየበት ነበር፡፡ የመስመር አጨዋወቶች በይበልጥ ጎልተው በተንፀባረቁበት ጨዋታ ይደረጉ ከነበሩ እንቅስቃሴዎች ውጪ ጥርት ያሉ አጋጣሚዎችን ለመመልከት የታደልንበት አልነበረም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳስን ለረጅም ደቂቃዎች ያህል በመቆጣጠር በተጋጣሚያቸው ላይ በተሻለ ብልጫን ሲያሳዩ ብንመለከትም በመስመር አጨዋወት የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት የሽግግር ሂደት ለመጫወት የሚዳዱት መቻሎች በተወሰነ መልኩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያሳዩት ትጋት ከጊዮርጊስ ተሽሎ መታየት ችሏል፡፡ 9ኛው ደቂቃ ላይ በዚህ የመልሶ ማጥቃት ሽግግር በቀኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ አቅጣጫ ከሳጥኑ ጠርዝ ምንይሉ ወንድሙ አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ በላይኛው የግቡ ብረት ታካ ለጥቂት በወጣችበት ቅፅበታዊ ሙከራ ወደ ጎል በመቅረቡ ቀዳሚ ሆነዋል፡፡

በእንቅስቃሴ ብርቱ የሜዳ ላይ ፉክክርን ነገር ግን የጎል ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ የስልነት ድክመትን ሁለቱን ቡድኖቹ ሲያሳዩ በደንብ አስተውለናል፡፡ በኳስ ቁጥጥሩ ቢበለጡም በተቃራኒው የሚያገኙት የግብ ቀዳዳ ፍለጋ ላይ በተሻለ የተሰማሩት መቻሎች ሁለተኛውን ሙከራም በድጋሚ አግኝተዋል፡፡ 11ኛው ደቂቃ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች የሰሩትን የሽፋን ስህተት ምንይሉ ለከነዓን ሰጥቶት ከነዓን ቢመታውም ኳሷ ኃይል ስላልነበራት በቀላሉ ባህሩ የያዘበት ተጠቃሿ ሌላኛዋ ሙከራ ሆናለች፡፡ ከመሀል ሜዳ ክፍሉ ወደ ቀኝ መስመር ወደ ተሰለፈው ቢኒያም በላይ በማጋደል ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ብልጫን ለመውሰድ ፈረሰኞቹ በእጅጉን ጥረዋል፡፡ 18ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ሔኖክ አዱኛ ሲያሻማ አማኑኤል ተርፉ በግንባር ገጭቶ ዳግም ተፈራ እንደምንም የያዘበት አጋጣሚ የቡድኑ ጥራት ያላት ሙከራ ነበረች፡፡ መቻሎች የኋላ መስመራቸውን በማስጠበቅ በመልሶ ማጥቃት ተጫውቶ ጎል ለማግኘት በሳሙኤል ሳሊሶ እና ከነዓን አማካኝነት ማግኘት ቢጥሩም የመጨረሻው የኳሱ ማረፊያ እምብዛም የተሳካ አልነበረም፡፡ በእንቅስቃሴ የበላይነትን በተለይ ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎችን የወሰዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት ሁለት ጊዜ ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡

ከዕረፍት ተመልሶ ጨዋታው ሲቀጥል አሁንም ኳስን በመቆጣጠሩ የፈረሰኞቹ የበላይነት የታየበትን እንቅስቃሴ ብንመለከትም የጨዋታው ይዘት ግን እጅጉን የተቀዛቀዘ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተደራጀው የመሀል ክፍሉ በሀይደር እና ጋቶች መሪነት በሁለቱ የመስመር ኮሪደሮች ቢኒያም እና ቸርነትን የማጥቂያ መንገዳቸው አድርገው ጎልን ለማግኘት የጣሩ ቢሆንም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የሚታይባቸውን የአጨራረስ ክፍተት ዳግም አለመቅረፋቸው ያገኙትን ዕድሎችን ለማባከን ተገደዋል፡፡ የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኙ መቻል በሁለተኛው አጋማሽ ይታይባቸው የነበረውን ክፍተት ለመድፈን አስራ አምስት ደቂቃዎች ከጠበቁ በኋላ አፋጣኝ የተጫዋች ለውጥን ለማድረግ ተገደዋል፡፡ በረከት ደስታ እና ፍፁም አለሙን በማስገባት ግርማ ዲሳሳ እና ከነዓን ማርክነህን ከለወጡ በኋላ ወደ ጨዋታ ቅኝት በመግባት በተለይ በበረከት የቀኝ መስመር በኩል ጥቃት መሰንዘርን ጀምረዋል፡፡

መቻሎች ምንም እንኳን የተጫዋች ለውጥን ካደረጉ በኋላ ተመጣጣኝ ወደ ሆነ ፉክክር ቢገቡም የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ ክፍል አስከፍቶ ዕድልን ከማግኘት አኳያ ከብዷቸው ተስተውሏል፡፡ በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግልፅ አጋጣሚዎችን በተደጋጋሚ ማግኘት ችለው ጎል እና መረብን ለማገናኘት አልታደሉም፡፡ 74ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ በኩል የተገኘን ቅጣት ምት ሱለይማን ሀሚድ በቀጥታ ወደ ግብ ክልል ሲያሻማ ዳዊት ወደ ራሱ ጎል ገጭቶ በሀይሉ ለማውጣት ሲጥር ተቀይሮ የገባው አቤል ያለው እግር ስር ኳሷ ገብታ ተጫዋቹ ቢሞክራትም ለጥቂት በቋሚ ብረቱ ታካ ወደ ውጪ ወጥታበታለች፡፡ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ መቻሎች በጥሩ ቅብብል ወደ ጊዮርጊስ የግብ አካባቢ ደርሰው ምንይሉ ወንድሙ በመጨረሻም ያገኘውን ከሳጥን ውጪ መቶ ግብ ጠባቂው ባህሩ ከያዘበት በኋላ ጨዋታው እንደ አጠቃላይ እንደነበረው ደብዛዛ ቅርፅ ሁሉ ጎል ሳያስመለክተን 0-0 ፍፃሜን አግኝቷል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጨዋታው መጥፎ እንዳልነበር እንዲሁም ውጥረት ፣ ሽኩቻ የበዛበት እንደሆነ እና ጎል አስቆጥረው ለማሸነፍ ቢጥሩም ወደ ጎልነት በመቀየሩ ረገድ ድክመት እንደነበረባቸው ከጠቀሱ በኋላ በቀጣይ ለማሻሻል እንደሚጥሩ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የመቻሉ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩሉ ተመሳሳይ መልክ የነበረውን አጋማሾች እንደተመለከቱ እና ልዩነት ያልነበረው እንደሆነ ሦስት ነጥብንም ፈልገው መጥተው ባይሳካም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሉ ትልቅ ቡድኖች አንድ ነጥብን ማግኘት ግን መጥፎ የሚባል አይደለም በማለት ገልፀዋል፡፡

ያጋሩ