የስምንተኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ሁለት መርሐ-ግብሮችን የተመለከቱ የጨዋታ በፊት መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ

በአንድ ነጥብ እና አንድ ደረጃ ተበላልጠው የተቀመጡት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት የዕለቱ የመክፈቻ ጨዋታ ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ-ግብሮች መካከል ሲካተት ሳቢ የሜዳ ላይ ፉክክርም ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል በኋላ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ በአዘጋጅ ከተማው ክለብ ድሬዳዋ ከተማ ሳይጠበቅ እጅ የሰጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በአዲሱ አሰልጣኛቸው ሥር የመዋሀድ ችግር እንዳለባቸው እየታየ ይገኛል። እርግጥ በጠባብ ጎሎች ባሸነፉባቸው ጨዋታም ይህ ነገር በመጠኑ ሲታይ የነበረ ሲሆን በድሬው ጨዋታ ግን የቡድን ግንባታው እና በየቦታው ያለው የተጫዋቾች እርስ በእርስ የመግባባት ነገር ገና እንደሆነ ተስተውሏል። ይህ ቢሆንም ግን በግላቸው የተሻለ ነገር ማድረግ የሚችሉ በርካታ ተጫዋቾች ስብስባቸው ውስጥ ስለሚገኙ ንቆ መግባት አያስፈልግም። በተጨማሪም ለ1 ሳምንት የተጠጋ የዕረፍት ጊዜ ስላገኙ አዲስ ጉልበት ይዘው ወደ ሜዳ ስለሚገቡ የተሻለ ተንቀሳቅሰው ሦስት ነጥቡን ለማግኘት እንደሚጥሩ ይገመታል። በተለይ ደግሞ የቡድኑ የአማካይ መስመር የጨዋታውን የኃይል ሚዛን እንዲቆጣጠሩ እንደሚያደርግ ይታሰባል።

እስካሁን ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ የተሸነፈው ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ ከመቀመጫ ከተማው ስምንት ነጥቦችን ከያዘ በኋላ በድሬዳዋ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ የወቅቱን ምርጥ እና የሊጉ መሪ ቡድን ኢትዮጵያ መድን አሸንፎ በጥሩ ጎዳና ላይ እንዳለ አስመስክሯል ፤ በአዲሱ አሠልጣኝ ሥርም ከጨዋታ ጨዋታም በሁሉም የሜዳ ክፍሎች መሻሻል እያሳየ ይገኛል። በጨዋታ ከሁለት ጎል በላይ አስተናግዶ የማያውቀው የኋላ መስመርም እየተረጋጋ የመጣ ሲሆን ከፊት ሁነኛ የሳጥን ውስጥ አጥቂ ባያገኝም እንኳን ከየአቅጣጫው ግቦችን እያገኘ ውጤቶችን እየሰበሰበ ነው። እንደ 6ኛው ሳምንት ተጋጣሚው መድን ቡናም ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት የሚፈልግ ስለሆነ ለኳስ ቁጥጥር ያለውን ተነሳሽነት በመቀነስ ፈጣኖቹን የወገብ በላይ ተጫዋቾች ብቃት ያማከለ የሽግግር አጨዋወት ሊከተል ይችላል።

ኢትዮጵያ ቡና ነገም የመስፍን ታፈሰ እና አስራት ቱንጆን ግልጋሎት አያገኝም። በባህር ዳር ከተማ ደግሞ አምበሉ ያሬድ ባየህ ከጉዳቱ አገግሞ ሲመለስለት ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና አደም አባስ ግን ከጉዳት አለማገገማቸው ተጠቁሟል።

በእስካሀኑ ስድስት ግንኙነታቸው ተመጣጣኝ ውጤት ያላቸው ቡና እና ባህር ዳር አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ የመጨረሻ አራት ጨዋታዎቻቸው ደግሞ በአቻ ውጤት ፈፅመዋል። በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ ቡና አስራ አንድ እንዲሁም ባህር ዳር ሰባት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

ይህንን ጨዋታ ተከተል ተሾመ በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በዓለም ዋንጫ ምክንያት በድሬዳዋ የመጨረሻ የዲ ኤስ ቲቪ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን የሚያገኘው የድሬ እና ኤሌክትሪክ ጨዋታ ደግሞ 1 ሰዓት ሲል ይጀምራል።

በመቀመጫ ከተማው በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ረገድ መሻሻል በማሳየት እየተጫወተ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ድሉን በደጋፊዎቹ ፊት ለማግኘት በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይገመታል። እርግጥ እስካሁን በሁሉም ጨዋታዎች ቢያንስ አንድ ጎል እያስተናገደ የተረጋጋ እና የተዋሀደ የተከላካይ ክፍል ማግኘት ባይችልም በማጥቃቱ ረገድ ግን ጨዋታ በጨዋታ እድገት እያሳየ ነው። በተለይ በአሠልጣኙ እምነት እያገኘ ተቀዳሚ ምርጫ የሆነው ቢኒያም ጌታቸው በቀጥታ ጎሎች ላይም ሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ እየተሳተፈ የፊት መስመሩን እያሾለው ይገኛል። ከእርሱ በተጨማሪም የአማካይ እና አጥቂ ክፍሉን በሚገባ እያገናኘ የሚገኘው ኤሊያስ አህመድም ለቡድኑ የከወገብ በላይ እንቅስቃሴ ጥንካሬን አላብሷል። የተከላካይ ክፍል ችግር ላለበት ኢትዮ ኤሌክትሪ ደግሞ ይህ ፈተና ሊሆን ይችላል።

ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ዋና እና የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኙን ወደ መዲናው ጠርቶ ካነጋገረ በኋላ የግብ ዘቡን አሠልጣኝ ወደ ታዳጊ ቡድኑ መላኩ ይታወቃል። ከዚህ የአሠልጣኝ ሽግሽግ በኋላ ነገ በተሻለ የመነቃቃት ስሜት እንደሚጫወት ይገመታል። ቡድኑ በ7ኛው ሳምንት በመድን ቡድኑ ሲረታ ራሱን ከጭቃው ጋር ለማስማማት መካከለኛ ርዝመት ያላቸው ኳሶችን ቀላቅሎ የነበረ ቢሆንም በመድን አማካዮች የተወሰደበት ብልጫ ጨዋታው ከእጁ እንዲወጣ ምክንያት የሆነ ይመስላል። በተጨማሪም በኋላ መስመሩ ላይ የነበረው አስገዳጅ የተጫዋቾች ለውጦች የተከላካይ ክፍሉ እንዳይረጋጋ በማድረግ ክፍተቶችን እንዲፈጥር አድርጎታል። ከፊትም ስል አጥቂ ማጣቱ ምናልባት ነገ የሔኖክ መመለስ ሊያሻሽለው እንደሚችል ይታሰባል። ቡድኑ እና አሠልጣኙ ካለባቸው የማሸነፍ ጫና መነሻነት ደግሞ ማጥቃት ላይ ያተኮረ አቀራረብ ሊከተሉ እንደሚችሉ ቀድሞ መናገር ይቻላል።

ድሬዳዋ ከተማ አቤል ከበደን በህመም እንየው ካሣሁንን ደግሞ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ አድርጓል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ተስፋዬ በቀለ እና ሚኪያስ መኮንንን በጉዳት ሲያጣ አጥቂው ሔኖክ አየለ ግን ለጨዋታው ይደርስለታል።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 14 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 6 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ 2 ጊዜ ረቷል። በ6 አጋጣሚዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ድሬዳዋ 10 ሰያስቆጥር ኤሌክትሪክ 19 አስቆጥሯል።

ይህ ፍልሚያ ደግሞ በአዳነ ወርቁ አልቢትርነት እንደሚከወን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ያጋሩ