ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ ከኋላ ተነስቶ ኤሌክትሪክን ድል አድርጓል

የቢኒያም ጌታቸው እና ቻርለስ ሙሴጌ የሁለተኛ አጋማሽ ጎሎች ድሬዳዋ ከተማን በመቀመጫ ከተማው ሁለተኛ ድል አቀዳጅተውታል።

01:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ከመቻሉ የአቻ ውጤት ብሩክ ቃልቦሬን በአቤል አሰበ ቦታ ሲያስጀምር በመድን ሽንፈት ያገኛቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከኋላ ማታይ ሉልን በአላዛር ሽመልስ እንዲሁም ከፊት ልደቱ ለማን በኢብራሂም ከድር ምትክ በቀዳሚ አሰላለፋቸው ውስጥ አካተዋል።

በሁለቱም በድኖች ዘንድ በሚታይ መሀል ሜዳ ላይ ኳስ የመቆጣጠር ፍላጎት በጀመረው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከኳስ ውጪ በቶሎ የተጋጣሚን እንቅስቃሴ የማቋረጥ ጥረት ታይቶባቸው የተሻለ ጫና ፈጥረዋል። በዚህም 9ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተገኘ ዕድል በሙሴ ካበላ እና ማታይ ሉል በግንባር የመግጨት ጥረት ከከሸፈ በኋላ ጨዋታው በመልስ ምት ሲቀጥል ቡድኑ ቀዳሚ የሆነበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ድሬዎች ከግብ ክልላቸው ኳስ መስርተው ለመውጣት ባደረጉት ጥረት አሳንቴ ጎድፍሬድ ለብሩክ ቃልቦሬ ለማቀበል ሲሞክር አቋርጦ ዮሴፍ ዮሐንስን በማለፍ ሳጥን ውስጥ የደረሰው ናትናኤል ሰለሞን ኤሌክትሪክን ቀዳሚ አድርጓል። ከአንድ ደቂቃ በኋላም ሌላኛው አጥቂ ልደቱ ለማ ከአማረ በቀለ ስህተት ሌላ ግብ ለመጨመር ተቃርቦ ነበር።

ከግቡ በኋላ ድሬዳዋ ከተማዎች አንፃራዊ የማጥቃት ጫና በመፍጠር የተሻሉ መስለው ቢታዩም 19ኛው ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ መሐመድ ከቀኝ መስመር ቅጣት ምት እንዲሁም 25ኛው ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ መሐመድ በፈጣን ጥቃት ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያደረሷቸውን ኳሶች የሚጠቀም አጥቂ አላገኙም። በቀጣይ ደቂቃዎች አጋማሹ ችኮላ በተሞላባቸው እና በሚቆራረጡ ቅብብሎች የቀጠለ ነበር። አልፎ አልፎ ብልጭ የሚሉ ፈጣን ቅብብሎችን ይከውኑ የነበሩት ኤሌክትሪኮች 36ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ናትናኤል ከተከላካይ ጀርባ ያሳለፈውን ኳስ ልደቱ ሳጥን ውስጥ ደርሶ ቢሞክርም ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

በአጋማሹ ጭማሪ ደቂቃዎች በሁለቱ የግብ ክልሎች አደገኛ ዕድሎች ተፈጥረው ታይተዋል። ልደቱ ከሌላ የአሳንቴ ጎድፍሬድ ስህተት ሳጥን ውስጥ ደርሶ ለግብ ቢቀርብም ዳንኤል ተሾመ ሲያድንበት በሌላኛው ግብ ቢኒያም ጌታቸው ከቻርለስ ሙሴንጌ የተሻገረለትን ኳስ በደካማ የግንባር ሙከራ አምክኗል።

ከዕረፍት መልስ ድሬዎች አማካዩ ብሩክ ቃልቦሬን አስወጥተው ሙኸዲን ሙሳን በማስገባት የማጥቃት ኃይላቸውን ጨምረዋል። ሆኖም በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ኤሌክትሪኮች በአብነት ደምሴ እና ስንታየሁ ዋለጬ የከረሩ ምቶች ሙከራ አድርገዋል ፤ በተለይም የስንታየሁ የ50ኛ ደቂቃ የቀኝ መስመር ሙከራ በዳንኤል ተሾመ ጥረት የዳነ ነበር። በሁለቱም በኩል እጅግ ደካማ በነበሩ የማጥቃት ሙከራዎች በቀጠለው ጨዋታ ቀጣዩ ሙከራ የታየው 66ኛው ደቂቃ ላይ አሳንቴ ጎድፍሬድ ከመሐመድ አብዱለጢፍ የቀኝ መስመር የቅጣት ምት በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ ሲወጣበት ነበር።

በአመዛኙ ረዥም ኳሶችን ወደ ቢኒያም ጌታቸው ያደርሱ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ ያሰቡትን አግኝተዋል። መሀል ሜዳ ላይ ከአብነት ደምሴ ያተቀማውን ኳስ ሙኸዲን በግራ መስመር ይዞ ገብቶ ሲያሻማ ቢኒያም ራሱን ከተከላካዮች ነፃ በማድረግ በግንባሩ ግብ አድርጎታል።

ተጋጣሚዎቹ ሌላ ግብ ለማግኘት በሚያደርጉት ያልተረጋጋ ጥረት ውስጥ ጨዋታው በድጋሚ ወደሚቆራረጡ ቅብብሎች እና ደካማ የማጥቃት ሂደቶች ተመልሶ ቢታይም ግቡ ያነሳሳቸው ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻለ የማጥቃት ጫና መፍጠር ችለዋል። የዚህን ፍሬም ቡድኑ 88ኛው ደቂቃ ላይ ሲያገኝ ከዳንኤል ተሾመ የተለጋውን የመልስ ምት ተከትሎ ቻርለስ ሙሴጌ የኤሌክትሪክን ተከላካዮች ዝንጉነት በአግባቡ ተጠቅሞ በመግባት የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎችን ያስፈነጠዘች ውድ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ውጤቱን ማስጠበቅ የቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በሜዳቸው ካደረጉት ሦስተኛ ጨዋታ ሰባት ነጥቦችን መሰብሰብ ያስቻላቸውን ድል አሳክተዋል።

አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ከዕረፍት በፊት የተሳቱ ኳሶች ፣ አስገዳጅ የጉዳት ቅያሪዎች እና ግለሰባዊ ስህተቶች ለሽንፈት እንደዳረጓቻው በመግለፅ ሽንፈቱን ከዕድል ጋር ሲያገናኙ ተጫዋቾቻቸውን ከመውቀስ ተቆጥበው ስላደረጉት ጥረት አመስግነዋል። አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ በበኩላቸው በዋናነት ከዕረፍት መልስ ቡድናቸው በመጠኑ መረጋጋት መቻሉ ለውጤት እንዳበቃቸው ገልፀው ቀድመው ግብ የማስተናገዳቸውን ጉዳይ በቀጣይ አሻሽለው ለመምጣት እንደሚሰሩ አስተድተዋል።