8ኛ የጨዋታ ሳምንት ፍፃሜውን የሚያገኝባቸውን ሁለት የነገ መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፋችን ቀርበዋል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
የዕለቱ የመጀመሪያ መርሃግብር ማሸነፍን አጥብቀው የሚሹትን ሁለቱን ቡድኖች እርስ በእርስ ያገናኛል።
የተረጋጋ የውድድር ዘመን ጅማሮ ለማድረግ የተቸገሩት አርባምንጭ ከተማዎች አሁን ላይ በአምስት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በተከታታይ በጥራታቸው ከላቁ ተጋጣሚዎች ጋር እጅግ ፈታኝ መርሃግብሮች ውስጥ የሰነበተው ቡድኑ ከባህር ዳር ጋር የነበረው የተራዘመው ጨዋታ ቀን አለመታወቁን ተከትሎ ነገ ፋሲልን የሚገጥሙበት ጨዋታ የዚህ ፈተና ማብቂያ ይመስላል። ከፋሲሉ ጨዋታ በኋላ በተከታታይ በንፅፅር “ማሸነፍ የሚችሏቸው” መርሃግብሮች የሚጠብቁት ቡድኑ ግን በፍጥነት ራሱን ፈልጎ ማግኘት ይጠበቅበታል።
በሊጉ እስካሁን በአንድ ጨዋታ ብቻ ድል የቀናቸው አርባምንጭ ከተማዎች አሁንም የመጀመሪያ ተመራጭ ተሰላፊ ተጫዋቾቻቸውን ፍለጋ ለውጦችን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። እስካሁን በስብስባቸው ከያዟቸው ተጫዋቾች መካከል ሃያ አራቱን የተጠቀሙት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከተጫዋቾች ባለፈ በጨዋታዎች ቡድኑ የተለያዩ ነገሮችን ለመሞከር ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን ውጤታማውን መንገድ በመፈለግ ላይ ይገኛሉ።
ፊት ላይ ኬኒያዊው አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶ ከጉዳት መልስ የጨዋታ ዝግጁነቱን እያሻሻለ መገኘቱ በአውንታዊነት የሚነሳ ቢሆንም በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ተስፋ ፈንጥቆ የነበረው ሁለገቡ ተመስገን ደረሰ ተፅዕኖ ግን ከጨዋታ ጨዋታ እየደበዘዘ መምጣት ለአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ስጋት የሚያጭር ነው።
በአርባምንጭ ከተማዎች በኩል አቤል ማሞ በነገው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት የማይኖር ሲሆን የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ቡድን አባል የነበሩት ቡጣቃ ሸመና እና አቡበከር ሻሚል ግን ከሀገራዊ ግዴታቸው ተመልሰዋል።
ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በ7ኛ ሳምንት የነበራቸው ጨዋታ መሰረዙን ተከትሎ በሊጉ ሦስት ቀሪ ጨዋታዎች የሚቀሯቸው ፋሲል ከነማዎች ወደ 8ኛ የጨዋታ ሳምንት የሚያመሩት በሰባት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሊጉ በወጥነት በሰንጠረዡ አናት ሲፎካከሩ የምናውቃቸው ፋሲል ከነማዎች እርግጥ ገና የውድድር ዘመኑ ጅማሬ ላይ ቢገኝም የዘንድሮ አጀማመራቸው አመርቂ አልሆነላቸውም። ዕድሎችን በመፍጠርም ሆነ ግቦችን በማስቆጠር ረገድ እየተቸገረ የሚገኘው ቡድኑ ከፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ወጥ የሆነ ግልጋሎትን ለማግኘት ተቸግሯል። የውድድር ዘመኑን በፍቃዱ ዓለሙ ሁለት ግቦች ታግዘው የጀመሩት ፋሲሎች በቀጣይ በነበሩት ጨዋታዎች የፍቃዱ ዓለሙን መቀዛቀዝ ተከትሎ አማራጮችን እያሰሱ ይገኛሉ። በመጨረሻው ጨዋታም ከታችኛው የሊግ እርከን የተገኘውን ጉልላት ተሾመን በፊት አጥቂነት ማስጀመራቸው የችግሩን አሳሳቢነት ማሳያ ነው።
ከማጥቃቱ ጀርባ በነፃ ስምንት ቁጥር ሚና የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የነበሩትን ሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መለዮን በዘንድሮው የውድድር ዘመን በጉዳት ምክንያት እስካሁን ማጣመር ያልቻሉት ፋሲሎች ተክተዋቸው ከሚገቡት አማካዮችም እንዲሁ የተሻለ ግልጋሎትን ይጠብቃል። ዐፄዎቹ በተቀሩት ድሬዳዋ ከተማ ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ውጤቶችን በመሰብሰብ የውድድር ዘመኑ ጉዟቸውን መስመር ማስያዝ የግድ ይላቸዋል።
በፋሲል ከነማዎች በኩል አሁንም አማካዮቹ ሃብታሙ ተከስተ እና ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን በተመሳሳይ ሌላኛው አማካይ ይሁን እንዳሻው በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገርም አጠራጥሯል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በፕሪምየር ሊግ በስድስት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ፋሲል ከነማ ሦስቴ እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች በአንድ አጋጣሚ ሲያሸንፉ የተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።
10 ሰዓት የሚደረገውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሚካኤል ጣዕመ በመሀል ዳኝነት እንደሚመሩት ይጠበቃል።
ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ወልቂጤ ከተማ
አራት ተከታታይ ሽንፈት በማስተናገድ በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲዎችን ከውጤት አልባ ጉዞ በኋላ እያንሰራሩ ከሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ጋር የሚያገናኘው ጨዋታ የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ መርሃግብር ይሆናል።
አዲስ አዳጊዎቹ ለገጣፎ ለገዳዲዎች ህይወት በፕሪምየር ሊግ ከተጠበቁት በላይ የከበዳቸው ይመስላል። በሁለት ተከታታይ አዎንታዊ ውጤቶች ሊጉን የጀመረው ቡድን በመጨረሻ አራት ጨዋታዎች በሙሉ ሽንፈትን አስተናግዶ በአራት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ይገኛል።
ለገጣፎዎች በሊግ ጨዋታ ግብ ካስቆጠሩ ከአምስት ሰዓታት በላይ የተቆጠሩ ሲሆን በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በድምሩ ስድስት ብቻ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን የማድረጋቸው ነገር በካርሎስ ዳምጠው እና ተፈራ አንለይ ላይ ስለተንጠለጠለው የቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ ወቅታዊ ሁኔታ በቂ ማስረጃ ነው። ቡድኑ በሊጉ የመቆየት ውጥኑን ለማሳካት በተለይ በመጀመሪያ ዙር የሚሰበስባቸው ነጥቦች እጅግ ወሳኝ መሆናቸውን ተከትሎ ለገጣፎዎች በፍጥነት ነጥቦችን ወደ መሰብሰብ መመለስ የማይችሉ ከሆነ በሁለተኛው ዙር ነገሮች እንዳይከብዱባቸው ስጋትን ያጭራል።
በተከታታይ ሽንፈቶች መነሻነት እየወረደ የሚገኘው የቡድኑን የራስ መተማመን ለመመለስ ከፍተኛ ሥራን የሚጠብቃቸው አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ እና ረዳቶቻቸው በተለይ በመጨረሻው ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና በጭማሪ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ቢሸነፉም በጨዋታው በመላው 90 ደቂቃ የነበራቸው ጥረት ተስፋ የሚሰጥ መሆኑ ለቀጣይ ጨዋታዎች ተስፋ እንዲሰንቁ የሚያደርግ ይሆናል።
በለገጣፎ ለገዳዲዎች በኩል በነገው ጨዋታ ዮናስ በርታ እና አቤል አየለ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም።
ከተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ውጤት አልባ ጉዞ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ባስመዘገቧቸው አራት ነጥቦች የተረጋጉ የሚመስሉት ወልቂጤ ከተማዎች በአስር ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ግቦችን ለማግኘት ጌታነህ ከበደ ላይ ጥገኛ ለሆኑት ወልቂጤ ከተማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከአንድ የውድድር ዘመን በኋላ የቀድሞ ቡድኑ ላይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ከግብ የታረቀው እና በጨዋታው ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበረው አቡበከር ሳኒ እነዚህን ግቦች እንደ መነሳሻ በመጠቀም ብዙዎች በአንድ ወቅት ተስፋ ጥለውበት የነበረውን አቅሙን ዳግም ያሳየን ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
እንደ ማጥቃቱ ሁሉ በመከላከሉ ወቅት በተለይ በመስመሮች የሚደረጉ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ የተወሰኑ ክፍተቶች ያሉበት ቡድኑ ከዋሀብ አዳምስ ባለፈ ለመከላከሉ ግለሰባዊ ስብዕናዎችን እንደሚፈልግ እየተመለከትን እንገኛለን።
በወልቂጤ ከተማዎች በኩል ጀማል ጣሰው በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ከሜዳ መሰናበቱን ተከትሎ በነገው ጨዋታ በቅጣት የማይኖር ሲሆን ሌላኛው የግብ ዘብ ሮበርት ኦዶንካራ በጉዳት ምክንያት እንዲሁ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። በሌላ በኩል ተከላካዩ ቴዎድሮስ ሀሙም የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል።
ሁለቱን ቡድኖች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ዮናስ ማርቆስ በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።