ሪፖርት | አርባምንጭ እና ፋሲል ነጥብ ተጋርተዋል

በአዞዎቹ እና በአፄዎቹ መካከል የተደረገው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ከወጣበት አሰላለፍ መሪሁን መስቀላ ፣ በላይ ገዛኸኝ እና ተመስገን ደረሰን በአቡበከር ሻሚል ፣ አሸናፊ ኤልያስ እና አሕመድ ሁሴን በማሰለፍ ጨዋታውን ጀምሯል። ፋሲል ከነማ በበኩሉ በስድስተኛ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ከተረታበት ስብስቡ መናፍ አወል እና ጉልላት ተሾመን በይሁን እንደሻውን እና ፍቃዱ ዓለሙ ተክቶ ለጨዋታው ቀርቧል።

ጥሩ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች መሪ የሆኑበትን ጎል ያስቆጠሩት ገና በአምስተኛው ደቂቃ ነበር። ከቀኝ መስመር በጥሩ መንገድ ያሻገረለትን ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ በሚገባ ኳሱን ተቆጣጥሮ አስቆጥሯል። 

ከጎሉ በኋላ ባሉት 15 ደቂቃዎች ፋሲሎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ወደፊት መጓዝ ሲችሉ በ12ኛው ደቂቃ በናትናኤል ወልደጊዮርጊስ ከሳጥን ውጪ መትቶ በይስሐቅ ተገኝ የተያዘበት ሙከራ የሚጠቀስ ነበር።

የመከላከል አደረጃጀታቸው እንደ ወትሮው ያልነበረው አርባምንጭ ከተማዎች በቀላሉ ፋሲል ከነማ በመስመሮች በኩል የሚያደርገውን የማጥቃት ሽግግር መቆጣጠር ሲሳናቸው ተመልክተናል። ያም ቢሆን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመግባት ግልፅ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ጀምረዋል። በተለይ በ19ኛው ደቂቃ ኤሪክ ካፓያቶ ከሳጥን ውጪ በጥሩ ሁኔታ አክርሮ የመታውን ሚካኤል ሳማኪ በአስደናቂ ሁኔታ ወደ ውጭ በማውጣት አድኖበታል።
ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ ከማዕዘን ምት የተሻገረንውን አሸናፊ ፊዳ ነፃ ኳስ አግኝቶ ወደ ውጭ የሰደዳት ለአዞዎቹን አቻ የሚሆኑበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

የጨዋታው እንቅስቃሴ ወደ ተመጣጣኝነት ተቀይሮ ፋሲል ከነማዎች በ24ኛው ደቂቃ ሌላ የጎል አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት በመሄድ ሽመክት ጉግሳ ከመስመር ያሻገረለትን ታፈሰ ሰለሞን ሳጥን ውስጥ አንድ ተከላካይ አሸማቆ በማለፍ ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አገባው ሲባል ይስሀቅ ተገኝ ወደ ውጭ አውጥቶበታል። ይህ ኳስ በድጋሚ ከማዕዘን ምት ሲመለስ አርባምንጮች በድጋሚ ወደ ፊት በመሄድ በ26ኛው ደቂቃ እጅግ ለጎል የቀረበ አጋጣሚ አሸናፊ ኤልያስ አግኝቶ ወደ ሰማይ የሰደዳት አዞዎቹን ወደ ጨዋታው መመለስ የሚችል ሌላ ዕድል ነበር።

የጨዋታው ፍጥነት በቀሩት ደቂቃዎች እየተቀዛቀዘ መጥቶ የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ከናትናኤል የተነሳውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ በጥሩ መንገድ ያቀበለውን ለጎሉ ሁለት ሜትር ርቀት ባዶ ጎል አግኝቶ ፍቃዱ በግንባር በመግጨት ያልተጠቀመበት የፋሲልን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ የሚችል ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ በቶሎ ጎል የማስቆጠሩ ተራ የአርባምንጭ ከነማ ሆኗል። በ52ኛው ደቂቃ ከከግራ መስመር ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት አሸናፊ ኤልያስ በቀጥታ በመምታ ግሩም ጎል በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። 

ከጎሉ በኋላ እምብዛም ለጎል የቀረበ ሙከራ ያልታጀበ ሆኖ ቢቀጥልም የጨዋታውን መንፈስ የሚረብሽ የኃይል አጨዋወት በሁለቱም በኩል ሲፈፀም ተመልክተናል ፤ ይህም የጨዋታው ፉክክርን ቀንሶታል።

የመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎችን ሙሉ ለሙሉ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት አርባምንጮች ጨዋታውን አሸንፈው የሚወጡበትን የጎል አጋጣሚዎች ፈጥረዋል። በ82ኛው ደቂቃ ተመስገን ደረሰ በግንባሩ ገጭቶ በቀላሉ ሚካኤል ሳማኪ የያዘበት ከሦስት ደቂቃ በኋላ ራሱ ተመስገን ሳጥን ውስጥ አሕመድ ሁሴን ወደ ጎል መቶት በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ ያገኘውን ኳስ በድጋሚ ወደ ጎል ቢመታውም ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

በረጃጅም ኳሶች የፋሲል ከነማን ተከላካዮች ሲረብሹ የቆዮት አርባምንጮች 88ኛው ደቂቃ ተመስገን ደረሰ የተላከውን ኳስ በግንባሩ ጨርፎ ያቀበለውን አሕመድ ሁሴን ኳሱን በደረቱ አብርዶ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል ቢመታውም በዕለቱ ፋሲሎችን ሲታደግ የዋለው ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኪ በአስደናቂ ሁኔታ ጎል እንዳይሆን አድርጎታል። ጨዋታውም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ያጋሩ