የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንፋስ ስልክ ድል ሲቀናው ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

የ2015 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ድል ሲያስመዘግብ መከላከያ ከልደታ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ነጥብ በመጋራት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐ-ግብሮች በሦስት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነዋል ፡፡ ረፋድ 4 ሰዓት ሲል አዲስ አዳጊው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ የሚለውን መጠሪያ ይርጋጨፌ ቡና በሚል ስያሜ በለወጠው ቡድን መካከል ተደርጓል፡፡ በአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ መሪነት ጨዋታቸውን ያደረጉት ይርጋጨፌ ቡናዎች በተሻለ አቅም በተጋጣሚያቸው ሙሉ በሙሉ የጨዋታ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ቢሆንም የኋላ መስመር ተሰላፊ የሆኑ ተከላካዮች በሰሩት የአቋቋም ስህተት ጎል ሊቆጠርባቸው ችሏል፡፡

ከዕረፍት መልስ 79ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ፈጣን የሽግግር ሂደት አጥቂዋ በሬዱ ታምሩ ንፋስ ስልክን አሸናፊ ያደረገች ግብን በቀድሞው ክለቧ ላይ አስቆጥራ ጨዋታው በአዲስ አዳጊው ክለብ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የማሸነፊያ ጎልን ለንፋስ ስልክ ከመረብ ያሳረፈችው አጥቂዋ በሬዱ በቀለ የጨዋታ ምርጥ ተብላ ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡

8 ሰዓት ላይ ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን የመቻል እና ልደታ ክፍለ ከተማ ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ተደርጎ ነጥብ በመጋራት ተጠናቋል፡፡ ሙሉውን የጨዋታ ክፍለጊዜ መቻሎች ኳስን በመቆጣጠር በተደጋጋሚ ወደ ልደታ የግብ ክልል በመድረስ በሴናፍ ዋቁማ እና ምርቃት ፈለቀ አማካኝነት የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የጣሩበትን ሂደት መመልከት ብንችልም የልደታዋ ግብ ጠባቂ ስመኝሽ ፍቃዱ በአስደናቂ ብቃት በቀላሉ ወደ ጎልነት እንዳይለወጡ ስታደርግ አስተውለናል፡፡

አብዛኛዎቹን የጨዋታ ደቂቃዎች ጥንቃቄ አዘል አጨዋወትን በመከተል ወደ መስመር በኩል በህዳት ካሱ አማካኝነት በማዘንበል ሲጫወቱ የነበሩት ልደታዎች 25ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህም ሀና በኃይሉ እና ህዳት ካሱ ጥሩ ተቀባብለው በመጨረሻ ህዳት ለረድኤት ዳንኤል የሰጠቻትን ኳስ አጥቂዋ ወደ ጎልነት ለውጣው ቡድኑን መሪ አድርጋለች፡፡ ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ብርቱ ትግልን ያደርጉ የነበሩት መቻሎች ተሳክቶላቸው በምርቃት ፈለቀ አማካኝነት አቻ ሆነው ጨዋታው 1ለ1 ተደምድሟል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የልደታ ክፍለ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ስመኝሽ ፍቃዱ የጨዋታ ምርጥ ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል የተደረገ ሲሆን በሜዳ ላይ ጠንካራ ፉክክርን ሳያስመለክተን ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በአንፃራዊነት የተሻለ ብቃትን ያሳየችው የድሬዳዋ ግብ ጠባቂ ብርሀን ባልቻ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡