በመጨረሻው የሊጉ የጨዋታ ሳምንት ላይ ጎልተው የወጡ ተጨዋቾች እና አሰልጣኝን የመረጥንበት የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ይህንን ይመስላል።
አሰላለፍ 4-3-3
ግብ ጠባቂ
ሚኬል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ
የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ ከሆነ በኋላ በብቃቱ ዙርያ ጥያቄ የሚነሳበት የዐፄዎቹ የግብ ዘብ በቅርብ ጨዋታዎች ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ቡድኑ ከአርባምንጭ ጋር ባደረገው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ እንደተወሰደበት ብልጫ መሸነፍ የሚችልበት ዕድል ቢፈጠርም ሳማኬ በድንቅ ብቃቱ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ የአርባምንጭን ኳሶች አምክኗል።
ተከላካዮች
ብርሃኑ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
በሀዋሳው ጨዋታ ብርሃኑ በመከላከሉም በማጥቃቱም በኩል ፈጣን ሽግግሮችን በማድረግ በኮሪደሩ ጥሩ ተንቀሳቅሷል። ፀጋዬ ብርሃኑ ላስቆጠረው ግብ ከማዕዘን መነሻ ሲሆን ወደ ግብነት ባይቀየርም በጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል። በመጨረሻ ደቂቃዎች ኳስ በእጁ ነክቶ ፍፁም ቅጣት ምት ቢያሰጥም በብዙ ጠንካራ ጎኖቹ በቦታው ተመራጭ አድርጎታል።
አሸናፊ ፊዳ – አርባምንጭ ከተማ
አዞዎቹ እና ዐፄዎቹን ባገናኘው ጨዋታ በተለየም በሁለተኛው አጋማሽ የፋሲል ከነማን ጥቃቶች በመቆጣጠር ቡድኑን ከአደጋ ይከላከል የነበረው አሸናፊ ተጋጣሚው ለማጥቃት ተስቦ በሚመጣባቸው ጊዜያት የፊት አጥቂዎቹን የማከሉ ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት በመላክ ማጥቃቱንም ሲያግዝ ተስተውሏል።
አሚን ነስሩ – መቻል
መቻል እንደቡድን በጥሩ መከላከል የቅዱስ ጊዮርጊስን ማጥቃት በተቋቋመበት ጨዋታ አሚን በግሉ ንቁ ሆኖ አሳልፏል። በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ያሳልፋቸው የነበሩ ውሳኔዎች በተለይም የሊጉን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን እየመራ ያለው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በጨዋታው ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንዳይኖረው የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል።
ዳዊት ማሞ – መቻል
በጨዋታ ሳምንቱ እንደወትሮው በማጥቃት ተሳትፏቸው ልቀው የወጡ የግራ መስመር ተከላካዮችን ባናገኝም ዳዊትን ተመራጭ አድርገናል። ተጫዋቹ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እምብዛም በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ባይገኝም የቅዱስ ጊዮርጊስ የቀኝ መስመር ጥቃት አደገኛ ዕድሎችን እንዳይፈጥር በታታሪነት ተነቀሳቅሷል።
አማካዮች
አለልኝ አዘነ – ባህር ዳር ከተማ
የጣና ሞገዶቹ ቡናማዎቹን በረቱበት ጨዋታ የመሃል ሜዳውን ሚዛን በሚገባ በመጠበቅ እና ብዙ ቦታዎችን በማካለል የቡና አማካዮች የጎል ዕድል እንዳይፈጥሩ ከማድረጉ በዘለለ የተሳካ ቅብብል እንዳያደርጉ በማቋረጥ ለራሱ ቡድንም የግብ ዕድሎችን በመፍጠር በጨዋታው ጎልቶ መውጣት ችሏል።
ዮናስ ገረመው – ኢትዮጵያ መድን
መድኖች የሊጉን መሪነታቸውን አጠናክረው በቀጠሉበት ጨዋታ በግላቸው ጎልተው ከታዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ዮናስ ነበር። ቡድኑ እንደተለመደው አማካይ ክፍል ላይ ለነበረው የበላይነት ቅብብሎችን በማሳለጥ እና የማጥቃት ሂደቱን በመምራት መሪ የነበረው ተጫዋቹ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብም አስቆጥሯል።
አበባየሁ አጂሶ – ወላይታ ድቻ
ወጣቱ አማካይ አሁንም መሻሻሉን በመቀጠል በድቻ ቤት ለትልልቅ ኃላፊነቶች ራሱን እያዘጋጀ ይመስላል። ቡድኑ አዳማን ሲረታ አማካይ ክፍል ላይ ጥሩ በመንቀሳቀስ እና ለአጥቂው ቃልኪዳን ዘላለም ቀርቦ በመጫወት ከግራ የቡድኑ ወገን የሚነሱ የማጥቃት ዕድሎችን ሲፈጥር የነበረው አበባየው ለወሳኟ ፍፁም ቅጣት ምት መገኘትም መነሻ ሆኖ ታይቷል።
አጥቂዎች
ቻርለስ ሙሴጌ – ድሬዳዋ ከተማ
በአሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ስር ከቀኝ መስመር የመነሳት ኃላፊነት የተሰጠው የጋንዳዊው አጥቂ ከጨዋታ ጨዋታ አስተዋፅኦው እየጎላ ይገኛል። በኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ ከመሐመድ አብዱለጡፍ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር የግራ መስመር የጥቃት መነሻ በመሆን የግብ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ያደረገ ሲሆን በመጨረሻም ወሳኟን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል።
የኋላሸት ሰለሞን – ወልቂጤ ከተማ
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከአራተኛው ሳምንት ጀምሮ የመሰለፍ ዕድል የሰጡት የመስመር አጥቂው የኋላሸት ራሱን ለማሳየት ዕድሉን በመጠቀም ወደፊት ተስፋ የሚጣልበት አጥቂ መሆኑን እያሳየ ይገኛል። ሠራተኞቹም ለገጣፎን በረቱበት ጨዋታ የሊጉን የመጀመርያ ጎሉን ለማግኘት ችሏል።
ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ
በወልቂጤ ከተማ የሊጉ ድል ውስጥ ሁሌም ሜዳ ውስጥ ካለ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የጎል ቀበኛው ጌታነህ ከበደ በዚህም ሳምንት የውድድር ዘመኑን ሰባተኛ ጎል ላይ ያደረሱትን ሁለት ጎሎች ከማስቆጠሩም ባሻገር አንድ ግብ የሆነ ኳስ በማቀበል ጥሩ ምሽትን አሳልፏል።
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ
ባለፉት የውድድር ዓመታት ወጥ አቋም ማሳየት ይቸገር የነበረው ባህር ዳር ከተማን መልክ እያስያዙት የሚገኙት አሰልጣኝ ደግአረገ ተከታታይ ድል በማሳካት የሳምንቱ ኮከባችን ሆነዋል። በሳምንቱ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ጨዋታዎች መካከል አንዱ በነበረው የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ቡድናቸው በጥሩ የጨዋታ ቁጥጥር ለድል እንዲበቃ ማድረጋቸው ለኮከብነት አብቅቷቸዋል።
ተጠባባቂዎች
አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን
ተስፋዬ መላኩ – ወልቂጤ ከተማ
ዳግም ንጉሴ – ሀዲያ ሆሳዕና
ፉዐድ ፈረጃ – ባህር ዳር ከተማ
ሀብታሙ ሸዋለም – ኢትዮጵያ መድን
ዮናታን ኤሊያስ – ወላይታ ድቻ
ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ
ኪቲካ ጀማ – ኢትዮጵያ መድን