አሠልጣኝ ክፍሌ ቦልተ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመለያየታቸው ነገር እርግጥ ሆኗል።
ትናንት ባደረስናቹሁ መረጃ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በድጋሚ በክለቡ ጥሪ ተላልፎላቸው ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መሆኑን እና ዛሬም ከክለቡ የቦርድ አካላት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ የሰማን መሆናችንን ገልፀን ነበር። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ከክለቡ ባገኘነው መረጃ መሠረት የውጤት መሻሻል በቡድኑ ውስጥ አለመታየቱን ተከትሎ በዛሬው ዕለት በደብዳቤ ማሰናበታቸውን አውቀናል። በጊዜያዊነትም ምክትል አሰልጣኙ ገዛኸኝ ከተማ ቡድኑን እንደሚመሩ ታውቋል።
“ከባለፈው ውይይት በኋላ ቡድኑን እንዳስተካክል ተነግሮኛል ፤ ሆኖም በአንድ ጨዋታ ሁሉን ነገር ማስተካከል አይቻልም። በመለያየቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም በከፍተኛ ጫና ነበር ስሰራ የቆየሁት” የሚሉት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና “ቀሪ የሰባት ወር ውል አለኝ ፤ ጥቅማጥቅሞቼ መከበር ስላለባቸው ጉዳዮን በጠበቃዬ አማካኝነት ወደ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ይዤ አመራለው” ብለዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ እስከ ስምንተኛ ሳምንት ባደረጋቸው ጨዋታዎች በአምስት ነጥብ አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።