በሁለቱ አጋማሽ የተቆጠሩት ሁለት ግቦች ሲዳማ ቡና መቻልን እንዲረታ አድርገዋል።
መቻል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለግብ ከተለያየበት ጨዋታ ከነዓን ማርክነህ እና ግርማ ዲሳሳን በማሳረፍ ፍፁም ዓለሙ እና በረከት ደስታን ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ አምጥቷል።
በኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ያስተናገደው ሲዳማ ቡና በበኩሉ በመጫወቻ ቦታዎች ላይ ሁሉ አሰላለፉን ለውጦ ገብቷል። ግብ ጠባቂው ፍሊፕ ኦቮኖ ከቅጣት መልስ በተመሳሳይ ቅጣት ያገኘው መክብብ ደገፉን ቦታ ሲወስድ የመስመር ተከላካዮቹ ደግፌ ዓለሙ እና ሰለሞን ሀብቴ በአማኑኤል እንዳለ እና መሀሪ መና ሚና ተተክተዋል። አማካይ ክፍል ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ሙሉዓለም መስፍንን እንዲሁም ከፊት ደግሞ ቡልቻ ሹራ እና ፀጋዬ አበራ እንዳለ ከበደ እና ጎድዊን ኦባጄን በመተካት ጨዋታውን ጀምረዋል።
የተመጣጠነ የኳስ ቅብብል ማሳየት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 17 ደቂቃ ድረስ የጠሩ የግብ ማግባት ሙከራዎች አልተደረጉበትም ነበር። በአንፃራዊነት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የሚያገኟቸውን ኳሶች ወደ ግብ በማድረስ ረገድ ሻል ያሉት ሲዳማዎች ይገዙን ማዕከል ያደረጉ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪም ከኳስ ውጪ የመቻልን ተከላካዮች ተጭነው በመጫወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠን ሲሞክሩ ታይቷል። ይህ ውጥናቸው ፍሬ አፍርቶም ግሩም ሀጎስ ለአሚኑ ነስሩ አቀብላለው ብሎ ያሳጠረው ኳስ የደረሰው ፍሬው ሰለሞን እየገፋ በመግባት ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።
በጊዜ መመራት የጀመሩት መቻሎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተራቸውን ጀምረዋል። እርግጥ እንደተመሩ ወደ አቻነት ለመሸጋገር ጥድፊያ የተሞላበት አጨዋወት ሲከተሉ ስለነበር አካሄዳቸው የሚፈልጉትን እንዲያሳኩ አላደረገም። ይህ ቢሆንም ግን ተከታታይ ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎችን ሰንዝረው ነበር። በቅድሚያ የአጥቂ አማካዩ ፍፁም ዓለሙ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሲያመክን በቀጣይ ደግሞ ከመስመር ተሻምቶ የተመለሰን ኳስ በኃይሉ ግርማ አግኝቶት ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ የሞከረው ኳስ በተከላካዮች ተመልሶበታል።
የሚፈልጉትን ቶሎ ያገኙት ሲዳማዎች ከግቡ በኋላ ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት ሲንቀሳቀሱ ነበር። ይህ የሲዳማ ማፈግፈግ የጠቀማቸው መቻሎች ደግሞ ይበልጥ ተጭነው መጫወት ይዘዋል። በ35ኛው ደቂቃም በድጋሜ ፍፁም በሳጥኑ የግራ ክፍል ፍጥነቱን ተጠቅሞ ገብቶ የሞከረው ኳስ ግብ ጠባቂው ፍሊፕ ኦቮኖ አድኖታል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ከቀኝ መስመር የተሻማን ኳስ ግብ ጠባቂው ኦቮኖ በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ያገኘው ምንይሉ አጋጣሚውን ይጠቀማል ተብሎ ሲጠበቅ በደንብ ሳይመታው ቀርቶ ተከላካዮች አውጥተውታል።
ከዕረፍት መልስ መቻሎች የመከላከል ባህሪ ያለው ተጫዋች ቀይረው የማጥቃት ባህሪ ያለው ተጫዋች ወደ ሜዳ ሲያስገቡ ሲዳማዎች ደግሞ ተቃራኒ ኃላፊነት የሚወጣ ተጫዋች በመለወጥ ጨዋታውን መከወን ቀጥለዋል። እንደ ተጫዋች አመራረጣቸውም ሲዳማዎች በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት ተንቀሳቅሰዋል።
እምብዛም የግብ ሙከራዎች ያልነበሩበት ይህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት ያስመለከተው በ66ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህ ደቂቃም ምንይሉ ወንድሙ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በረከት ደስታ በግንባሩ ሞክሮት ወጥቶበታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሳጥኑ ጫፍ የተገኘን የቅጣት ምት በረከት ደስታ ለመጠቀም ጥሮ ነበር።
በሚፈልጉት መልኩ ጨዋታው የቀጠለላቸው ሲዳማዎች ጥሩ እየተከላከሉ የሚያገኙዋቸውን ኳሶች በፍጥነት በመላክ መቻልን ለመፈተን እና ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረዋል። በ75ኛው ደቂቃም መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድገዋል። በዚህም ሙሉቀንን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሙሉዓለም ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ በግንባሩ አስቆጥሯል። በቀሪ ደቂቃዎች መቻሎች ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማግኘት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ሦስት ነጥብ አስረክበው ወጥተዋል።