የአሠልጣኞች አስተያየት | መቻል 0-2 ሲዳማ ቡና

“ውጤት የተጠማ ቡድን ያገኘውን ድል ማስጠበቅ የግድ ይለዋል” ሥዩም ከበደ


“በእኔ ዕምነት በማጥቃቱ ላይ ያለን ነገር ዋጋ እያስከፈለን ነው” ፋሲል ተካልኝ

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ሲዳማ ቡና

ከ4ለ0 ሽንፈት ስላገገሙበት መንገድ…

“ዛሬ ከነበርንበት ቦታ ለመላቀቅ በነበሩን ልምምዶች ላይ የሰራናቸውን ስህተቶች እና ያበላሸናቸውን ነገር ለማስተካከል ሞክረናል። ከምንም በላይ ደግሞ በመድኑ ጨዋታ የነበሩትን የራሳችን ክፍተቶች ለማረም ጥረናል። በጨዋታው የነበረውም የተጫዋቾቹ ሥነ-ልቦና ወርዶብኝ ነበር። ይሄንን ለማስተካከል በክፍልም ጭምር የተለያዩ ምሳሌዎችን በማምጣት ለማስረዳት ሞክረናል። በተጨማሪም ልምምድ ሜዳ ላይ የማየውን ነገር እየተንተራስኩ ለውጦችን አድርጌያለው። የመጫወቻ ቦታ የማንም ርስት አይደለም። ይህንን ተከትሎ ሁሉም በደንብ ተነሳስተው ነው ወደ ሜዳ የመጡት። በዚህም ውጤቱን በማግኘታችን ደስተኞች ነን።

በጨዋታው ስላደረጉት የተጫዋች እና የአጨዋወት ለውጥ…

“የሜዳው አለመመቸት ነው እንጂ አማካይ ላይ ለምሳሌ ሙሉቀን፣ ፍሬው እና ቴዎድሮስ ያላቸው የኳስ ፍሰት የሚገርም ነው። መስመር ላይም ያሉት እንደዛው። እንዳልኩት የሜዳው ችግር ነው እንጂ ከዚህም በላይ መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾችን ነው ያስገባነው። ወደፊት ደግሞ በደንብ እየተግባባን ስንሄድ የተሻለ ይሆናል። ሲዳማ ብዙ ደጋፊ ያለው ክለብ ነው። የክለቡ አመራሮችም በጣም እየደገፉኝ ከጎኔ ናቸው። በዚህ ድጋፍ ይሄንን ድል ማግኘታችን የበለጠ ያነቃቃናል።

የመጀመሪያውን ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ስለመረጡት የመከላከል አጨዋወት…

“ውጤት የተጠማ ቡድን ያገኘውን ድል ማስጠበቅ የግድ ይለዋል። ከዚህ ባለፈም ወጥቼ ልጫወት ብትል ሜዳው የሚመች አይደለም። እንደፈለክ ኳሱን ለማንሸራሸር አይመችም። እነርሱም መጫናቸው ያን ያህል መጥፎ አይደለም። መገደባችን በመልሶ ማጥቃት እንድንወጣ አድርጎናል። የተገኘን ውጤት እያብላላህ ነው መጫወት ያለብህ። በዛሬው ጨዋታ አስፈላጊያችን የነበረው ሙሉ ነጥብ ማግኘቱ ነበር።”

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – መቻል

ስለጨዋታው…

“በጨዋታው የመጀመሪያው እና ሁለተኛውን ጎል በማስተናገዳችን መካከል ያለው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። የግብ ዕድሎችንም አግኝተን ነበር። ጎሎች እኛ ላይ በቀላሉ ነው የሚቆጠሩት። በተቃራኒው ደግሞ እኛ የምናገኛቸውን ዕድሎች አንጠቀምም። ብዙ ዕድሎችን እናባክናለን። የጨዋታው ለውጥም ይሄ ነው።

የሚገኙ የግብ ማግባት ዕድሎችን ስላለመጠቀም…

“ውጤቱን ከመፈለግ ነው። ይሄንን ባለፈው ጨዋታም ለማስተካከል ጥረት አድርገናል። ተጫዋቾች ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ሲገኙ ከአዕምሯቸው ውጪ ነው የሚሆኑት። በጣም ቀላል ቀላል ኳሶች ነበር ሲሳቱ የነበረው። ይሄንን ማስተካከል የግድ ይጠበቅብናል። ሲዳማ ያገኛቸውን የግብ ዕድሎች ነው የተጠቀመው። እኛ ከእነርሱ የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረን አልተጠቀምንም። ከፊት አቅም ያላቸው ተጫዋቾች አሉን። ግን ያቅማቸውን ያህል እያገኘን አይደለም።

ቡድኑ ላይ ስላለው የእንቅስቃሴ ችግር…

“ስትከላከል አትኖርም። በማጥቃቱ ጎል እያገባህ ቡድኑን እስካላገዝክ ድረስ ጎሎችን ታስተናግዳለህ። ተከላካዩን ማገዝ የምትችለው አንተ ጎል ስታገባ ነው። ዛሬም ግብ ያስተናገድነው ከእኛ ስህተት የተገኘ እንጂ የእነርሱ የማጥቃት አቅም ከእኛ የመከላከል አጨዋወት በልጦ አይደለም። እኛ በሰራነው ስህተት ነው ጎል ያስተናገድነው። ከዛ በኋላ የጎል ዕድሎችን ፈጥረን ግን አላገባንም። በአጠቃላይ በእኔ እምነት በማጥቃቱ ላይ ያለን ነገር ዋጋ እያስከፈለን ነው።”