በመጀመሪያው አጋማሽ ድንቅ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሀዋሳ ከተማ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል ሸምተዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ባደረጋቸው ለውጦች አቤኔዜር ዮሐንስ ፣ ብርሀኑ አሻሞ እና ከቅጣት የተመለሰው እዮብ ዓለማየሁ ወደ ቀዳሚው አሰላለፍ መጥተው በቃሉ ገነነ ፣ ዳዊት ታደሰ እና ዓሊ ሱለይማን አርፈዋል። ከመቻል ጋር ነጥብ የተጋራው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ረመዳን የሱፍን በሄኖክ አዱኛ ምትክ ተጠቅሟል።
ጨዋታውን በጥሩ መንገድ የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ፈጣን ጥቃቶችን መሰንዘር ጀምረዋል። በተለይ የመስመር ተጫዋቾቻቸውን ፍጥነት በመጠቀም ገና በጊዜ ጨዋታውን ወደ ራሳቸው ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ነበር። ብዙም ደጅ ሳይጠኑ በ6ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂያቸው ባህሩ ነጋሽ የተላከን ኳስ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ የመጀመሪያውን ፍልሚያ አሸንፎ ለአማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባሩ ሲያመቻችለት አማኑኤል በጥብቅ ምት የግቡን ቋሚ አጋጭቶ ከመረብ ጋር አዋህዶታል።
ገና በጊዜ ፈተና የጠናባቸው ሀዋሳዎች ግባቸውን በሚገባ መጠበቅ ተስኗቸው በተደጋጋሚ ሲጋለጡ ተመልክተናል። በ12ኛው ደቂቃም ከመስመር የተነሳን ኳስ ግዙፉ አጥቂ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።
አሁንም በፈጣን አጨዋወት የሀዋሳን ግብ ከመጎብኘት ያልቦዘኑት ጊዮርጊሶች በ16ኛው ደቂቃ ሌላ ለግብ የቀረቡበትን ሁነት አስተናግደዋል። አጎሮ ቸርነት የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ የሰጠውን ኳስ በድጋሚ ወደ ግብ ልኮ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ አድኖበታል። ሙንታሪ የመለሰውን ኳስ ደግሞ ሀይደር ለመጠቀም ጥሮ ወጥቶበታል። ከደቂቃ በኋላ ግን ከቆመ ኳስ ሁለተኛ ግብ አስቆጥረው የሀዋሳን ጨዋታ አክብደዋል። በዚህም ከመዓዘን የተሻማን ኳስ መሐመድ ሙንታሪ በአግባቡ ማፅዳት ሳይችል ጋቶች ፓኖም አግኝቶት ወደ ግብነት ቀይሮት የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጓል።
በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ውጤታማ ያልሆኑት ሀዋሳዎች እጅግ የተለዩ በነበሩት ጊዮርጊሶች ከፍ ያለ ብልጫ ተወስዶባቸው ታይቷል። ከምንም በላይ በወጥነት መዋሀድ ያልቻለው የተከላካይ መስመራቸው ዋጋ እያስከፈላቸው ነበር። በተቃራኒው ጎል ፊት ምንም ርህራሄ ማሳየት ያልፈለጉት ፈረሰኞቹ በ32ኛው ደቂቃ ሦስተኛ ጎል አግኝተዋል። የቡድኑ የመሐል አጥቂ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ራሱን ነፃ አድርጎ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመገኘት ቢኒያም በላይ ሰብሮ በመግባት የላከውን ኳስ በተለምዷዊው ግራ እግሩ መዳረሻውን የሙንታሪ መረብ አድርጎታል።
ጨዋታው የከበዳቸው ሀዋሳዎች ጭራሽ በ39ኛው ደቂቃ ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ ዓይነት ነገር ገጥሟቸዋል። በዚህም የተከላካይ አማካያቸው ብርሃኑ አሻሞ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጎ ከባዱን ፈተና በጎዶሎ ተጫዋች መጋፈጥ የግድ ብሏቸዋል። አጋማሹ ተገባዶ አራተኛ ዳኛው ጭማሪ ደቂቃ በሚያሳዩበት ቅፅበትም አራተኛ ጎል በአጎሮ አማካኝነት ሊቆጠርባቸው ከጫፍ ደርሶ ነበር።
ማጥቃቱን እና መከላከሉን ማመዛዘን የሚገባቸው ሀዋሳዎች በሁለቱ የሜዳ ክፍሎች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የሚና እና ሰው ሽግሽግ ቢያደርጉም በዕለቱ አልቀመስ ያሉትን ጊዮርጊሶች በቀላሉ መብለጥ አልቻሉም። የቁጥር ብልጫውን በሚገባ መጠቀም የቀጠሉት የአሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ተጫዋቾች ደግሞ በ54ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ በፈጠረው ዕድል ለሌላ ጎል ተቃርበው ነበር። በድጋሚም በ59 እና 60ኛው ደቂቃ ፍሪምፖንግ እና አማኑኤል በሞከሯቸው ኳሶች ጥሩ ቡጢ ሰንዝረው ተመልሰዋል።
ጨዋታው 63ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያውን የጠራ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሰንዝሯል። በዚህም በአጋማሹ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተባረክ ሄፋሞ ሙጂብ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ያመቻቸለትን ኳስ ወደ ግብ ልኮት ባህሩ በጥሩ ቅልጥፍና አድኖበታል። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በረከት ሳሙኤል ከቅጣት ምት የተሻለ ሙከራ አድርጎ ለጥቂት ዒላማውን ስቶበታል።
82ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳ የማስተዛዘኛ ጎል የሚያገኝበትን የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ በእጅ በመነካቱ ምክንያት አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በጨዋታው ብዙም ያልተፈተነው ባህሩ ነጋሽ የዓሊን ደካማ ምት አድኖታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ሌላ ሙከራ ሳይስተናገድ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።