ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጊዜያዊነት አሰልጣኞችን ሾሟል

ከአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር የተለያየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለት አሰልጣኞች እየተመራ ቀጣዮቹን የድሬዳዋ ጨዋታዎች እንዲያከናውን ተወስኗል፡፡

በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከከፍተኛ ሊጉ በማደግ እየተካፈለ የሚገኘው ስመ ጥሩ ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከታችኛው የሊግ ዕርከን ካሳደገው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር በሊጉ ያለፉትን ስምንት ጨዋታዎች ካደረገ በኋላ ከውጤት መጥፋት እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ በጋራ ስምምነት መለያየቱን ገልፀን ነበር፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዛሬ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ ጀምሮ በሁለት አሰልጣኞች እንዲመራ የክለቡ ቦርድ በትናንትናው ዕለት ውሳኔን ስለማሳለፉ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡

በዚህም መሠረት የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ረዳት እና ጊዜያዊ አሰልጣኝ የነበሩት እንዲሁም የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ረዳት የነበሩት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ድሬዳዋ ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎችን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ ተወስኗል።

በረዳት አሰልጣኝነት ሚና ደግሞ የቀድሞው የክለቡ ተጫዋች እና የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ሆኖ የሰራው ስምኦን አባይ ቡድኑን እንደሚቀላቀል ይጠበቃል፡፡ ሁለቱ አሰልጣኞች በቀሩት የድሬዳዋ መርሀግብሮች ውጤታማ የሚሆኑ ከሆነ የዋና ኃላፊነት ሚናን እንደሚያገኙም አረጋግጠናል፡፡