የአሠልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 0-3 ቅዱስ ጊዮርጊስ

“ከመጀመሪያው ጀምሮ ለማሸነፍ የነበረን ነገር በመጀመሪያው አጋማሽ የምንፈልገውን ይዘን እንድንወጣ አድርጎናል” ዘሪሁን ሸንገታ


“አንድ ጨዋታ ቀረፃ ሳይኖረው ተደርጎ ምን ያህል ቡድናችንን ዋጋ እንዳስከፈለው ታይቷል” ዘርዓይ ሙሉ

ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው…

ጥሩ ነው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለማሸነፍ የነበረን ነገር በመጀመሪያው አጋማሽ የምንፈልገውን ይዘን እንድንወጣ አድርጎናል። በተለይ ተጫዋቾቼ ያደረጉት ነገር ደስ ብሎኛል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በተደጋጋሚ ስለሚያስቆጥሯቸው ጎሎች..

የተወሰኑ ውጤቶችን አጥተን ነበር፡፡ ዕኩል ለዕኩል ብዙ ጨዋታዎችን የወጣነው ለዛም ቁጭት ነበረብን፡፡ ምን ማድረግ እንደነበረብን ምን መስራት እንደነበረብን ተነጋግረን የነበረንን ቅርፅ እና የነበረንን አጨዋወት ወደ ጥሩ ነገር ቀይረን ጥሩ ነገር ይዘን ወጥተናል።

የቁጥር ብልጫን ስላለመጠቀማቸው…

ውስንነት ሳይሆን መጫወት ያለብንን በአግባቡ እንሄዳለን የምንስታቸው ኳሶች አሉ። በዚህ ሂደትም ይመጡብናል እንጂ በአግባቡ ተጫውተው ኳሱን ያዝ አድርገው ለመጫወትና የቁጥር ብልጫውን ፈልገናል አድርገውናል፡፡ ብዙ ኳሶችን ስተናል። እነኚህ ነገሮች ላይ ጥሩ ነገር ሰርተን የተሻለው ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማየት ነው የምንፈልገው።

ስለ ቀጣዮቹ ጉዞዎች

ሁሌም ሂደት ነው። ከፊት ከፊት ያሉትን ጨዋታዎች ነው የምንጫወተው። ሁሉም ቡድን ከእኛ ጋር ሲመጣ የሚመጣበት መንገድ የተለየ እና ሌላ ቅርፅ ነው ያለው። ሁሌ የራሳችንን ቅርፅ እና የማሸነፍ ፍላጎታችንን ከፍ አድርገን የምንጫወትበት ዘይቤዎች አሉን። የራሳችን ሲስተሞች አሉን በእዛ ውስጥ ጥሩ ነገሮችን አድርጎ ለማሸነፍ እና ወደ ነበርንበት መንገድ ለመሄድ ነው የምናስበው”፡፡

ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው…

ከእረፍት በፊት በነበረው ነገር ደስተኛ አይደለሁን። በማይሆኑ ጥፋቶች በተደጋጋሚ ፊሽካ ሲነፋ ነበር። በዚህም ጊዮርጊስ ኳሊቲው በሆነው የቆመ ኳስ ለመጠቀም ሲጥር ነበር። እነዛ ፋውሎች ያሰጣሉ የሚለው ነው ትልቁ ነገር። አንድ ጨዋታ ቀረፃ ሳይኖረው ተደርጎ ምን ያህል ቡድናችንን ዋጋ እንዳስከፈለው ታይቷል። ከዚህ ውጪ የተሰጠው ቀይ ካርድ የቡድናችንን ትልቁን እንቅስቃሴ አበላሽቶታል። ሁለትም ሆነ ሦስት ለባዶ ብትመራ ቢያንስ ጎል አግብተህ አቻ የመሆን ዕድልህ ሰፊ ነው። በ30 ደቂቃ ጎል ገብቶብህ በ30 ደቂቃ ተጫዋች ከወጣብህ ዋጋ ነው የምትከፍለው። እንዳልኩት ግን ገና በአንድ ቀረፃ በሌለው ጨዋታ ቡድናችን ዋጋ ከፍሏል ፤ ይሄ መታረም አለበት። በዚህ ሁኔታ ውድድር ማድረግ ከባድ ነው። እነሱ ውጤት እንደሚፈልጉ ሁሉ እኛም ውጤት እንፈልጋለን። እኛ ጭራሽ ጨዋታውን እንዳንመራ ነው ያደረገን። በአጠቃላይ ዛሬ በነበረው ነገር በጣም ነው ያዘንኩት። ከእረፍት በኋላ ጎዶሎ ሆነንም ኳሱን ተቆጣጥረን ጎሎች እንዳይገቡብን አድርገን ተጫውተናል። ከዛ በፊት የነበሩ ስህተቶች ግን ዋጋ አስከፍሎናል።

ቡድኑ ላይ ስለነበረው የመከላከል ክፍተት…

የቡድኔ የመከላከል ክፍል ችግር እንዳለበት ይታወቃል። ግን ዛሬ ይህንን የጋበዘን የተፈጠሩት ነገሮች ናቸው። ተቃራኒ የሚጠቀመው የቆመ ኳስን ነበር። ይሄ እንዲሆን ምንጩ ነው የተገኘው። የእኛ የተከላካይ ክፍል ችግር እንዳለ ሆኖ በተደጋጋሚ የተፈጠሩት ነገሮች እኛ ላይ ችግር እንዲፈጠር አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወደጨዋታው ለመመለስ ስላደረጉት ነገር…

እኔ ሁሌ የማምነው ጎል ከገባ መሸነፍ መሸነፍ ነው። ለማሸነፍ እና ጎሎች ለማግባት ማጥቃት አለብህ። እኛ አልተጠቀምንም እንጂ ፍፁም ቅጣት ምትን ጨምሮ ሌሎች ዕድሎችን አግኝተን አልተጠቀምንም። ጎሎቹን ማጥበብ ይቻል ነበር። ለእኔ ሁል ጊዜ ጎሎች በገቡ ቁጥር ሸሽቶ መጫወት ለእኔ አዋጭ አይደለም። አጥቅቶ መጫወት ነው አስፈላጊው። ለዚህም ጊዮርጊስ አማካይ ላይ ብዙም ስላልሆነ መሐሉን ሳሳ አድርገን አጥቂ አስገብተን የእነሱን ረጃጅም ኳሶች ተቆጣጥረን ወጥተናል። በጨዋታው መጀመሪያ ላይ የተቆጠሩብን ጎሎች ዋጋ ቢያስከፍሉንም ተጫዋቾቼ ጎሉን ለማጥበብ እና ሌላ እንዳይቆጠር ያደረጉት ነገር ጥሩ ነበር።