ሪፖርት | ብርትካናማዎቹ በመድን ላይ ጣፋጭ ድል ተጎናፅፈዋል

ድሬዳዋ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ ጎሎች በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ድል ያገኘበትን ውጤት ኢትዮጵያ መድን ላይ አስመዝግቧል።

ኢትዮጵያ መድን ሲዳማ ቡናን የረታበትን ስብስብ በመጀመሪያ አሰላለፉ ሳይለውጥ ሲቀርብ ኢትዮ ኤሌክትሪክን የረታው ድሬዳዋ ከተማ አቤል አሰበ እና ያሬድ ታደሰን በሱራፌል ጌታቸው እና ሔኖክ ሀሰን ተክቶ ወደ ሜዳ ገብቷል።

ከተከታታይ ድል በኋላ ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ኢትዮጵያ መድኖች ገና በ2ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም በቀኝ መስመር ኪቲካ ጅማ እየገፋ ወደ ሳጥን ገብቶ ያሻማውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ አግኝቶት ወደ ግብ ቢልከውም ኳስ መስመር ከማለፏ በፊት አብዱለጢፍ መሐመድ በደረቱ መልሷታል። በመጀመሪያው ቡጢ እጅ ያልሰጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው ኳሱን በሚገባ በመቆጣጠር ወደ ፊት ጠጋ ብለው ለመጫወት ሲሞክሩ ታይቷል።

የሚያገኙትን ኳስ በፈጣን ቅብብል ወደ ግብ በማድረስ የተሻሉት መድኖች በ20ኛው ደቂቃም በመሐል አጥቂያቸው ሲሞን ፒተር አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል። ከደቂቃ በኋላ ግን በራሳቸው ስህተት ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። በዚህም ቢኒያም ጌታቸው ተከላካዮች የተሳሳቱትን ኳስ አግኝቶ ወደ ግብነት ቀየረው ተብሎ ሲጠበቅ በወረደ አጨራረስ አጋጣሚውን አምክኖታል። በ24ኛው ደቂቃ ደግሞ አሰጋኸኝ ጼጥሮስ ያሻማውን የመዓዘን ምት ቁመታሙ ተከላካይ አሳንቴ ጎድፍሬድ በግንባሩ ሞክሮት ለጥቂት ወጥቶበታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ መድኖች ሲሞን ፒተር በድጋሜ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝቶ የግብ ዘቡ ዳንኤክ ተሾመ በጥሩ ቅልጥፍና ባዳነው ኳስ መሪ ሊሆኑ ነበር።

አጋማሹ ሊገባደድ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት በመቀመጫ ከተማቸው እየተጫወቱ የሚገኙት ድሬዳዋዎች ቀዳሚ ሆነዋል። በዚህም ያሬድ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል በኩል የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው አቡበከር ሲመልሰው ተከላካዮች ቢያርቁትም ዮሴፍ ዮሐንስ አግኝቶ ወደ ግብ ሲመታው ጀርባውን ለጎሉ ሰጥቶ የነበረው ቢንያም ወደ ኋላ አመቻችቶለት ሙሴጌ በግሩም ሁኔታ አክርሮ በመምታት አስቆጥሯል። አጋማሹም በድሬዳዋ መሪነት ተጠናቋል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሁለተኛው አጋማሽ ተጠናክረው ወደ ሜዳ የገቡት ኢትዮጵያ መድኖች የአጥቂ መስመራቸው ላይ ለውጥ ቢያደርጉም እስከ 70ኛው ደቂቃ ድረስ ዳንኤል ተሾመን የፈተነ አጋጣሚ አልፈጠሩም። ድሬዎች በበኩላቸው ወረድ ብሎ መጫወትን በመምረጥ በመልሶ ማጥቃት እና ረጃጅም ኳሶች ብቻ በመንተራስ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ተንቀሳቅሰዋል። በ57ኛው ደቂቃም የግቡ ባለቤት ሙሴጌ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ጥብቅ ኳስ መጥቶ አቡበከር አውጥቶበታል። ወደ ውጪ የወጣውን ይህንኑ ኳስ ደግሞ አሰጋኸኝ ከመዓዘን ምት ሲያሻማው ቢኒያም በግንባሩ ሞክሮት ዒላማውን ስቶበታል።

70ኛው ደቂቃ ላይ የገብረመድህን ኃይሌ የተጫዋች ለውጥ ፍሬ አፍርቶ መድን ወደ አቻነት ተሸጋግሯል። በዚህም በ55ኛው ደቂቃ ኪቲካ ጅማን ተክቶ የገባው ሀቢብ ከማል በጥሩ ምት ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ቡድኑን አቻ አድርጓል። 

ከ3 ደቂቃዊች በኋላ ድሬዳዋዎች በፈጣን የመስመር ላይ ሽግግር መድን የግብ ክልል ደርሰው ቢኒያም ዳግም መሪ ሊያደርጋቸው ተቃርቦ ነበር።

የጨዋታው መገባደጃ ላይ ሳይጠበቅ ሁለት ተከታታይ ግቦች ተቆጥረዋል። በ88ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ኤልያስ አህመድ ጨርፎት ወደ መስመር ሲወጣ አቤል አሰበ አግኝቶ ያሻማውን ኳስ አሳንቴ ጎድፍሬድ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ የድሬን መሪነት አስመልሷል። በጭማሪው ሦስተኛ ደቂቃ ላይ ደግሞ በጥሩ የመልሶ ማጥቃት ያሬድ ታደሰ ያሳለፈለትን ኳስ ቻርልስ ሙሴጌ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ወደ ሳጥን በመግባት በአቡበከር ኑራ መረብ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በድሬዳዋ 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።ተጠናቋል።