በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መካከል የሚደረገው የጥሎ ማለፍ ውድድር ሩብ ፍፃሜ ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ተጀምሯል፡፡ የአምናው ባለድል መከላከያም ደደቢትን በመርታት ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል፡፡
በጣለው ዝናብ ምክንያት በጨቀየው የአዲስ አበባ ስታድየም 11፡30 የተጀመረው ጨዋታ በተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ታጅቦ እንዲሁም ጥቂት የግብ ማስቆጠር አጋጣሚዎችን ብቻ አስገኝቶ የመጀመርያው አጋማሽ ካለ ግብ ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽም እንደመጀመርያው ሁሉ የረባ እንቅስቃሴ ያልታየበት ሲሆን ጨዋታው ካለግብ ተጠናቆ አሸናፊውን ለመለየት ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምት ያመራል ተብሎ ሲጠበቅ በ88ኛው ባዬ ገዛኸኝ የመከላከያን ወሳኝ የድል ግብ ከመረብ በማሳረፍ መከላከያን ወደ ድል መርቷል፡፡ ባዬ ገዛኸኝ በመጀመርያው ዙር መከላከያ የቀድሞ ክለቡ ወላይታ ድቻን 3-0 ሲረታ ሁለት ግቦችን ከመረብ ማሳረፉ የሚታወስ ነው፡፡
በጨዋታው የደደቢቱ አጥቂ ዳዊት ፍቃዱ በትከሻ ጉዳት በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የወጣ ሲሆን በቅርቡ ለደደቢት ፊርማውነ ንያኖረው ጋናዊው ተከላካይ ጆን ቱፎር የመጀመርያ ጨዋታውን አድርጓል፡፡
ድሉን ተከትሎ መከላከያ ለተከታታይ 4 አመታት ወደ ግማሽ ፍፃሜው መሸጋገሩን ሲያረጋግጥ ተሸናፊው ደደቢት ወደ አፍሪካ ውድድር የመመለስ ተስፋው ፕሪሚየር ሊጉን በማሸነፍ ላይ ብቻ እንዲንጠላጠል አስድዶታል፡፡
የሊጉ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ሲቀጥሉ አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ፣ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይጫወታሉ፡፡
ማስታወሻ – የዚህ ውድድር ይፋዊ ስያሜ “የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ” የሚል ነው፡፡ በሶከር ኢትዮጵያ ዘገባዎች ላይ “የሊግ ዋንጫ” በሚል ስያሜ የምንጠቀመው ለአጠራር እና አዘጋገብ አመቺ እንዲሆን በሚል ነው፡፡